ህንድ አየር መንገዶች የቦይንግ አውሮፕላኖች የነዳጅ መቆጣጠሪያዎችን እንዲፈትሹ አዘዘች

በህንድ ለ260 ሰዎች ህይወት መቀጠፍ መንስዔ የቦይንግ አውሮፕላን ከተነሳ ከሰኮንዶች በኋላ የነዳጅ መቆጣጠሪያዎች ጠፍተው ወደ ሞተሩ የሚደርሰው ነዳጅ መቋረጡ መሆኑን ሪፖርት መውጣት ተከትሎ፤ህንድ አየር መንገዶች የአውሮፕላኑ ነዳጅ መቆጣጠሪያዎችን በጥብቅ እንዲፈትሹ መመሪያ አወጣች ።

የአገረቱ ሲቪል አቪዬሽን ዳይሬክቶሬት ጄነራል እንዳስታወቀው የህንድ እና አለም አቀፍ አየር መንገዶች በነዳጅ መቆጣጠሪያዎቹ ላይ የራሳቸውን ፍተሻ ማድረጋቸውን ተከትሎ መመሪያው እንደወጣ ገልጿል።

የአሜሪካ የፌደራል አቪዬሽን ባለስልጣን የቦይንግ የነዳጅ መቆጣጠሪያዎች ማብሪያና ማጥፊያዎች ደህንነታቸው የተጠበቀ ነው ብሏል።

የቦይንግ የነዳጅ መቆጣጠሪያ ማብሪያና ማጥፊያዎች ደህነንት ጥያቄ የተነሳባቸው የህንድ አየር መንገድ አውሮፕላን ከተነሳ ከሰኮንዶች በኋላ መቆጣጠሪያዎቹ ጠፍተው ነዳጅ ተቋርጦ እንደነበር አደጋውን አስመልክቶ የወጣው ቅድመ ሪፖርት ማመላከቱን ተከትሎ ነው።

ከአንድ ወር በፊት፣ ሰኔ 5/ 2017 ዓ.ም በምዕራብ ህንድ ከሚገኘው አህመዳባድ አየር ማረፊያ ወደ ለንደን እያቀና የነበረው ቦይንግ 787-87 ድሪምላይነር አውሮፕላን ከተነሳ ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ነው የተከሰከሰው።

260 ሰዎች በተቀጠፉበት በዚህ አሰቃቂ አደጋ አንድ እንግሊዛዊ መንገደኛ ብቻ በተአምር መትረፍ ችሏል።

ሪፖርቱ ቅዳሜ፣ ሐምሌ 5/ 2017 ዓ.ም ይፋ መሆኑን ተከትሎ ህንድም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ምላሽ ከመስጠት በተጨማሪ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስደዋል።

የህንድ አቪዬሽን ተቆጣጣሪ አየር መንገዶች የቦይንግ አውሮፕላኖች የነዳጅ መቆጣጠሪያዎች ማብሪያና ማጥፊያዎችን እስከ ሐምሌ 14/ 2017 ዓ.ም ድረስ ፈትሸው እንዲያጠናቅቁ ጠይቆ "የተቀመጠውን ቀነ ገደብ በጥብቅ መከተል የመብረር ብቃት እና የአፕሬሸኖችን ደህንነት ለማረጋገጥ መሰረታዊ ጉዳይ ነው" ብሏል።

አቪዬሸኑ የጠየቀው ፍተሻ የአሜሪካ የፌደራል ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በአውሮፓውያኑ 2018 ካወጣው ምክረ ኃሳብ ጋር የሚጣጣም ሲሆን ይሄም በቅድመ ሪፖርቱ ተጠቅሷል።

የህንዱ አቪዬሽን ባለስልጣን፣ ዲጂሲኤ አየር መንገዶች የነዳጅ መቆጣጠሪያዎች ላይ ፍተሻ አድርገው ሪፖርት እንዲያደርጉ መመሪያ አውጥቷል።

ሪፖርቱን ተከትሎ የአሜሪካው ሲቪል አቪዬሽን የ2018 ምክረ ኃሳብ "የነዳጅ መቆጣጠሪያዎቹ ማብሪያ/ ማጥፊያዎቹ በሚቆለፍ መልኩ የተገጠሙ ሲሆን" ይህም አውሮፕላኖቹን ደህንነቱ ያልተጠበቀ ያደርጋቸዋል ብሎ እንደማያምን ገልጿል።

የህንድ አየር መንገድ ፓይለቶችን የሚወክለው ማህበር በበኩሉ ፓይለቶችን ተከላክሎ መግለጫ አውጥቷል።

የህንድ ፓይለቶችን ማህበር ባወጣው መግለጫ በተከከሰው አውሮፕላን ውስጥ የነበሩት አብራሪዎች "በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ማድረግ ያለባቸውን በስልጠናቸው እና በተሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት እርምጃ ወስደዋል። ባልተሟላ መረጃ/ በግምት ላይ ተመስርቶ የፓይለቶቹን ስም ማጉደፍ ተገቢ አይደለም" ብሏል።

በህንዱ የአውሮፕላን አደጋ የምርመራ ቢሮ (AAIB) ቅዳሜ ዕለት የወጣው ሪፖርት አውሮፕላኑ ከተነሳ ከሰኮንዶች በኋላ መቆጣጠሪያዎቹ ከመብራት ወደ መጥፋት በመቀየራቸው ወደ ሞተሩ የሚወስደው ነዳጅ መቋረጡን መረጃ አመላክቷል።

አደጋውን ተከትሎ ከኮክፒት የተገኘ የድምጽ ቅጂ አንደኛው ፓይለት "ለምን አቋረጥከው?"ሲል የሚሰማ ሲሆን ሌላኛው አብራሪ ደግሞ "አኔ አላቋረጥኩትም" ሲል ይደመጣል።

ሪፖርቱ ማንንም "ጥፋተኛ ወይም ተጠያቂ ለማድረግ" ያቀደ አለመሆኑን አመላክቷል።

እንዲሁም ሰኞ እለት ደቡብ ኮሪያ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ሁሉም አየር መንገዶች የቦይንግ አውሮፕላኖች የነዳጅ መቆጣጠሪያዎች ማብሪያ ማጥፊያዎችን እንዲፈትሹ ለማዘዝ እየጠበቀች መሆኑን የሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።