'ሕይወቷ በማስታገሻ መድኃኒት ላይ ተንጠልጥሏል'- የጋዛ ህጻናት አሰቃቂ ታሪክ

ነሃድ አቡ ጀዛር የሁለት ዓመት ልጇን፣ ፋጡማን ለማባበል ቀስ ብላ ትዘምርላታለች።

እውነታ በጣም አሰቃቂ በሚሆንበት ጊዜ ግን ልጇን የሚያረጋጋው ምን እንደሆነ መገመት አስቸጋሪ ይሆንባታል።

"ጥቅምት 6 የቦምብ ፍንዳታ ከእንቅልፍ ቀሰቀሰን። ራሳችንን ያገኘነው ግን በቤታችን ፍርስራሽ ውስጥ ነው። ፋጡማ እቅፌ ውስጥ የነበረች ቢሆንም እንደምንም ለመውጣት ቻለች። ልረዳት ስሞክር ሁለቱም እግሮቿ መጎዳታቸውን አየሁኝ” ስትል ጋዛ ሆነው ለቢቢሲ እየሰሩ ለሚገኙ ጋዜጠኞች ተናግራለች።

የፋጡማ በደረሰባት ጉዳት ሁለቱም እግሮቿ ከጉልበት በታች መቆረጥ ነበረባቸው።

በደቡባዊ ጋዛ በሚገኘው የአውሮፓ ሆስፒታል በእናቷ ታፋ ላይ ተቀምጣለች። ፊቷ በእንባ ርሷል፣ እግሮቿ በነጭ ፋሻ ተጠቅልለው ህመም እንደበረታባት በሚያሳይ መልኩ ታለቅሳለች።

ነሃድ እና ባለቤቷ ልጅ ለመውለድ ለ14 ዓመታት ሞክረው አልተሳካለቸውም ነበር። በኋላ ፋጡማን ወልደው ለመሳም በቁ።

" በመትረፏ በጣም ደስተኛ ነኝ። ግን ጥፋቷ ምንድን ነው? ምን ስህተት ሠራች? የሌሎች ልጆች ዓይነት ሕይወት እንዲኖራት እፈልጋለሁ" ስትል ነሃድ ትናገራለች።

"ያለማቋረጥ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን እንሰጣታለን። አንዱ ህመሙን አላስታግስ ሲላት ሌላ እንሰጣታለን። ህይወቷ በህመም ማስታገሻ መድኃኒት ላይ ተንጠልጥሏል። በየዕለቱ ደግሞ ቀዶ ሕክምና ታደርጋለቸ።”

እስራኤል ከአንድ ወር በላይ በጋዛ በፈጸመችው ከፍተኛ የቦምብ ድብደባ በነዋሪዎች ላይ አስከፊ ጉዳት ደርሷል።

በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ከ4,400 በላይ ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 10,800 ሰዎች ተገድለዋል። እስራኤል የቁጥሩን ትክክለኛነት ጥያቄ ብታነሳበትም የዓለም ጤና ድርጅት አሃዞቹ ትክክለኛ ናቸው ብሎ ያምናል።

ከ 26,000 በላይ ሰዎች ሲጎዱ፤ እንደ ፋጡማ ሁሉ ብዙዎቹ ህይወታቸውን የሚቀይር ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ቀጥሎ ያለው ክፍል የ13 ዓመቷ አሚራ አል-ባዳዊ ትገኛለች። የሚያምር አስደናቂ ቡናማ ዓይኖች እና ጥቁር ፀጉር አላት።

"ቦምብ ሲፈነዳ ተኝቼ ነበር። መተንፈስ ስላልቻልኩ ከእንቅልፌ ነቃሁ። የሰዎች ድምጽ ይሰማኛል። ከበላዬ እና ከስሬ የድንጋይ ክምር ነበር" ትላለች።

አሚራ በአከርካሪዋ ላይ ከባድ ጉዳት አጋጥሟታል። ለወደፊት መራመድ ትችል እንደሆነ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

በጥቃቱ እናቷን እና ሰባት ወንድሞቿን አጥታለች።

አባቷ ኢያድ አል ባዳዊ ከእስራኤል ጦር ማስጠንቀቂያ በኋላ አል-ዛይቱን ከሚገኘው ቤታቸውን በመሸሽ ደቡባዊ ጋዛ ወደምትገኘው ራፋህ መሄዳቸውን ተናግሯል። በሸሹበትም ግን ጥቃቱን አልቀረላቸውም።

ጋዛውያን ለደህንነታቸው ሲሉ ወደ ደቡብ እንዲሄዱ እስራኤል ስታስጠነቅቅ ቆይታለች። እንደዛም ሆኖ በማዕከላዊ ጋዛ እና ደቡባዊ አካባቢዎች ጥቃት መሰንዘሯን ቀጥላለች።

