"ከመሬት አግኝቼ ለባለቤቱ የመለስኩት 430 ሺህ ዶላር ፍቅርም ጥላቻም አድርሶብኛል"

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኛ የሆኑት አቶ አማረ ታደሰ፣ በተለያየ ጊዜ በጥሬ ገንዘብ እና በቼክ በአጠቃላይ 436 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በሚሠሩበት ስፍራ ተረስቶ በማግኘት ለባለቤቱ መመለሳቸውን ይናገራሉ።

ይኹን እንጂ በዚሁ በጎ ሥራቸውን የወደዷቸው እና ድርጊቱን ያደነቁላቸው የመኖራቸውን ያህል ድርጊቱን እንደ ሞኝነት የቆጠሩም እንዳሉ አቶ አማረ ታደሰ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ተናግረዋል።

“ጓደኞቼም ሆኑ ዘመድ እንዲሁም 95 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ‘አንተ የማትለወጥ ሰው ነህ፤ አያልፍልህም። ለምን ትመልሳለህ?’ ብለውኛል” በማለት ያጋጠማቸውን ይናገራሉ።

'መሠረቴ ያደግኩበት ሁኔታ ነው'

አቶ አማረ ታደሰ የ56 ዓመት ጎልማሳ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት በቦሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ የመንገደኞች ተርሚናል ቢዝነስ ክላስ ላውንጅ ውስጥ ከፍተኛ አስተናጋጅ በመሆን እየሠሩ ናቸው።

አቶ አማረ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በዚሁ መሥርያ ቤት ውስጥ ተቀጥረው በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

“የመጀመርያዎቹ አስር ዓመታት የሠራተኞች ካፍቴሪያ ውስጥ ነው የሠራሁት። የዛሬ 22 ዓመት ደግሞ ላውንጅ ውስጥ መሥራት ጀመርኩ” በማለት ስለሥራቸው ያስረዳሉ።

በዚሁ የሥራቸው ባህሪ ምክንያት ከተለያየ አገራት የሚመጡ መንገደኞች ጋር እንደሚገናኙ እና በርካታ ዕውቀትን ከእነርሱ ማግኘታቸውን የሚናገሩት አቶ አማረ፣ አንዳንድ መንገደኞች የተለያዩ እቃዎችን በመርሳት እንደሚሄዱ ያስታውሳሉ።

“እኛ ብዙ ነገሮችን እናገኛለን። ሞባይል፣ የኪስ ቦርሳ፣ የማይገኝ ነገር የለም። እነዚህን ሁሉ ታድያ ወድቀው የሚገኙ ቁሳቁሶች የሚቀመጡበት ስፍራ ላይ እናስቀምጣለን” በማለት ተረስቶ የሚያገኙትን እቃ እንዴት አንደሚያስተናግዱ ይናገራሉ።

ያገኙትን ወይንም የተረሳ እቃን ለባለቤቱ መመለስ ባህላቸው እንዳደረጉ እና ለዚሁ ደግሞ የአስተዳደግ ሁኔታቸው መሠረት እንደሆናቸው የሚናገሩት አቶ አማረ፣ “በአደግኩበት አካባቢ፣ ከዚያ ሰው ፈቃድ ውጪ የሰውን ገንዘብ መውሰድ ትልቅ ሀጥያት ነው” ይላሉ።

“እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ጥቅምት 6/2010 ከናይጄርያ ወደ ቻይና እየተጓዘ የነበረ ነጋዴ፣ 200 ሺህ ዶላር የያዘ ቦርሳውን ረስቶ ሄደ” በማለት አቶ አማረ ታደሰ እንዲታወቁ ያደረጋቸውን ገጠመኝ ያስታውሳሉ።

“ላውንጁ ውስጥ እየተመላለስኩ ባለሁበት ወቅት ነበር ይህንን ቦርሳ ያገኘሁት። ከፍቼ ስመለከተውም ዶላር ውስጥ እንዳለ ተገነዘብኩ። ለአንድ ሰዓት ከግማሽ ያህል የገንዘቡ ባለቤት ሳይመለስ ሲቀር ለአለቆቼ ሰጥቼ ልወጣ እየተሰናዳሁ ባለሁበት ወቅት የገንዘቡ ባለቤት ተመልሶ መጣ።”

ከዚያም በኋላ የተለያየ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ገንዘቡ የናይጄርያዊው ነጋዴ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ለመንገደኛው ገንዘቡን እንደመለሱ አቶ አማረ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህም ተጓዥ በትልቅ ድንጋጤ ውስጥ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ አማረ፣ “ሰውየው ገንዘቡን የሚያገኝ አልመሰለውም ነበር። ማመንም አቃተው፤ ስለዚህም በጣም በመደነቅ ተሞላ። ‘የኢትዮጵያ ሕዝብ መልካም ሕዝብ ነው፤ ድርጅቱም መልካም ድርጅት ነው’ በማለት አድናቆቱን ገልጾ ነበር” ይላሉ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውሱ።

