“ሰቆቃው ከሶሪያ ሱዳን ተከተለኝ”

ካሪም ከሁለት ዓመት በፊት የትውልድ አገሩ ሶሪያን የእርስ በእርስ ጦርነት ሸሽቶ ወደ ሱዳን ሸሽቶ ነበር። አሁን በድጋሚ ጦርነት አግኝቶታል።

አሁን ቤት አልባ ሆኗል። ሶሪያ ከመመለስ ውጭ አማራጭ ያለው አይመስልም።

በሱዳን መዲና ካርቱም ነው የ23 ዓመቱ ካሪም ይሠራ የነበረው።

ይሠራበት የነበረው ድርጅት ቤት፣ መኪና እና በየወሩ 500 ዶላር ደመወዝ ይሰጠዋል።

ገንዘቡ ከሱ ተርፎ ለቤተሰቡ ሶሪያ ይደርስ እንደነበር ይናገራል።

ከወር በፊት ቀለበት ለማሰር አቅዶ ነበር። ፍቅረኛውን ከእናቱ ጋር አስተዋውቋል። በዚህ መሀል በሱዳን ውጊያ ተጀመረ።

“በሱዳን ሕይወቴ ጥሩ ነበር። ከዚህ የተሻለ አልመኝም” ይላል።

ሁለቱ የሱዳን ጄነራሎች መዋጋት ሲጀምሩ ካሪም ከፊል ሕይወቱን እንደተነጠቀ ተሰማው።

የሚያውቀው ሶሪያዊ ተገድሏል። እሱም እጣው እንዳይሰርሰው ከካርቱም ተነስቶ በቀይ ባሕር ወደምትገኘው ፖርት ሱዳን ሸሸ።

አብረውት ሌሎችም ሶሪያውያን ነበሩ።

“ተረግመናል”

ጉዟቸው ሁለት ቀን ነው የወሰደው። በመደበኛ ጊዜ 40 ዶላር የሚያስከፍለው ጉዞው አሁን 400 ዶላር ይጠየቅበታል።

እሱና ሌሎች ሶሪያውያንን ‘ክፉ ዕድል’ እያሳደዳቸው እንደሆነ ይሰማዋል።

“ታሪክ ራሱን እየደገመ ነው። እዚህ በድጋሚ እየኖርን ያለነው ሶሪያ ውስጥ ያለፍንበትን ሕይወት ነው። ገና ሕይወትን አልኖርኳትም። ተረግመናል” ይላል።

ከፖርት ሱዳን ለመውጣት አልቻለም። አውሮፕላን አግኝተው ቦታውን ጥለው የወጡ ሰዎችን ያውቃል። እነዚህ ሰዎች ገንዘብ ያላቸው ናቸው።

“ሁሉም ነገር ከገንዘብ ጋር ይያያዛል። ገንዘብ ያላቸው ራሳቸውን ማዳን ይችላሉ” ይላል።

ከሪም ከቢቢሲ ጋር በጽሑፍ መልዕክት ነው ያወራው። ስልኩን መስጊድ ውስጥ ቻርጅ እያደረገ ነበር ታሪኩን ያካፈለን።

በሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ሳቢያ በርካቶች ወደ ሱዳን ተሰደዋል።

ይፋዊ ቁጥር ባይኖርም እስከ 150 ሺህ እንደሚደርሱ ይገመታል።

ገንዘብ ያላቸው ወይም የሀብታም ልጅ የሆኑ ሶሪያውያን በአጎራባች አገሮች የመኖሪያ ፈቃድ ስላላቸው ሱዳንን ጥለው ወጥተዋል። እሱ ግን አልቻለም።

