"ሞት ለእስራኤል ጦር " ሲሉ መፈክር ያሰሙት ሙዚቀኞች ከማንችስተር ፌስቲቫል ተሰረዙ

ቦብ ቪላን

የፎቶው ባለመብት, PA Media

ፓንክ እና ራፕን አጣምረው የሚጫወቱት የዩናይትድ ኪንግደሙ ቦብ ቪላን ባንድ ሙዚቀኞች ባለፈው ቅዳሜ በግላስተንበሪ ፌስቲቫል ላይ "ሞት ለእስራኤል ጦር" በሚል መድረክ ላይ ባሰሙት መፈክራቸው ከማንችስተር ሙዚቃ ፌስቲቫል ተሰረዙ።

ባንዱ በመጪው ቅዳሜ የራዳር ፌስቲቫል ላይ ዋነኞቹ ሙዚቀኞች የነበሩ ቢሆንም አዘጋጆቹ በሰጡት መግለጫ የዚህ ፌስቲቫል አካል እንደማይሆኑ አረጋግጠዋል።

ቦብ ቪላን በበኩላቸው ለአድናቂዎቻቸው በኢንስታግራም በሰጡት ምላሽ "ወደ ማንችስተር እንመለሳለን" ብለዋል።

ቦብ ቪላን በተጨማሪም በመጪው እሁድ በፈረንሳዩ ፌስቲቫል ካቬ ፈስት የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ይጫወቱ የነበረ ቢሆንም የፌስቲቫሉ አዘጋጆች እንደሰረዟቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የባንዱ መሪ ቦቢ ቪላን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች በተገኙበት ግላስተንበሪ ፌስቲቫል ላይ "ፍልስጤም ነጻ እንደምትወጣ" እና ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ እና ምዕራቡ ዓለም በፍልስጤማውያን ላይ በሚፈጸመው ግድያ ተባባሪ ናቸው ብሏል።

ከዚያም በመቀጠል "ሞት ለእስራኤል መከላከያ ኃይል" ሲል መድረክ ላይ የተሰማው ቦቢ ቪላን ታዳሚዎችንም በመጋበዝ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች "ሞት ለእስራኤል መከላከያ ኃይል" በማለት መፈክር አሰምተዋል።

ይህንንም ተከትሎ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር "ሰቅጣጭ የጥላቻ ንግግር" ሲሉ ከማውገዝ በተጨማሪ በርካታ ፖለቲከኞች ከፍተኛ ውግዘት አሰምተዋል።

ቦብ ቪላን በበኩላቸው "እውነት በመናገራቸው ኢላማ ተደርገናል" ሲሉ በያዝነው ማክሰኞ በኢንስታግራም ገጻቸው ምላሽ ሰጥተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"እኛ አይሁዶች፣ አረቦች ወይም የትኛውም ዘር እንዲሞት አንፈልግም። እኛ የምንፈልገው ይህ ሁከት ፈጣሪ ወታደራዊ ማሽን [የእስራኤል መከላከያ ኃይል] እንዲፈርስ ነው። ይህ ወታደራዊ ማሽን አብዛኛውን ጋዛ ያወደመ ነው" ብለዋል።

አክለውም "እኛ ከዚህ በፊት መነጋገሪያ እንደሆኑት ሁሉ ዋነኛ ዜና አይደለንም። እኛ ከዋናው ዜና [ፍልስጤማውያን] ማዘናጊያ ነን፤ እናም የሚደርሱብን እርምጃዎች እንዲሁም ማዘናጊያ ይሆናል" ብለዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ፖሊስ በቦብ ቪላን ባንድ ላይ እንዲሁም በሌላኛው በፍልስጤም ድጋፋቸው በሚታወቁት የአየርላንድ ባንድ ኒካፕ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ የወንጀል ምርመራ መክፈቱን አስታውቋል።

ከዚያ በተጨማሪም የሜትሮፖሊታን (ለንደን) ፖሊስ ቃል አቀባይ ባንዱ ከአንድ ወር በፊት በአሌክሳንድራ ቤተ መንግሥት በነበራቸው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ በሰጡት አስተያየት ምርመራ ተከፍቷል ብለዋል።

ምርመራው የተከፈተው በዝግጅቱ ወቅት በስፍራው የተቀረጸ የሚመስል ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎ ነው ብለዋል። ነገር ግን ምርመራው መቼ እንደተጀመረ ግልጽ አይደለም።

ከሙዚቃ ፌስቲቫሎች መሰረዛቸውን ተከትሎ ቦብ ቪላን በሰጡት ምላሽ "ዝምታ ምርጫ አይደለም። ደህና እንሆናለን ፤ የፍልስጤም ህዝብ እየተጎዳ ነው" በማለት የጸና አቋማቸውን ደግመዋል።

ባንዱ በተጨማሪም ወደ ፊት ወደ ማንቸስተር እንደሚመለሱም አክለዋል።

በመስከረም ወር በጀርመኗ ኮሎኝ በሚደረገው የሙዚቃ ኮንሰርት ጎጎል ቦርዴሎ ለተሰኘው አሜሪካዊ ባንድ የመክፈቻ ሙዚቃ ይጫወታሉ ተብለው የነበሩት ቦብ ቪላን ከዚህም ተሰርዘዋል።

የግላስተንበሪ ፌስቲቫልን በቀጥታ እያሠራጨ የነበረው ቢቢሲ የቦብ ቪላንን የሙዚቃ ዝግጅት እንዲሁም "ሞት ለእስራኤል ጦር" የሚለውን መፈክር በቀጥታ አስተላልፏል።

ይህንንም ተከትሎ ቢቢሲ የቀጥታ ሥርጭቱን ማቋረጥ ነበረበት የተባለ ሲሆን፣ መገናኛ ብዙኃንን በበላይነት የሚቆጣጠረው ኦፍኮም የተባለው ተቋም ቃለ አቀባይ "የዚህ የሙዚቃ ዝግጅት ቀጥታ መተላለፉ በጣም አሳሳቢ ነው፤ ቢቢሲ መመለስ የሚገባው ጥያቄዎች አሉ" ብለዋል።

የቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር ቲም ዴቪ ማክሰኞ ለቢቢሲ አይሁድ ሰራተኞች ኔትወርክ በላኩት ኢሜይል "ቦብ ቪላን በግላስተንበሪ ዝግጅት ያሳየው ባህርይ አጸያፊ እና ፍጹም ተቀባይነት የለውም" ብለዋል።

ዳይሬክተሩ "በቢቢሲ ውስጥ ለጸረ ሴማዊነት ምንም ቦታ የለም" ሲሉ አክለዋል።