ኤአይ ያፈቅራል? ያዝናል? የኅልውና ስጋት ነው?

ኤአይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ካረን ሆብስ ታዋቂ ኮሜድያን ናት።

በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ብዙ መድረክ ላይ ቀልድ አቅርባለች። ለቀልድ እንግዳ ባትሆንም ቀልዶች ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ወስዳ ግን አታውቅም።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ቀልዶ ያስቃል ወይ? የሚል ጥናት እየሠሩ ያሉ ባለሙያዎች ናቸው ጥያቄውን ያቀረቡላት።

ቻትጂፒቲ ቀልዶች እንዲጽፍላት አዘዘች። ቀልዶቹን ከማቅረቧ በፊት ሌሎች ኮሜድያኖች የጻፏቸውን ቀልዶች ያቀርባሉ።

ታዳሚዎች በሰዎች እና በኤአይ በተጻፉ ቀልዶች እኩል ይስቁ ይሆን? አጥኚዎቹ በጉጉት ይጠብቃሉ።

በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሳውዝ ካሊፎርንያ የፒኤችዲ ተማሪ ድሪው ጎሬዝ ጥናት የሚሠራው ሰዎች እንዴት በቀልድ እንደሚስቁ ነው።

በሰዎች እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተጻፉ ቀልዶችን ሲያወዳድር በመካከላቸው ልዩነት አግኝቷል።

በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ተባባሪ ፕሮፌሰር አሊሰን ፓዌልም በሰዎች እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተጻፉ ቀልዶችን አነጻጽራለች።

ሰዎች ከመቀለዳቸው በፊት ያቅዳሉ፣ መድረክ ላይ ከወጡ በኋላ ታዳሚያቸውን አይተው ቀልዳቸውን ያሻሽላሉ ወይም አቀራረቡን ሊለውጡ ይችላሉ።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት እነዚህን አያደርግም።

በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሳውዝሀምተን የሚሠራው ፕሮፌሰር ሌስ ካር እንደሚለው፣ "ሰው ሠራሽ አስተውሎት በጊዜ ሂደት መረጃ እያከማቸ እና እየተማረ ሲሄድ ሊሻሻል ቢችልም አሁን ባለው ደረጃ ግን ቀልድ የሚጽፈው “እንደ 5 ዓመት ልጅ ነው።"

ሰዎች ቀልድ ሲነግሩ ታሪክ እየፈጠሩ፣ እያዋዙ፣ ድምጻቸውን እንደየአስፈላጊነቱ ከፍ ዝቅ እያደረጉ፣ ታሪኩን በሰውነት እንቅስቃሴ ጭምር እያጀቡ ነው።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት ይህን ማድረግ ይችል ይሆን?

ካረን ሆብስ በኤአይ የተጻፉ ቀልዶችን ማቅረብ ጀመረች። አንዳች የሚጎረብጥ ነገር ነበረው።

በታዳሚዎቿ ላይ ግራ መጋባትን ስታነብ “ቀልዶቹ በቻትጂፒቲ ነው የተጻፉት” አለች።

ቀልድ ‘ሰዋዊ’ ሊባሉ ከሚችሉ ድርጊቶች አንዱ ነው።

ከቀልድ ባሻገር ሰው ከመሆን ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያላቸው ስሜቶችን መውሰድ እንችላለን። ማፍቀር እና ማዘንን በምሳሌነት እናንሳ።

ዕለት ከዕለት እየተራቀቀ የመጣው ሰው ሠራሽ አስተውሎት እነዚህን ስሜቶች ሊያሳይ ወይም ሊላበስ ይችላል?

ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጠን የማይንድ ፕሌክስ ሥራ አስኪያጅ እና የአይኮግ ላብስ መሥራች ኅሩይ ፀጋዬን ጠይቀናል።

ሰዎች የሚያደርጉትን ሁሉ ኤአይ ይችላል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሰው ልጆች የሚያደርጉትን ሰው ሠራሽ አስተውሎት መቼ መሥራት ይችላል? ብለን ከተነሳን፣ ኅሩይ ሦስት መላ ምቶችን ያስቀምጣል።

የዘርፉ ባለሙያዎች ሰው ሠራሽ አስተውሎት እአአ በ2035 ወይም በ2045 ወይም በ2075 የሰው ልጆች የሚሠሩትን ሊከውን ይችል ይሆናል በሚል የተለያየ አቋም ይዘዋል።

