ዓለምን ያስደነገጠው የቻይናው ዲፕሲክ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ለውጦታል?

የፎቶው ባለመብት, Shutterstock
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ገና እግራቸው ከመግባቱ ነበር ዲፕሲክ የተባለው አዲሱ የቻይና ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) መተግበሪያ የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል የሆነውን ሲሊከን ቫሊን ያናወጠው።
በአንድ ምሽት ዲፕሲክ-አር1 (DeepSeek-R1) በአሜሪካ የአፕል ተጠቃሚዎች ዘንድ በብዛት በነጻ የተጫነ መተግበሪያ ሆነ።
ኩባንያው በወቅቱ አዲሱ ቻትቦት ቻትጂፒትን ተቀናቅኗል ብሏል።
ከዚህም ባሻገር መተግበሪያውን ለመሥራት የወጣው ወጪ እጅጉን አነስተኛ መሆኑም ተገልጿል።
እነዚህ መረጃዎች እና መተግበሪያው ያገኘው ድንገተኛ ተወዳጅነት ከቺፕ አምራቹ ግዙፉ ኒቪዳ 600 ቢሊዮን ዶላር ወይም 17 በመቶ የገበያ ድርሻን ወስዷል።
ይህም በአሜሪካ የአክሲዮን ገበያ ታሪክ ውስጥ በአንድ አክሲዮን ላይ በአንድ ቀን የደረሰ ከፍተኛው ኪሳራ ሆኖ ተመዝግቧል።
ሌሎች በርካታ የሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚጠቀሙ የቴክኖሎጂ አክሲዮኖችም በዚህ የገበያ ሽሚያ ክፉኛ ተጎድተዋል።
ዲፕሲክ በአሜሪካ የሰው ሠራሽ አስተውሎት የበላይነት ላይ ጥርጣሬን አጭሯል።
እስከዚያን ጊዜ ድረስ ቻይና ከአሜሪካ ኋላ እየተከተለች ነበር። አሁን ቻይና በግንባር ቀደምነት እየመራች ይመስላል።
ማርክ አንድሬሰን የዲፕሲክ-አር1 መምጣትን "የሰው ሠራሽ አስተውሎት ስፑትኒክ ቅጽበት" ሲል ገልጾት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት ከአሜሪካ እና በሶቮየት ኅብረት መካከል የነበረውን የሕዋ ምርምር እሽቅድምድም በማስታወስ ከሶቪየት የሳተላይት መንኮራኩር ጋር አወዳድሮታል።
በዝምታ ውስጥ የሚሰራው ዲፕሲክ
ዲፕሲክ ዓለምን ካስደመመ ስድስት ወር ሞልቶታል።
ዛሬ የቻይና ግኝት የሆነው ይህ መተግበሪያ ከዋና ዋና የዓለም ዜናዎች ውጪ ሆኗል።
በሳን ፍራንሲስኮ ውስጥም ቢሆን አሁን ሻይ ቡና እየተባለ ወይንም ቢራ እየተጠጣ የሚወራበት ርዕስ ጉዳይ አይደለም። ነገር ግን ዲፕሲክ አልጠፋም።
ዲፕሲክ የቻትጂፒቲ ፈጣሪ በሆነው የኦፕንኤአይ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳም አልትማን እና ሌሎች የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ስለ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚያስቀምጡትን አንዳንድ ቁልፍ ግምቶችን ተገዳድሯል።
