በጋምቤላ ክልል ሦስት የ12ተኛ ክፍል ተፈታኞችን ጨምሮ አራት ሴቶች በሙርሌ ታጣቂዎች መታገታቸው ተገለጸ

የ12ተኛ ክፍል ሴት ተፈታኞች ፈተና ላይ

የፎቶው ባለመብት, Gambella University

የምስሉ መግለጫ, የ12ተኛ ክፍል ሴት ተፈታኞች ፈተና ላይ (ፎቶ፡ ያለፈው ዓመት ተፈታኞች)

በጋምቤላ ክልል፤ በመጪው ሰኞ የሚጀምረውን የ12ተኛ ክፍል ፈተና ለመውሰድ በጉዞ ላይ የነበሩ ሦስት ሴት ተማሪዎች እና አንዲት የ13 ዓመት ልጅ በሙርሌ ታጣቂዎች መታገታቸውን ሁለት የጎግ ወረዳ የመንግሥት ኃላፊዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከ13 እስከ 22 ዕድሜ ያላቸው አራቱ ሴቶች በታጣቂዎች የታገቱት ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ሰኔ 18/2017 ዓ.ም. ከቀኑ አራት ሰዓት ገደማ እንደሆነ ባለሥልጣናቱ ገልጸዋል።

አራቱ ሴቶች የታገቱት በአኝዋ ዞን ጎግ ወረዳ ከምትገኘው ቴዶ ቀበሌ ተነስተው ወደ ወረዳው ዋና ከተማ ፒኝውዶ በእግር እየተጓዙ በነበረበት ሰዓት እንደሆነ የወረዳው የካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አጃክ ኦኮንጎ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከአራቱ ሴቶች መካከል ሦስቱ የ12ተኛ ክፍል ተፈታኞች እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ አጃክ፤ ወደ ፒኝውዶ ከተማ እየተጓዙ የነበረው፤ ነገ ቅዳሜ ከሌሎች ተፈታኞች ጋር በመሆን ፈተናው ወደ ሚሰጥበት ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ለመሄድ ነበር።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠው የ12ተኛ ክፍል ፈተና የሚጀምረው በመጪው ሰኔ 23/2017 ዓ.ም. ነው።

አራተኛዋ ታጋች የ13 ዓመት ታዳጊ መሆኗን የሚናገሩት ኃላፊው፤ ሌሎቹ ታጋቾች ዕድሜያቸው 18፣ 20 እና 22 እንደሆነ አስረድተዋል። የ20 እና 22 ዕድሜ ያላቸው ተፈታኞች የልጆች እናት መሆናቸውንም አክለዋል።

የካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊው እንደሚገልጹት ጉዞው ሲደረግ የነበረው ከሌሎች ስድስት ወንዶች ጋር ነበር። "ሲጓዙ የነበሩት አስር ናቸው። ሴቶቹ ፍጥነት ስላልነበራቸው ወደ ኋላ ቀርተው አራት ሆኑ" የሚሉት አቶ አጃክ፤ አራቱ ሴቶች አለመኖራቸው የታወቀው ወንዶቹ ወደ ከተማው ከደረሱ በኋላ መሆኑን አስረድተዋል።

ሌሎቹ ተጓዦች ለፍለጋ ተመልሰው ከሄዱ በኋላ አራቱ ሴቶች እንደታገቱ መታወቁን ተናግረዋል። የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንም ዛሬ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ "በእግር በመጓዝ ላይ የነበሩ አራት ታዳጊ ልጆች" መታገታቸውን ሪፖርት እንደተደረገለት አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እገታው የተፈጸመው "በደቡብ ሱዳን ሙርሌ ዘራፊዎች" እንደሆነ የፖሊስ ኮሚሽኑ መረጃ ይገልጻል። የወረዳው የካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አጃክ እና የወረዳው ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጊዲሞ ኡቲኪም በተመሳሳይ ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ታጣቂዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።

የካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊው እንደሚገልጹት በወረዳው በሙርሌ ታጣቂዎች ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው አይደለም። "በዓመት ከአራት አምስት ጊዜ በላይ እንደዚህ ዓይነት ድርጊት ይፈጸማል" የሚሉት ኃላፊው፤ ከአንድ ወር ገደማ በፊት የዝርፊያ ሙከራ መፈጸሙን አስታውሰዋል።

የወረዳው አስተዳደር የፀጥታ ኃይሎችን በማሰማራት ከቀበሌው የሚነሱ ሌሎች ተማሪዎችን በእጀባ እንዳጓጓዘ አክለዋል።

ረቡዕ ዕለት የታገቱት አራት ሴቶችን ለማስመለስ የፀጥታ ኃይሎች ቢሰማሩም እስካሁን ድረስ ያሉበት እንዳልታወቀ አቶ አጃክ ገልጸዋል። "አስር የሚሆኑ ታጣቂዎችን ወደ አካባቢው አሰማርተናል። ታጣቂዎቹ የተመለሱት ትናንት [ሐሙስ] ሌሊት ነው። እነሱም አልተገኙም" ብለዋል።

ታጣቂዎቹ፤ በዚህ ፍጥነት ወደ ደቡብ ሱዳን መመለስ አይችሉም የሚል ግምት ያላቸው ኃላፊው፤ አሁንም ድንበር ውስጥ ይሆናሉ የሚል እምነታቸውን ገልጸዋል። የጎግ ወረዳ አስተዳደር የአራቱን ሴቶች እገታ ለክልሉ መንግሥት ሪፖርት መድረጉን ተናግረዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ባወጣው መግለጫ "የወረዳው ፖሊስ እና የፀጥታ አካላት ታግተው የተወሰዱትን ልጆች ለማስመለስ ወደ ሥፍራው እንደሄዱ እስከአሁን ድረስ ያልተመለሱና ክትትል ላይ መሆናቸው ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል" ብሏል።

ቢቢሲ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ከደቡብ ሱዳን ተሻግረው የሚመጡት የሙርሌ ታጣቂዎች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እገታ፣ ዝርፊያ እና ግድያ ሲፈጽሙ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ባለፈው ግንቦት 17/2017 ዓ.ም. የሙርሌ ታጣቂዎች 39 ሰዎችን አሳፍሮ ይጓዝ በነበረ አውቶብስ ላይ በከፈቱት ተኩስ ሹፌሩን ጨምሮ አምስት ሰዎች ሲገደሉ ሰባት ሰዎች ቆስለዋል።