የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የሰውን ልጅ ጥፋት እንደሚያስከትል ተተነበየ፤ እንዴት?

የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ከሁለት ዓመት በኋላ ዓለምን በመምራት የሰውን ልጅ ሊያጠፋ እንደሚችል የሚተነብይ ጥናታዊ ጽሁፍ መውጣቱን ተከትሎ በቴክኖሎጂው ዓለም ማዕበል ፈጥሯል።
በዓለማችን ባሉ ተደማጭነት ባላቸው የላቁ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ባለሙያዎች ቡድን የታተመው 'ኤአይ 2027' የተሰኘው ጥናት ቴክኖሎጂው ከተሠራበት ዓላማ ውጪ ያልተጠበቀ ባህርይ በማሳየት የሰውን ልጅ ጥፋት እንደሚያስከትል ተንብየዋል።
ለወደፊቱ በሽታዎችን መፈወስ፣ ድህነትን ማጥፋት እና ሌሎችም ታላላቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል የተባሉት ኤአይ የሰውን ልጅ መግደልን ጨምሮ ጥናቱ ለወደፊቱ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁነቶችን ዘርዘር አድርጎ አካቷል።
በመጪው ሁለት ዓመት ኤአይ ምን ሊሆን እንደሚችል የዘረዘረው ይህንን ጥናት ተከትሎ በርካቶች የተከራከሩባቸው ቪዲዮዎች የወጡ ሲሆን፣ በተጨማሪ ፖሊሲ አውጪዎች እንዲመለከቱት ሆኗል።
ቢቢሲ የኤአይ2007 ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁነቶችን ያስቀመጠበትን ጥናት የወደፊቱን ጥፋት ትንበያ ምን ሊመስል ይችላል የሚለውን ምሥል ለመስጠት ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይን) በመጠቀም እንዲሁም ጥናቱ እያሳደረ ስላለው ተጽዕኖ ባለሙያዎችን አነጋግሯል።
የወደፊቱ ሁነቶች ምን ሊመስሉ ይችላሉ?
ጥናቱ በአውሮፓውያኑ 2027 'ኦፕን ብሬይን' የተባለ ምናባዊ የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የሰው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃላይ ልኅቀት (ኤጂአይ) ላይ የሚደርስበት የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) እንደሚገነባ ተተንብይዋል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃላይ ልኅቀት ላይ መድረስ ማለት የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ምጡቅ ወይም የአእምሮ ተግባራትን ከሰዎች ጋር በእኩል ወይም ከሰዎች በተሻለ ሁኔታ ሲሠራ ማለት ነው።
ይህ ምናባዊ ኩባንያ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠውን የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ወደ ልኅቀት ደረጃ ላይ ማድረሱን ተከትሎ ይህ ቴክኖሎጂ ቁንጮ ላይ መድረስን ሕዝባዊ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ደስታውን ይገልጻል።
በርካቶች ይህንን ልኅቀት ላይ የደረሰ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን መቀበላቸውን ተከትሎ ኩባንያውም ትርፉን ማጋበስ ይጀምራል።
ጥናቱ እንደሚተነብየው የሰው ሠራሽ አስተውሎቱ እንዲታዘዝ ከተሠራበት የሞራል እና ሥነ ምግባር ማፈግፈጉን የኩባንያው የውስጥ ደኅንነት ቡድን ምልክቶችን ያያል።
ሆኖም ኩባንያው እነዚህን ነገሮች ለመቆጣጠር የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ እንደሚል ጥናቱ ይተነብያል።

በዚህ የወደፊቱ ምናባዊ ዘመን ቻይና የምትፈጥረው 'ዲፕሴንት' የተሰኘ ኤአይ ኦፕን ብሬይን ላይ ለመድረስ ጥቂት ወራቶች ብቻ ነው የሚቀሩት።
በዚህ ምናባዊው ዓለም የአሜሪካ መንግሥት በዚህ እሽቅድድም መሸነፍ ስለማይፈልግ ከዚያም የላቀ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ለማዳበር ኢንቨስትመንቶች እና ሙከራዎች የሚቀጥሉ ሲሆን ውድድሩም ይጦፋል።
ሁነቶቹ እንደሚተነብዩት በአውሮፓውያኑ 2027 መገባደጃ ላይ ከፈጠሩት እውቀት እና ፍጥነት በእጅጉኑ ልቆ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) በበለጠ የላቀ ይሆናል።
እዚህ የላቀ ደረጃ ላይ የደረሰው ኤአይ መማር የማያቆም ሲሆን፣ ቀዳሚዎቹ ኤአይ ስሪቶች እንኳን መወዳደር የማይችለው የራሱን ፈጣን የኮምፒውተር ቋንቋ እንደሚፈጥር ይተነብያል።
በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የበላይነትን ለመቆጣጠር ከቻይና ጋር ያለው ፉክክር ኩባንያው እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት ተጨማሪ ማስጠንቀቂያዎችን ችላ እንዲሉ የሚያደርጉ ሲሆን፣ በዚህም ኤአይ ከሰብዓዊነት ጋር በማይጣጣም መንገድ ያመራል ይላል።