ለዚሁ ተግባራቸውም የአፍሪካ ድንቃድንቃ መዝገብ ‘አቶ አማረ በሚሠሩበት ቦታ ተጥሎ ያገኙትን 200 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ለመሥሪያ ቤታቸው በመመለሳቸው የአፍሪካ ድንቃ ድንቅ መዝገብ የክብር አባልነት የምስክር ወረቀት ሰጥተናቸዋል’ ሲል ሚያዚያ 23 2015 ዓ.ም የምስክር ወረቀት ሰጥቷቸዋል።

‘ብላክ ቤሪ ስልኩን ሸለመኝ’

አቶ አማረ ስለሌላ ገጠመኛቸው ሲናገሩ ቀኑን በትክክል አያስታውሱም።

ይኹን እንጂ በዚያን ወቀት የሞባይል ስልክ በኢትዮጵያ ውስጥ እምብዛም ያልተስፋፋ እና እንደ ትልቅ ነገር የሚታይበት ወቅት እንደነበር ያስታውሳሉ።

አንድ ቀን በሥራ ቦታቸው ላይ እያሉ 234 ሺህ ዶላር የተጻፈበት ቼክ እና 2000 ዶላር ጥሬ ገንዘብ የያዘ ቦርሳ ማግኘታቸውን ይናገራሉ።

“ሰውየው ወደ አሜሪካ ሊጓዝ ነበር። በሚገባ አይቸው ስለነበር እርሱ ሊሳፈርበት ወደነበረው አውሮፕላን ሮጬ በመሄድ ሰጠሁት። ሰውየውም በጣም ተደንቆ ‘ከሳምንት በኋላ እመለሳለሁ እና ምን ይዤልህ ልምጣ ብሎ ጠየቀኝ።

“እኔም ሞባይል አምጣልኝ አልኩት። በዚያኑ ቅጽበት ከስልኩ ውስጥ ሲሙን በማውጣት የራሱን ብላክ ቤሪ ስልክ ሸልሞኝ ሄደ” ይላሉ።

ገንዘብ የሰው ልጅ ሠርቶ ማግኘት የሚችለው ነገር መሆኑን የሚናገሩት አቶ አማረ፣ እምነት ግን የሁሉ ነገር መሠረት በመሆኑ ወድቆ ያገኙትን ነገር በሙሉ መልሰው ለባለቤቱ እንደሚሰጡ ይናገራሉ።

ይኹን እንጂ ጓደኞቻቸውም ሆኑ ዘመዶቻቸው፣ እንዲሁም አብዛኛው የሚያውቃቸው ማኅበረሰብ፣ ‘አንተ መቼውንም አትለወጥም፤ ለምንድን ነው የምትመልሰው?’ በማለት እንደሚወቅሷቸው እና በዚሁ ድርጊታቸው ያዘኑ እና የተቆጡ እንዳሉ ይናገራሉ።

“ማኅበረሰቡ ጠልቶኛል ማለት እችላለሁ። እኔ የምፈልገው ግን በመጀመርያ የድርጅቱን ሕግ ማክበር ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እምነቴን እና ፈጣሪዬን ማክበሬን ነው። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ቤተሰቦቼ በሥራዬ ወይንም በባህርዬ ከተደሰቱ ሌላው ለእኔ ምንም አይደለም” ይላሉ።

አክለውም “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሕግ፣ ያንተ ያልሆነን ነገር አትውሰድ ይላል። ይህ ደግሞ ትክክለኛ መመርያ እና ሰውን የሚያስደስት ነው” ብለዋል አቶ አማረ።

በሚያደርጉት ድርጊትም የማይጸጸቱ መሆኑን በመጥቀስ “እኔ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ የተለየ ስሜት ነው የሚሰማኝ። እቃውን ረስቶ ለሄደ ሰው ስመልስ በጣም ደስታ ይሰማኛል” በማለት አብሯቸው ያደገው ባህሪ የደስታቸው ምንጭ መሆኑን ይገልጻሉ።

አቶ አማረ ታደሰ 200 ሺህ ዶላር ከሚሠሩበት ስፍራ አግኝተው ለባለቤቱ መልሰዋል የሚለው መረጃ በማኅበራዊ ሚደያ ላይ በስፋት በተሰራጨበት ወቅት አንዳንድ ሰዎች ‘እንዴት አንድ ሰው 200 ሺህ ዶላር ይዞ ወደ አየር መንገድ ሊገባ ቻለ’ በማለት ጥያቄ ሲያነሱ ተስተውሏል።

አቶ አማረ በበኩቸው አንዳንድ መንገደኞች አየር መንገዱን ተጠቅመው ወደ ሌላ አገር በሚበሩበት ወቅት፣ ከአየር መንገዱ ውስጥ ሳይወጡ ወደ ሌላ አገር ሲጓዙ፣ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ከአገራቸው ይዘውት የመጡትን ገንዘብ ይዘው መጓዝ እንደሚችሉ አስረድተዋል።