ያደረገው ኢድሊብ ውስጥ ሲሆን ወደ አሌፖ የተሰደደው ከዓመታት በፊት ነው። እዛም በከበባ ውስጥ ነው ከቤተሰቡ ጋር የኖረው።

ለቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ እንደሆነ ይናገራል።

ቤተሰቡና ዘመዱ የሚተዳደረው ከሱዳን በሚልከው ገንዘብ ነበር።

ይህ ሁሉ ሆኖም ተስፋ አልቆረጠም። በነገሩ ልቡ መሰበሩ ግን አልቀረም።

“ወደ ጅዳ መሄድና ሌላ አማራጭ መፈለግ እችላለሁ። ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ 400 ዶላር ያስፈልገኛል” ይላል።

ለቱሪስት ቪዛ የሚከፍለው ገንዘብ ስለሌለው ወደ ግብፅ መሰደድ አይችልም።

“ምግብ የምንገዛበት ገንዘብ ጨርሰናል። እንዴት 1,350 ዶላር መበደር እንችላለን። ሱዳን ለሁለት ዓመት ስሠራ የቆጠብኩት አንድ ሺህ ዶላር ነው። ይሄንንም ወደ ፖርት ሱዳን ለመምጣት አውዬዋለሁ” ይላል።

በወደብ ከተማው እየተዘዋወረ ዜና በመከታተል የወደፊት እጣ ፈንታው ምን ሊሆን እንደሚችል ለመወሰን ይሞክራል።

በሳዑዲ አረቢያ ዘመድ ወይም እዛ እንደማይቀር ማረጋገጫ የሚሰጥ ሰው ስለሌለው ሳዑዲ መሄድ እንደማይችል ተረድቷል።

“ሸብቻለሁ”

ፓስፖርቱም በቅርቡ ቀኑ ያልፋል። ስለዚህ ወደ ኢትዮጵያ ወይም ሌላ አገር መጓዝ አይችልም።

“እግዚአብሔርን ምንም ነገር ስሜት አይሰጠኝ። ፀጉሬ ሸብቷል። ያለ ፍርሃት ወደ ሶሪያ ልመለስ ነው የምችለው። ከዚህ በኋላ ምንም የማጣው ነገር ስለሌለኝ ግድ አይሰጠኝም” ሲል ይናገራል።

ወደ ሶሪያ ከተመለሰ የግዳጅ ወታደራዊ ሥልጠና ስለሚጠብቀው ሶሪያ ለመሄድ አያስብም ነበር። በሌላ አገር የተሻለ ሕይወት መገንባት ነበር ሕልሙ።

አሁን ግን ወደ ትውልድ አገሩ ሶሪያ መመለስ እንኳን ከባድ ነው። ገንዘብ የለውም።

በፖርት ሱዳን በጎ ፈቃደኛ ለቢቢሲ እንደገለጹት በየቀኑ ወደ ሶሪያ የሚሄድ አውሮፕላን ለንግድና ለአደጋ ጊዜ ሽሽት በሚል ዘርፍ ተከፍሎ የሚካሄድ ይሆናል።

የንግድ አውሮፕላን ትኬት የሚገዛው ሶሪያ ከሚገኙ የጉዞ ኤጀንቶች ነው። የአደጋ ጊዜ ሽሽት አውሮፕላን ግን በስም ዝርዝር ለተጠቀሱ ሰዎች ነጻ አገልግሎት ይሰጣል። 450 ዶላር ያስከፍላል።

በቅድሚያ የሚጓዙት አረጋውያን፣ ሕሙማን፣ ነፍሰ ጡሮች እና ቤተሰቦች ናቸው።

የከሪም ቤተሰብ ትኬት ሊገዛለት እየሞከረ እንደሆነ ይናገራል። ሆኖም ግን ሁሉም በረራዎች ሙሉ እንደሆኑ ተነግሯቸዋል።

“ሁሉም ችግር በ3,000 ዶላር ይቀረፋል። በዚህ ብር ፓስፖርቴን አሳድሳለሁ። ከዛ በግብፅ የቱሪስት ቪዛ አወጣለሁ። ከዛ እህቴ ያለችበት ቱርክ እሄድና ወደ አውሮፓ ለመግባት መንገድ እፈልጋለሁ። ግን በዚህ ጊዜ ማን 3,000 ዶላር ያበድረኛል?”