“አሁን ያለው ሰው ሠራሽ አስተውሎት ወደ አርቴፊሻል ሱፐር ኢንተለጀንስ ወይም አርቴፊሻል ጄነራል ኢንተለጀንስ ሲሻገር ነው የሰው ልጆች የሚከውኑትን በአጠቃላይ መሥራት የሚችለው” ይላል ኅሩይ።

ይሄንን ደረጃ የላቀ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ልንለው እንችላለን።

የሰው ልጆችን ‘የተለዩ’ የሚያደርጉ ስሜቶችን ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሊያንፀባርቅ ይችላል? በሚል ከቢቢሲ የተጠየቀው ኅሩይ፣ የሰው ልጆች አስተውሎትን ከማስረዳት ይጀምራል።

ሁለት የሰው ልጆች አስተውሎት ገጽታን እንመልከት። እነዚህ Rational Intelligence (ምክንያታዊ ልኅቀት) እና Emotional Intelligence (ስሜታዊ ልህቀት) ናቸው።

ምክንያታዊ ልህቀት የምንለው ቀድሞ ከነበረን የሕይወት ተሞክሮ ወይም ትምህርት የሚመነጨውን ሲሆን፣ ስሜታዊ ልህቀት ‘ከምክንያት ውጪ’ ስሜት ላይ የተመረኮዘ ነው።

“ሰዎችን ማፍቀር፣ ሰዎች ሲከፋቸው ማወቅ፣ ለሰዎች መስጠት ያለብንን ስሜታዊ ምላሾች መረዳት ‘ኢሞሽናል ኢንተለጀንስ’ ውስጥ ይካተታሉ” ይላል ኅሩይ።

የሰው ልጆች ከምክንያታዊ ልህቀት ጀርባ ስሜታዊ ልህቀት ስላላቸው፣ ሁለቱን አስተናብረው ይኖራሉ።

ሰው ሠራሽ አስተውሎትስ?

ህሩይ እንደሚለው፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ስሜታዊ ልህቀት ይጎድለዋል።

ስሜታዊ ልህቀት ከሌለው ደግሞ እንደ ሰው ማሰብ ፈፅሞ አይችልም ማለት ነው።

“ቀልድን እንውሰድ። ቀልድ ምክንያታዊ ቀመር አለው። ስሜታዊ ጎንም አለው። ሰው ሠራሽ አስተውሎት ምክንያታዊ ቀመሩን ሊያገኘው ይችላል። ቻትጂፒቲ፣ ላማ እና ሌሎችም መተግበሪያዎች ቀልድ መጻፍ ጀምረዋል። ምን ያህል ያስቃል? ስንል ግን ስሜታዊ ጎኑ ስለሚጎድል ፍጹም አልሆነም።”

ኤአይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፍቅር፣ ሐዘን እና ቀልድ

ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሰዋዊ ማንነት (Embodiment) ስለሚጎድለው ስሜታዊ ልህቀትን ማምጣት አይቻልም ብለው የሚከራከሩ ባለሙያዎች ያሉ ሲሆን፣ በተቃራኒው ሰዋዊ ማንነት የግድ አስፈላጊ አይደለም ብለው የሚሞግቱም አሉ።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት “ኮድ ብቻ ከሆነና አካባቢውን የማይረዳ ከሆነ፣ እኛ በስሜት ህዋሳችን አማካይነት የምናገኘው ይጎድለዋል” ሲል ባለሙያው ያስረዳል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት እንደ ሰው መሆን ባይቻለው ማስመሰል አይችልም?

ሰው ሠራሽ አስተውሎት ስሜትን ማስመሰል ከቻለ ማለትም ስለ ፍቅር፣ ስለ ሐዘን ወይም ስለ ቀልድ ተረድቶ፣ ያፈቀሩ ሰዎች እንደሚሆኑት ከሆነ፣ ሐዘን የተሰማቸው ሰዎች የሚያደርጉትን ካደረገ ወይም ቀልዶ ካሳቀ፣ እነዚህን ድርጊቶች ‘እንደ ሰው ከውኗቸዋል’ ማለት ነው የሚል ክርክር አለ።