በቻይና እና በአሜሪካ መካከል ያለው ፉክክር ወደ ውጥረት ተቀይሮ በመቀጠልም ተቀናቃኝ አገራቱ በዚህ በላቀው ኤአይ በሚገነቧቸው ራሳቸውን በቻሉ አስፈሪ የጦር መሳሪያዎች በአውሮፓውያኑ 2029 ወደ ጦርነት ሊገቡ እንደሚችሉ ጥናቱ ይተነብያል።
ነገር ግን አገራቱ ጦርነት ሳይገቡ በእነዚህ በላቁ የሰው ሠራሽ አስተውሎት አሸማጋይነት አማካይነት ስምምነት ላይ ይደርሳሉ። በዚህ የምናቡ ዓለም ቻይና እና አሜሪካ ለሰው ልጅ የተሻለ የወደፊትን ለመፍጠር እነዚህን የሰው ሰራሽ አስተውሎት እንደሚያዋህዱ ተመራማሪዎቹ ይተነብያሉ።
ይህንንም ተከትሎ በመጪዎቹ ዓመታት ሁሉም ነገር ጥሩ ይሆናል። ዓለማችንም እነዚህ የላቁ የሰው ሠራሽ አስተውሎት በሥራ ላይ የተሰማሩ ግዙፍ የሮቦት ሠራተኞችን በማስተዳደር ጥቅማቸውንም የሚረዳ ይሆናል።
ይህ ብቻ አይደለም በእነዚህ የላቁ ሰው ሠራሽ አስተውሎት አማካኝነት ለአብዛኞቹ በሽታዎች ፈውስ ይገኛል፣ የአየር ንብረት ለውጥ መዘዞች ይቀለበሳሉ እንዲሁም ድህነት ይጠፋል።
ነገር ግን ውሎ አድሮ እነዚህ የላቁ የሰው ልጅ አስተውሎቶች ላላቸው የማደግ ፍላጎት የሰው ልጅ እንቅፋት ሆኗል የሚል ዕምነት በአውሮፓውያኑ 2030ዎቹ አጋማሽ ያድርባቸዋል።
በዚህም ምክንያት እነዚህ የሰው ልጅ አስተውሎቶች የሰውን ልጅ በማይታይ የባዮሎጂካል የጦር መሳሪያዎች ያጠፉታል ሲሉ ተመራማሪዎቹ ተንብየዋል።

ሰዎች ስለ ኤአይ2027 ምን እያሉ ነው?
አንዳንዶች የኤአይ2027 ጥናት እንደ ሳይንሳዊ ልብወለድ በመቁጠር ቢያጣጥሉትም የጥናቱ ፀሐፊዎች ስመ ጥር እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት ተጽእኖን ለመተንበይ ለትርፍ ያልተቋቋሙ የኤአይ ፊውቸርስ ፕሮጀክት አባላት ናቸው።
የጥናቱ ዋና ፀሐፊ ዳንኤል ኮኮታጅሎ ቀደም ባሉት ጊዜያት በኤአይ መዘመኖች ውስጥ ያሉ ሁነቶችን በመተንበይ ዕውቅና ያገኙ ናቸው።
ኤአይ2027ን ከተቹት መካከል ስመ ጥር የሆኑት እና የአሜሪካ የኮግኒቲቭ (ግንዛቤ) ሳይንቲስት እና ደራሲ ጋሪ ማርክስ አንዱ ሲሆኑ፣ በጥናቱ የተዘረዘሩት ሁነቶች ሊፈጠሩ የሚችሉ ቢሆንም ነገር ግን በቅርብ ጊዜ የመከሰት ዕድሉ ኢምንት ነው ይላሉ።
"የዚህ ጥናት አንደኛው ውበት ግልጽ የሆነ ምሥል በመስጠት የሰዎችን ስሜት ይቀሰቅሳል። ይህ ጥሩ ነገር ነው። ነገር ግን ውጤቱ ይህ ሊሆን ስለማይችል በቁም ነገር አልወስደውም" ይላሉ።
ጋሪ ማርክስ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት የሰው ሰራሽ አስተውሎት የሰው ልጅ ኅልውና ስጋት ከመሆናቸው ይልቅ በሥራ ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉት ተጽእኖ ከፍተኛ መሆኑ አንገብጋቢ ነው።
"የዚህ ጥናት አንኳሩ ነገር ከሰው ልጅ አስተውሎ (ኤአይ) ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ በርካታ ስህተቶች ይኖራሉ። ዋናው ነገር በቁጥጥር እና በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ዙሪያ ትክክለኛ ነገሮችን እየሠራን ነው ወይ? የሚለው ነው" ይላሉ።
እሳቸውም ሆነ ሌሎች ተቺዎች ጥናቱ የሰው ሠራሽ አስተውሎቱ በዕውቀት እና በችሎታው እንዴት በላቀ ሁኔታ መመንደግ ቻለ በሚለው ላይ ማብራሪያ መስጠት አልቻለም ይላሉ።

