የዓለም ገበያ በተቃወሰበት በአሁኑ ወቅት ገንዘብን በወርቅ ላይ ማዋል የሚያዋጣ አማራጭ ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፉት ጥቂት ወራት ዓለም አቀፍ የወርቅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው። በዚህም ምክንያት የወርቅ ዋጋ ከዚህ ቀደም ከተመዘገበው ከፍተኛውን ጣሪያ ነክቷል።
በዓለም ገበያ ውስጥ ባለው መዋዠቅ ምክንያት ነጋዴዎች አስተማማኝ የኢንቨስትመን አማራጭ እያፈላለጉ ይገኛሉ።
ለወትሮው የምጣኔ ሃብት ምስቅልቅል ሲፈጠር ወርቅ አስተማማኝ እና ቋሚ የሃብት ማከማቻ መንገድ ተደርጎ ይወሰድ ነበር።
በወቅታዊው ሁኔታ ወርቅ የሚታሰበው ያህል አስተማማኝ ነው? የሚል ጥያቄ አጭሯል።
ወርቅ የሚታሰበው ያህል አስተማማኝ ነው?
ዶናልድ ትራምፕ በአገራት ላይ የጣሉት ታሪፍ በዓለም አቀፍ ገበያ ትልቅ የሚባል ለውጥ አምጥቷል። በዓመታት ያልታየ የንግድ ፖሊሲ ለውጥም ተስተውሏል።
ባለፈው ሳምንት ወርቅ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዋጋው ከ3,167 ዶላር በላይ ሆኗል።
በዚህ ዓመት የወርቅ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቀድሞ የያዘውን ክብረ ወሰን እየሰበረ ነው።
ዋነኛ ምክንያቱም ፕሬዝዳንት ትራምፕ የቀሰቀሱት የታሪፍ እና የንግድ ጦርነት ነው። አለመረጋጋት ሲኖር ደግሞ የወርቅ ዋጋ ይጨምራል።
የገበያ መዋዠቅን ተከትሎ ብዙዎች ወርቅ ለማከማቸት ስለሚሞክሩ ዋጋው እየናረ ይሄዳል።
በቤልፋስት ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ዶ/ር ፊሊፕ ፍሌርስ፣ ወርቅ የሚገዙት መንግሥታት፣ ባለሃብቶች ወይም አከፋፋዮች እንደሆኑ ይናገራሉ።
"ብዙዎች የገበያ ድርሻቸውን ትተው ወርቅ ላይ እያተኮሩ ነው። ዋጋው የሚጨምረው በዚህ ምክንያት ነው" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ማንኛውም ዓይነት ማሽቆልቆል ሲታይ እንደ አማራጭ የሚወሰደው ወርቅ ይሆናል።
በተቃራኒው ዓለም አቀፍ የገበያ መዋዠቅ የወርቅ ዋጋ እንዲረክስም ሊያደርግ ይችላል።
በአውሮፓውያኑ 2020 የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው የምጣኔ ሃብት መዳከም የተነሳ ወርቅ ዋጋው አሽቆልቁሎ ነበር።
በዚህም የተነሳ "ወርቅ ሁነኛ የኢንቨስትመንት አማራጭ ነው ማለት ሁሌም አስተማማኝ ነው ማለት ግን አይደለም" ይላሉ ዶ/ር ፊሊፕ።
ወርቅ የሚገዛው ማን ነው?
ወርቅ አስተማማኝ ነው የሚባልበት ምክንያት ከታሪክም ጋር ይተሳሰራል። በተለያዩ ባህሎች ወርቅ ዘመን የማይሽረው በምንም እንደማይተካ ሃብት ይቆጠራል።
በጥንታዊ ግብፅ የንጉሥ ቱታንክሀሙን የፊት ጭምብል የተሠራው ከወርቅ ነው። በጋና የአሻንቲ ሥልጣኔ ውስጥም ወርቅ ጉልህ ቦታ አለው። በሕንድ ፓድማናባስዋሚ ቤተ መቅደስ የሚገኙ መንበሮች ከወርቅ ነው የተሠሩት።
በርካቶች ሃብታቸውን በወርቅ ለማከማቸት የሚመርጡትም ያለ ምክንያት አይደለም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከወርቅ የተሠሩ ጌጣጌጦች እና መገልገያዎች በዓለም አቀፍ ገበያ ምክንያት ዋጋቸው ላይለዋወጥ ይችላል።
ከፍተኛ መጠን ያለው ኢንቨስትመንት ግን በገበያው ተጽዕኖ ሥር ይወድቃል።
ዶ/ር ፊሊፕ እንደሚሉት፣ በቅርብ ጊዜ የወርቅ ዋጋ የጨመረው የአገራት ብሔራዊ ባንኮች ወርቅ እየገዙ ስለሆነ ነው።
አጠራጣሪ እና ያልተረጋጋ በሆነ ገበያ ውስጥ በድርሻ ኢንቨስትመንት ላይ ከመተማመን ይልቅ ክምችታቸው ጠንካራ እንዲሆን ወርቅ ይገዛሉ።
"ይሄ አካሄድ ሁሉም አስተማማኝ ነው ማለት ግን አይደለም። ገበያው ሲረጋጋ፣ መንግሥታትም ይሁኑ ሕዝቡ ወርቅን እንደ አማራጭ መውሰድን ይተዉታል" ሲሉ ዶ/ር ፊሊፕ ያስረዳሉ።
ሰዎች በወርቅ ኢንቨስት ሲያደርጉ ዘለቄታዊ ጥቅሙን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ባለሙያው ያክላሉ።