ሆኖም ግን ይህ ከማስመሰል ያለፈ እንዳልሆነ እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት ምክንያታዊ ልህቀትን ቢማርም እንኳን ስሜታዊ ልህቀት ላይ መድረስ እንደማይችል የሚያስረዱም አሉ።

ኤአይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሰው እና ማሽን ሲወዳደሩ

ሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ ምክንያታዊ ልህቀት እንዲኖረው ማድረግ እንደሚቻል ታይቷል።

መቼ ይደረስበታል? ለሚለው ጥያቄ እአአ 2075 ከሚሉት ወገን እንደሆነ ኅሩይ ይናገራል።

“ምክንያታዊነት በአልጎሪዝም እና በሶፍትዌር እንደሚመጣ ታይቷል። አሁን ባለው ሃርድዌር ግን እዚያ ላይ ለመድረስ ከባድ ነው። ስለዚህ በ2075 እና ከዚያ በኋላ እንደርስበታለን ከሚሉት ወገን ነኝ። ምክንያታዊነትን አሁን ባለው ሃርድዌር ማምጣት ካልተቻለ ደግሞ ስሜትን ለማምጣት አሁን ባለው ሃርድዌር የሚታሰብ አይሆንም።”

የሰው ልጆች መተንፈስ፣ መመገብ እና መራመድን ጨምሮ ሁሉንም እንቅስቃሴዎች እንዲከውኑ ከአእምሮ መልዕክት ተቀብለው የሚያስተላልፉ ሕዋሳትን (Neurons) የሚተካ የሰው ሠራሽ አስተውሎት አቻ አለመኖሩን እንደ መከራከሪያ ያስቀምጣል።

እንደ ኳንተም ኮምፒውቲንግ (Quantum Computing) ያሉ ቴክኖሎጂዎች ፈጣን የማሰላሰል ጉልበት ስለሚያመጡ አሁን ያለው ሁኔታ እንደሚለወጥ የሚከራከሩ ባለሙያዎች አሉ።

አሁን ባለው ሃርድዌር ግን የላቀ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ መድረስ “የሚታሰብ አይሆንም” ይላል ኅሩይ።

ቻትጂፒቲ ይፋ ሲደረግ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሰው ልጆች የህልውና አደጋ ነው፣ ዓለምንም ይቆጣጠራል የሚል ፍርሃት ተስተጋብቷል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት በሰው ልጆች የሚሠለጥነው ምን ድረስ ነው? የሚለው በምዕራባውን አገራት ምክር ቤቶችም ጭምር አከራካሪ ሆኖ ቆይቷል።

በሌላ በኩል በሥነ ምግባር የሚመራ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (Ethical AI) ስጋት አይሆንብንም ብለው የሚከራከሩ ባለሙያዎች ተደምጠዋል።

ኅሩይ በበኩሉ፣ “ኤአይ ሊያጠፋን ነው በሚለውም፣ በሥነ ምግባር ተመርተን እንሠራዋለን በሚለውም ወገን በኩል የማጋጋል ነገር አለ” ይላል።

እርግጥ ነው፤ ሰው ሠራሽ አስተውሎት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ሂደቶችን አልፏል። ይደረጋሉ ተብለው ያልተገመቱ ነገሮችን አድርጎ ታይቷል። ከዚህ በኋላም ዕድገቱ ይቀጥላል።

ታዲያ በቀጣይ ኤአይ እንደ ሰዎች ነፍስ ባይዘራም፣ ቀልብ ባይገዛም፣ በርካታ መረጃ በተመገበ ቁጥር ስሜት ባይሰማው እንኳን ማስመሰል አይችልም?

ኅሩይ፣ ያለ ስሜታዊ ልህቀት ይሄ ሊሆን እንደማይችል በምሳሌ ያስረዳል።

ለምሳሌ፣ አንድ ሰው ስለ ድሃ እና ሃብታም ሲጽፍ ለድሃው ሐዘን ስላለው እና ስቃዩን ስለሚረዳ በአሳማኝ መንገድ ሁኔታውን ከመግለጽ ባሻገር ጨለምተኛ ቀልዶች (Dark Humour) ወይም ሽሙጥ ያካትታል።

ይሄ የተኖረ ሕይወት ላይ ወይም ተሞክሮ ላይ የሚመሠረት ነው።

“ይሄንን ቻትጂፒቲ ወይም ላማ ቢጽፈው ውበት አይኖረውም። ከተሞክሮ የሚነሳ ገለጻ አይኖረውም። ያለ ስሜታዊ ልህቀት አይመጣም” ይላል።

ኤአይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኤአይ ንቃተ ሕሊና አለው?

