መፈንቅለ መንግሥት የተፈጸመባቸው የጊኒ ቢሳው ፕሬዝዳንት ወደ ሴኔጋል ሸሹ

መፈንቅለ መንግሥት የተፈጸመባቸው የጊኒ ቢሳው ፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኤምባሎ ወደ አጎራቧች አገር ሴኔጋል መግባታቸውን የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። በዚህ ሳምንት መፈንቅለ መንግሥቱን በፈጸሙት ወታደሮች ተይዘው የነበሩት ፕሬዝዳንቱ ወደ ሴኔጋል የገቡት ተለቅቀው እንደሆነም ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

መፈንቅለ መንግሥት ፈጻሚዎቹ ፕሬዝዳንቱን የለቀቁት የምዕራብ አፍሪካ የትብብር ብሎክ በሆነው ኢኮዋስ አማካኝነት በተደረገ ድርድር ነው። ጊኒ ቢሳው ውስጥ የተፈጠረው ውጥረት እየጨመረ ባለበት በዚህ ወቅት የተደረገው ድርድር ፕሬዝዳንቱ ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲተላለፉ ያለመ ነበር።

የሴኒጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ፤ ኤምባሎ ሐሙስ ምሽት በቻርተርድ ወታደራዊ አውሮፕላን "በሰላም እና በጤንነት" ወደ አገሪቱ መግባታቸውን አስታውቋል።

በጊኒ ቢሳው ሥልጣን የያዘው ወታደራዊ ኃይል በበኩሉ ጄነራል ሆራታ ናታም በሽሽግር መሪነት ለአንድ ዓመት አገሪቱን እንዲመሩ ሾሟል።

የረቡዕ ዕለቱ መፈንቅለ መንግሥት የተፈጸመው፤ በአገሪቱ የተደረገው ፕሬዝዳንታዊ እና ፓርላሜንታዊ ምርጫ ጊዜያዊ ውጤት ይፋ ሊደረግ አንድ ቀን ሲቀረው ነው። ወታደራዊው ኃይል የምርጫ ሂደቱን አግዶ፤ ውጤቱም ይፋ እንዳይደረግ ከልክሏል።

በምርጫው ሲወዳደሩ የነበሩት ኤምባሎ እና በጠባብ ልዩነት የሚፎካከረው ፈርናንዶ ዲያስ በበኩላቸው ሁለቱም በፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ማሸነፋቸውን አውጀዋል።

ወታደራዊው ኃይል መፈንቅለ መንግሥቱን ያካሄደው፤ ስማቸውን ባልጠቀሳቸው እና "የታዋቂ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ድጋፍ" አላቸው ያላቸውን ፖለቲከኞች አገሪቷን ወደ አለመረጋጋት የመክተት ሴራ ለማክሸፍ እንደሆነ ተናግሯል። ወታደራዊው ኃይል የሰዓት እላፊም ጥሏል።

በሴኔጋል እና ጊኒ መካከል የምትገኘው ጊኒ ቢሳው፤ የእደንዛዥ ዕፅ አዋዋሪዎች ማዕከል በመሆን ትታወቃለች። በአውሮፓውያኑ 1974 ከፖርቹጋል ቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ የአገሪቱ ሠራዊት ከፍተኛ ተጽዕኖ ያለው አካል ሆኖ ቆይቷል።

የሦስት ልጆች እናት የሆነች አንዲት ነዋሪ፤ ይህ መፈንቅለ መንግሥት የመጀመሪያዋ እንዳልሆነ ለቢቢሲ ተናግራለች። ይሁን እንጂ ከተመዘገቡ መራጮች ውስጥ 65 በመቶ ያህሉ ተሳትፈውበታል ተብሎ የሚገመተውን ምርጫ ውጤት ለማወቅ እየተጠባበቁ ባሉበት ሰዓት መፈንቅለ መንግሥት መፈጸሙ ያልተጠበቀ እንደሆነ አስረድታለች።

"የተኩስ ድምጽ ሰማን። በሩጫ ሸሸን። ቦርሳችንን ሸክፈን ወደ ቤት ለመሄድ ነው የሞከርነው" ስትል በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ገልጻለች።

የዋና ከተማዋ ቢሳው ነዋሪ የሆነ ሌላ ሰው በበኩሉ በሁኔታ ደስተኛ እንዳልሆነ ተናግሯል። "ይሄ ማንንም አይጠቅምም። ምክንያቱም አገሪቱን ወደ ቀውስ ነው የሚከትታት" ሲል ስጋቱን አስረድቷል።

መፈንቅለ መንግሥቱን በተመለከተ በአገሪቱ ነዋሪዎች ዘንድ የተፈጠረው ስሜት ግን የተደበላለቀ ነው። የተወሰኑት ሠራዊቱ ለወሰደው እርምጃ ድጋፋቸውን በመግለጽ ሥርዓት ያለው የሽግግር ሂደት ይኖራል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል።

ሰንካር ጋሳማ የተባለ አንድ ነዋሪ፤ "በአገሪቱ ያለውን የኑሮ ሁኔታ እስካሻሻሉ ድረስ ወታደራዊ አገዛዝ ላይ ተቃውሞ የለኝም" ብሏል።

"ጊኒ ቢሳው ለጥሩ ኑሮ የሚሆኑ ሁኔታዎች የሚገኙባት እጅግ ሀብታም አገር" እንደሆነች የሚናገረው ነዋሪው፤ "ሰዎች ዴሞክራሲ እንዲመሠረት መታገል አለባቸው" በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።