የኤአይ ቺፕ ዲ-ማትሪክስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሲድ ሼት "ትልቅ የተሻለ ነው ተብሎ የሚታሰብበት መንገድ ላይ ነበርን" ይላል።
ምናልባት በርካታ የዳታ ማዕከላት፣ ሰርቨሮች፣ ቺፕስ እና ኤሌክትሪክ መጠቀም ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት አዋጭ መንገድ አልነበረም።
ምንም እንኳን ዲፕሲክ በወቅቱ አለ የተባለውን ቴክኖሎጅ ማግኘት ባይችልም ሼት ለቢቢሲ እንደተናገረው "በምርጥ ምህንድስና፣ ብቃት ያለው ሞዴል መገንባት ይቻላል።"
በጥር ወር በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ዲፕሲክ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ሲጨምር፣ የኮርፖሬት አይቲዎች የሠራተኞቹን ፍልሰት ለማስቆም እርምጃ ወስደዋል።
ኩባንያዎች ሠራተኞቻቸው ዲፕሲክን እየተጠቀሙ መሆኑን ሲደርሱበት እና ለማስቆም ሲሯሯጡ ቻይና፣ ዲፕሲክ መቀመጫውን ያደረገባት አገር፣ የተጠቃሚዎችን ዳታ አግኝታ ይሆን የሚለው ስጋት ቦታውን ያዘ።
ነገር ግን ትክክለኛ ቁጥሮች ባይገኙም፣ ብዙ አሜሪካውያን ዛሬም ዲፕሲክን ይጠቀማሉ።
አንዳንድ የሲሊኮን ቫሊ ጀማሪ ሙያተኞች ወጪዎችን ለመቀነስ በጣም ውድ ከሆኑ የአሜሪካ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ኩባንያዎች ምርት ይልቅ ዲፕሲክን መጠቀም መርጠዋል።
አንድ ባለሀብት የገንዘብ አቅማቸው አነስተኛ የሆኑ ኩባንያዎች፣ ዲፕሲክን በመጠቀም የሚቆጥቡት ገንዘብ ተጨማሪ ሠራተኛን መቅጠር የመሰሉ ጠቃሚ ነገሮች ላይ እያዋሉት ነው ይላል።
ይሁን አንጂ ጥንቃቄ ማድረጋቸውን አልረሱም።
በኦንላየን በሚካሄዱ የውይይት መድረኮች ላይ ተጠቃሚዎች ዲፕሲክ-አር1 በቻይና የሚገኘውን የዲፕሲክ ሰርቨር ከመጠቀም ይልቅ በራሳቸው የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎቻቸው ላይ እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ ያሳያሉ። ይህም የግለሰቦች ዳታ እንዳይሰረቅ ይረዳል ተብሎ ይታመናል።
ሚል ፖንድ ሪሰርች ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክሪስቶፈር ኬን እንዳሉት "ሞዴሉን ቻይና ሰርጋ ትገባለች ብለው ሳይጨነቁ ለመጠቀም ጥሩ መንገድ ነው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ እና የቻይና ፉክክር
አንዳንድ ባለሙያዎች የዲፕሲክ መምጣት በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ባለው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፉክክር ላይ ለውጥ ያመጣል ይላሉ።