ጉግል ይሠራ የነበረው መሃንዲስ ብሌክ ለሞይን ከሥራው የተባረረው በድርጅቱ የተሠራው ‘ላንጉጅ ሞዴል’ ነፍስ አለው በማለቱ ነው።

‘Consciousness’ ወይም በግርድፉ ንቃተ ሕሊና በሳይንስ ይህ ነው የሚባል ማብራሪያ ገና አላገኘም።

ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ የሰው ልጆች እንዴት እና ለምን ንቃተ ሕሊና ኖረን? የሚለው ጥያቄ መልስ ሳያገኝ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ንቃተ ሕሊና እንዲኖረው ማስቻል ቀላል አይሆንም።

ንቃተ ሕሊናን ማምጣት ይቻላል ብለው ሙከራ የሚያደርጉ ባለሙያዎች እንዳሉ የሚጠቅሰው ኅሩይ፣ ለምን ይህንን ማድረግ አስፈለገ? የሚለው ላይ ጥያቄ ያነሳል።

በተደጋጋሚ ሙከራዎች ይሄንን ማድረግ እንደሚቻል አምነው የሚመራመሩ አሉ።

“ከኮንሸስነስ ጀርባ ፍሪ ዊል [ነጻ ፈቃድ] አለ። ይሄንን ነጻ ፈቃድ ማራመድን ደግሞ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሊከውነው አይችልም” ይላል።

የሰው ልጆች ‘መለያ’ ከሚባሉት አንዱ ነጻ ፈቃድ ነው። ሰው ሠራሽ አስተውሎት ግን የተቀረፀለትን መንገድ ተከትሎ ይሠራል።

ሰዋዊ ባህሪ ተደርገው ከሚወሰዱት መካከል አንዱ መዋሸት ነው።

ሕጻናት አእምሯቸው እስኪጎለብት ድረስ መዋሸት አይችሉም። ትንሽ ከፍ ሲሉ ደግሞ ብዙም የማያሳምን እና ውሸት እንደሆነ የሚያስታውቅ ውሸት ይዋሻሉ። የሰው ልጅ አእምሮ የማሰላሰል ብቃቱ ከፍ ሲል ደግሞ ውሸት ጠንካራ እና አሳማኝ ይሆናል።

ይህንን ለማድረግ ስሜታዊ ልህቀት ያሻል።

ኅሩይ እንደሚለው፣ ይሄንን ንጽጽር ወደ ሰው ሠራሽ አስተወሎት ስንወስደው የምናገኘው ውጤት ተመሳሳይ አይደለም።

“ሰው ሠራሽ አስተወሎት የላቀ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፍሻል ሱፐር ኢንተለጀንስ) ቢሆንም እንኳን ነጻ ፈቃድ ስለሌለው ከተጻፈለት ሲስተም መውጣት አይችልም” ሲል ያስረዳል።

በእርግጥ የሰው ልጆች ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ለፈለጉት ዓላማ መሣሪያ ሊያደርጉት ይችላሉ። ይህም የህልውና ስጋት ሊያደርገው ይችላል።

“ሰው እስካልተጠቀመበት ድረስ መሣሪያው ስለተፈጠረ ብቻ አይጎዳም። ሰው ሠራሽ አስተውሎት ኮንሸስ አይሆንም። ነጻ ፈቃድ አይኖረውም። ነጻ ፈቃድ ከሌለው ደግሞ ከተጻፈለት ፕሮግራም አይወጣም” ይላል ባለሙያው።

ምናልባት ሰው ሠራሽ አስተውሎት ንቃተ ሕሊና እንዲኖረው ማድረግ ቢቻል፣ ያኔ በሰው ልጆች እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት መካከል ልዩነት አይኖርም ማለት ነው።

ሰው የሚያደርገው፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ግን የማይችለው የሚባል ነገርም ይኖርም።

አሁን ባለው ደረጃ እና ሳይንሱ በሚያስረዳው ልክ ግን፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ስሜታዊ አስተውሎት የሚጠይቁ ክንውኖችን ማድረግ ይችላል ብሎ መደምደም ይከብዳል።