ሐማስ ላይ ያነጣጠሩ ዒላማዎችን የትም ይሁን የት እንደምታጠቃ ይናገራል።

"ወደ ሆስፒታል ተወሰድኩኝ፤ ልጆቼና ባለቤቴ መገደላቸውን ሰማሁ። አሳድገን አስተምረናቸዋል። አንዳንዶቹንም ድረናቸዋል። አሁን ደግሞ አጣናቸው" ይላል ኢያድ።

የ18 ወር ወንድ ልጁ እና ሦስት ሴት ልጆቹ በሕይወት በመቆየታቸው ምስጋናው ትልቅ ነው።

አሚራ "ሠላም እና ደህንነትን እንዲሰፍን እጠይቃለሁ። የደረሰብኝ ጉዳት መታከም እና ወደ ተለመደው ሕይወቴ፣ ወደ ቤቴ መመለስ እፈልጋለሁ። እንደገና ደህንነት እንዲሰማኝም እፈልጋለሁ" ብላለች።

ምኞቷ ነው እንጂ የምትመለስበት ቤት የለም። ጋዛ ውስጥ ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ የለም።

ሆስፒታሎቹ በሟቾች እና በቆሰሉ ሰዎች ይሞላሉ። ከእነዚህ ውስጥ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉት ህጻናት ናቸው።

አሴፍ አቡ ማዘን በአል-ኑሴይራት ይኖር ነበር። የ11 ዓመቱ ልጅ በሰፈሩ በሚገኝ ክለብ ውስጥ እግር ኳስ ተጫውቷል። በተከላካይነት ቢጀምርም፤ የቡድኑ የግብ ዘብ ለመሆን በቅቶ ነበር።

አሴፍ ከጓደኞቹ ጋር እግር ኳስ እየተጫወተ ሳለ ነበር በአየር ድብደባ ቤቱ ወድሞ ሕይወቱን እስከወዲያኛው የቀየረው ጉዳት ያጋጠመው።

ቀኝ እግሩ ከጉልበቱ በታች መቆረጥ ነበረበት። አሁንም ድረስ በፋሻ ታስሯል።

"ገና 11 ዓመቴ ነው። ማንንም አልጎዳሁም። ጥፋቴ ምንድን ነው?" ሲል ይጠይቃል አሴፍ።

ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋች ለመሆን የነበረው ሕልሙ አሁን አብቅቷል።

"በጣም ጥሩ ተጫዋች ነበርኩ። ከፈለግክ አሰልጣኜን መጠየቅ ትችላለህ" ይላል።

አንድ አርብ ጠዋት በነበራቸው ጨዋታ የተቃራኒ ቡድን ተጫዋች አክርሮ ወደ ጎሉ ማዕዘን ኳሷን ይመታል። “ተወረወርኩኝ እና የኳሷን አቅጣጫ ለማስቀየር ቻልኩ” ሲል ያስታውሳል።

ቤተሰቡ አሴፍ ሙሉ የእግር ኳስ ትጥቁን ለብሶ የሚያሳየውን ፎቶግራፍ አላቸው። ፎቶው ላይ ውሃ ሰማያዊ ማሊያ ፣ ጥቁር ሰማያዊ ቁምጣ ፣ አረንጓዴ እና ጥቁር እግር ኳስ ጫማ ተጫምቶ ይታያል።

"የእግር ኳስ ትጥቄ በቤታችን ፍርስራሽ ስር ተቀብሯል። ካልሲዎቼ፣ ጫማዎቼ እና ኳሴ የሉም። ሁሉም ወደ አቧራነት ተቀይሯል" ይላል አሴፍ።

ከጥቃቱ በኋላ በበጎ ፈቃደኞች ዕርዳታ ነው በተሽከርካሪ ወንበር ሆስፒታሉ የደረሰው።

የሆስፒታሉ ግቢ ጦርነት ለሚሸሹ ሰዎች መጠለያ በሆኑ ጊዜያዊ ድንኳኖች የተሞላ ነው።

አሴፍ ከበጎ ፈቃደኞቹ ጋር ይቀልዳል። ግቢው ሳቅ የሌለበት ቦታ ሊመስል ይችላል። ብዙ ጋዛውያን እየደረሰባቸው ያለውን ፍርሃት እና ሃዘን የሚቋቋሙት አንድም በዚህ መንገድ ነው።

እናቱ የሚያሳየውን ጥንካሬ የተሞላበት ፊት እያየች "የክፍል ጓደኞቹ እግሩ የተቆረጠው ልጅ ብለው ይጠሩት እንደሆነ እና ይሳለቁበት እንደሆነ ጠየቀኝ" ትላለች።

"ሲሮጥ ወይም እግር ኳስ ሲጫወት የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምስል ለሊት ለሊት እያየ ሲያለቀሰ ብዙ ጊዜ አየዋለሁ" ስትል ታክላለች።