"እስካሁን በትላልቅ የቋንቋ ሞዴሎች ላይ ለመድረስ ጥረት እንደምታደርግ ቆይታለች። የእነርሱ ሞዴል ጥሩ ቢሆንም አሁንም ከምዕራባውያኑ አንጻር የሚቀረው ነገር አለው" ሲሉ የማርኬተር ኢኒስቲትዩት ፎር ቻይና የፖሊሲ ተንታኝ ዌንዲ ቻንግ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ትልቅ የቋንቋ ሞዴል (LLM) በአንድ ዓረፍተ ነገር ወይም ሐረግ ውስጥ ቀጣዩን ቃል ለመተንበይ የሠለጠነ የማመዛዘን ሥርዓት ነው።
ዲፕሲክ ከአሜሪካ ከተመሳሳይ ሞዴሎች እጅግ ያነሰ የኮምፒውተር ኃይል እና ገንዘብ በመጠቀም ከፍተኛ አፈጻጸም ያለው ሞዴል ገንብቻለሁ ሲል የነበረውን ግምት ቀይሯል።
ኦፕንኤአይ በ2024 ብቻ 5 ቢሊዮን ዶላር አውጥቷል።
በንጽጽር የዲፕሲክ ተመራማሪዎች እንዳሉት ዲፕሲክ-አር1፣ የኦፕንኤአይ o1ሞዴል በበርካታ ሙከራዎች የበለጠውን፣ በ5.6 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ሠርተዋል።
"ዲፕሲክ የቻይናን ሰው ሠራሽ አስተውሎት መልክዓ ምድር ተወዳዳሪነት ለዓለም አሳይቷል" ሲል ቻንግ ተናግሯል።
የአሜሪካ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሠሪዎች ይህንን አሻሽለው ለማዘጋጀት ደፋ ቀና እያሉ ነው።
በትራምፕ አስተዳደር እና በዋና ዋና የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከኤአይ ጋር የተገናኙ ስምምነቶች እና ሌሎች የሚሰጡ መግለጫዎች ከቻይና ቀድመው ለመቆየት ወሳኝ ሆነው ተስለዋል።
የትራምፕ የሰው ሰራሽ አስተውሎቱ ቄሳር ዴቪድ ሳክስ አስተዳደሩ ባለፈው ወር የኤአይ የድርጊት መርሃ ግብሩን ይፋ ባደረገበት ወቅት ቴክኖሎጂው "ለኢኮኖሚውም ሆነ ለአገር ደኅንነት ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል" ብለዋል።
ሳክስ "አሜሪካ በኤአይ የበላይ ሆና መቀጠሏ በጣም አስፈላጊ ነው" ብለዋል።
መቀመጫው በቻይና የሆነው ዲፕሲክ በደኅንነት ዙሪያ የሚቀርብበትን ስጋት ለመቀልበስ አልቻለም።
ሮይተርስ በሰኔ ወር ለመጀመሪያ ጊዜ እንደዘገበው የአሜሪካ መንግሥት ኩባንያው ከቻይና ጋር ያለውን ግንኙነት ሲገመግም ቆይቷል።
አንድ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ዲፕሲክ በፈቃደኝነት፣ ለቻይና ወታደራዊ እና የስለላ ሥራዎች ድጋፍ መስጠቱን ይቀጥላል" ብለዋል።
ዲፕሲክ ለቢቢሲ አስተያየት ምላሽ አልሰጠም፤ ነገር ግን የኩባንያው የግላዊ መረጃ ጥበቃ ፖሊሲ ሰርቨሮች በቻይና ውስጥ ይገኛሉ ይላል።
"አገልግሎቶቻችንን ሲጠቀሙ የእርስዎ ግላዊ ዳታ በቻይና ባሉ ሰርቨሮች ውስጥ ሊቀመጥ እና ሊታይ ይችላል" ይላል ፖሊሲው ።
"ይህ ለእኛ የግል ዳታ ቀጥተኛ አቅርቦት ወይም እኛ ወይም ሦስተኛ አካል ለሚያደርገው ማስተላለፍ ሊያገለግል ይችላል።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አዲስ አቀራረብ?
ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ኦፕንኤአይ ጥንድ የኤአይ ሞዴሎችን ይፋ ካደረገ በኋላ ስለዲፕሲክ መወራት ጀምሯል።
እነዚህ በአሜሪካው ግዙፍ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኩባንያ ከአምስት ዓመታት ወዲህ፣ ቻትጂፒቲ በተጠቃሚዎች ከተጥለቀለቀ ወዲህ፣ የመጀመሪያዎቹ ነፃ እና ለሁሉም ክፍት የሆኑ ምርቶች ነበሩ።
ይህም ማለት በነጻ ማውረድ እንዲሁም ማሻሻል ይቻላል።
ዲ ማትሪክስ ሼት "ከዲፕሲክ ኦፕንኤአይ በዚህ ሳምንት እስከለቀቀው መተግበሪያ ድረስ ቀጥታ መስመር ማስመር ትችላላችሁ" ሲል ያለውን ሽግግር ለመጠቆም ይሞክራል።
ሼት "ዲፕሲክ ትናንሽ እና ቀልጣፋ ሞዴሎች አሁንም አስደናቂ አፈፃፀምን ሊሰጡ እንደሚችሉ አረጋግጧል፤ ይህ ደግሞ የኢንዱስትሪውን አስተሳሰብ ለውጧል" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
"አሁን እያየነው ያለነው የዚያ አስተሳሰብ ቀጣዩ ዙር ነው። ወደ ትክክለኛው መጠን ያላቸው ሞዴሎች መጥተናል። ፈጣን፣ ርካሽ ወደ ሆኑ እና በሚፈለገው መጠን ለመጠቀም ዝግጁ ወደሆኑት እየሄድን ነው።"
ነገር ግን በኤኤይ ውስጥ ተዋናይ ለሆኑት አሜሪካውያን ባለሙያዎች፣ የድሮው መንገድ አዋጭ ይመስላል።
ኦፕን ኤአይ ነፃ ሞዴሎቹን ከለቀቀ ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ ጂፒቲ-5ን (GPT-5) አስተዋወቀ።
ኩባንያው የኮምፒዩተር አቅሙን እና የኤአይአይ መሠረተ ልማትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደጉን ገልጿል።
የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ምርጥ የኤአይ ባለሙያዎችን ለመቅጠር ሲፎካከሩ ስለ አዲሱ የኤአይአይ የመረጃ ማዕከል ስብስቦች በስፋት እየተነገረ ነው።
የሜታ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማርክ ዙከርበርግ የኤአይ ምኞቱን ለማሳካት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በማፍሰስ ከተፎካካሪዎቹ ሠራተኞችን በ100 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ለማማለል ሞክሯል።
በቴክኖሎጂው ዘርፍ ስኬታማ የሆኑት ኩባንያዎች በኤኤይ ላይ የሚያፈሱት መዋዕለ ንዋይ እንዲሁም ባለፈው ሩብ ዓመት ያገኙት አማላይ ገቢ፣ አሁን የበለጠ ፉክክራቸው እግር በእግር የመከታተል መሆኑን ያሳያል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዲፕሲክ ከመጣ በኋላ የወደቀው የኒቪዳ አክሲዮኖች ዳግም አንሰራርተዋል።
አዲስ የሽያጭ ጣሪያን በማስመዝገብ በታሪክ በዓለም ከፍተኛ ዋጋ ያለው ኩባንያ ሆኗል።
የሚል ፖንድ ሪሰርች ባልደረባው ኬይን "የመጀመሪያው ታሪክ ትንሽ አሳሳች እንደነበር አረጋግጧል። አሁን ወደ ፊተኛው ተመልሰናል። ያም ማለት የሰው ሠራሽ አስተውሎት የበለጠ በዳታ ማዕከላት፣ በቺፕሶች እና በኤሌትሪክ ኃይል ላይ የበለጠ ወደሚተማመንበት" ብሏል።
በሌላ አነጋገር ዲፕሲክ የቴክኖሎጂውን ዘርፍ እንዳሸበረ ፀንቶ መቆየት አልቻለም።
እና ዲፕሲክ ራሱስ ቢሆን?
በሲድኒ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ማሪና ዣንግ "ዲፕሲክ አሁን የጀመረበትን ፍጥነት የማስቀጠል ተግዳሮቶች አጋጥመውታል" ብለዋል።
ይህ የሆነበት ምክንያት ከበፊቱ ከሥራ ክንዋኔዎች ጋር የተያያዘ ነው። ነገር ግን በአሜሪካ እና በቻይና ካሉ ኩባንያዎች ከፍተኛ ፉክክር በመኖሩ ጭምር መሆኑን ፕሮፌሰሯ ተናግረዋል።
ዣንግ የኩባንያው ቀጣይ ምርት ዲፕሲክ-አር2 (DeepSeek-R2) መዘግየቱ ተገልጿል ይላሉ።
ይህም የሆነበት ብቸኛ ምክንያት ከፍተኛ ደረጃ ያለው የቺፕስ እጥረት በማጋጠሙ ነው።