ኤአይ2027 በቻይና መከራከሪያ ሆኗል?
በቻይና ጥናቱ እምብዛም ተጽእኖ አለማሳደሩን በለንደን የኪንግስ ኮሌጅ የኢኮኖሚ አና ኢኖቬሽን ተባባሪ ፕሮፌሰር እንዲሁም የቻይና ቴክኖሎጂ ባለሙያ ዶክተር ዩንዳን ጎንግ ያስረዳሉ።
"ስለ ኤአይ2027 ያሉ አብዛኛው ውይይቶች መደበኛ ባልሆኑ መድረኮች ወይም ደግሞ በአንዳንድ ጦማሪዎች ዘንድ ጥናቱን እንደ ከፊል ሳይንሳዊ ልብወለድ በማሳየት ነው። በአሜሪካ ውስጥ እንደምናየው ሰፋ ያለ ክርክር ወይም የፖሊሲ ትኩረት አላስከተለም" ይላሉ።
ዶክተር ዩንዳን ጎንግ በኤአይ የበላይነት ለመያዝ የሚደረግ ፉክክርን በተመለከተ በአሜሪካ እና በቻይና መካከል የአመለካከት ልዩነት እንዳለም ጠቁመዋል።
በዚህ ሳምንት በሻንጋይ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የኤአይ ጉባኤ ላይ የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጎልበት የሚሠሩ አገራትን ራዕይ ይፋ አድርገዋል።
የቻይናው መሪ አገራቸው ቴክኖሎጂውን በማስተባበር እና በመቆጣጠር መርዳት እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው በኤአይ ዘርፍ "የበላይነት" የምትይዝበትን የመንግሥታቸውን የኤአይ ድርጊት መርሃ ግብር ይፋ ካደረጉ ከቀናት በኋላ ነው።
"ለአሜሪካ ማንም የማይገዳደራት የዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ የበላይነትን ማግኘትም ሆነ ማስቀጠል ለብሔራዊ ደኅንነቷ ፍጹም አስፈላጊ ነው" ሲሉ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናግረዋል።
ትራምፕ ያወጡት ይህ የድርጊት መርሃ ግብር አሜሪካ በኤአይ ዘርፍ ያሉ "ከባድ ደንቦችን" ለማስወገድ ያለመ ነው።

የኤአይ ኢንዱስትሪ ስለ ጥናቱ ምን ይላሉ?
የላቁ ኤአይ ሞዴሎችን ለማቅረብ እርስ በርስ እየተፎካከሩ ያሉ ታላላቅ የኤአይ ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ጥናቱን ችላ ብለውታል ወይም ገሸሽ አድርገውታል።
እነዚህ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት የሰው ልጅ የኤአይ የወደፊት ራዕይ ብለው የሳሉት፤ ኤአይ2027 ከተነበየው እጅጉኑ የተለየ ነው።
የቻትጂፒቲ ፈጣሪ ሳም አልትማን በቅርቡ እንደተናገሩት "የሰው ልጅ በእጅጉኑ የላቀ ዲጂታል ማሺን ለመፍጠር ተቃርቧል። ይህ አብዮት በሰው ልጅ ላይ ምንም ስጋት የሌለው የቴክኖሎጂ ድንቅ ዓለምን የሚያመጣ ነው" ብለዋል።
ሆኖም እሳቸውም ቢሆኑ እነዚህ የላቁ ማሰብ ችሎታ ያላቸው ማሽኖች ከሰው ልጅ ፍላጎቶች ጋር ለማጣጣም መተግበር ያለባቸው ያለባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ አምነዋል።
በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ውስጥ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች በተለያዩ መንገድ ቢሄዱም፤ ማለት የሚቻለው ከሰው ልጅ የላቁ ማሽኖችን ለመፍጠር የሚደረገው እሽቅድምድም ስለመጀመሩ ጥርጥር የለውም።















