በኬንያ የሚሠለጥኑ የዩኬ ወታደሮች ለዓመታት ወሲባዊ ጥቃት እና ግድያ መፈጸማቸውን የሕዝብ እንደራሴዎች ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በኬንያ ወታደራዊ ሥልጠና ሲያደርጉ የነበሩ የዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች ለአሥርት ዓመታት ወሲባዊ ጥቃት፣ ግድያ እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ እንደነበር የሕዝብ እንደራሴዎች ተናገሩ።
የኬንያ የሕዝብ እንደራሴዎች፤ ወታደራዊ የጦር ሰፈር ይገኝባቸው ከነበሩ የላይኪፒያ እና ሳምቡሩ ግዛት ነዋሪዎች የተሰጡ አሰቃቂ ምስክርነቶችን አጣቅሰዋል።
የኬንያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቋቋመው ኮሚቴ ምርመራ ሲያካሂድ የዩኬ ወታደሮች ቃላቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከተጠያቂነት ማምለጣቸው ተገልጿል።
በኬንያ የዩኬ ከፍተኛ ኮሚሽን እንዳለው በኬንያ ምክር ቤት በቀረበው ሪፖርት ላይ ምላሹ አለመካተቱ አሳዝኖታል።
"ማስረጃ ከቀረበ" ክሶቹን "ሕግን ተመርኩዞ" ለመመርመር ቁርጠኛ መሆኑንም አክሏል።
የዩኬ ወታደሮች ለዓመታት በማዕከላዊ ኬንያ ሥልጠና አድርገዋል። ወታደሮቹ በሰብአዊ መብት ጥሰትም ሲከሰሱ ቆይተዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም፤ በየዓመቱ ከ1,000 በላይ ኬንያውያን ወታደሮችን ታሠለጥናለች። የዩኬ ወታደሮችም ሥልጠና ለማካሄድ ወደ ኬንያ ይላካሉ።
የኬንያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቋቋመው ኮሚቴ ለሁለት ዓመታት ምርመራ ካካሄደ በኋላ 94 ገጾች ያሉት ሪፖርት አውጥቷል።
የዩኬ ወታደሮች የሥነ ምግባር መርሆችን እና የሰብአዊ መብት ሕግጋትን እንደጣሱ ሪፖርቱ ይጠቁማል። በተጨማሪም ከባቢ አየር ላይ ጉዳት በማድረስ እና በሠራተኞች ብዝበዛ ተከስሰዋል።
የተጎጂዎች፣ የማኅበረሰብ መሪዎች እንዲሁም የሲቪል ማኅበራት ምስክርነት በሪፖርቱ ተካትቷል።
ወታደራዊ ሰፈር የነበረባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ ወታደሮቹ ግድያ እና ብዝበዛ ከመፈጸማቸው ባሻገር በአደባባይ ግብግብ እንዲሁም የትራፊክ አደጋ በመፍጠር ሁከት ያነሱ ነበር።
በተጨማሪም ሪፖርቱ "ወታደሮቹ እንደ አጋር ሳይሆን እንደ ወራሪ ነው የሚታዩት። ከቅኝ ግዛት ብዝበዛ ያልተናነሰ ጥቃት በነዋሪዎች ላይ አድርሰዋል" ይላል።
እአአ በ2012 በኛኙኪ ግዛት አግነስ ዋንጂሩ የተባለች ኬንያዊት አስከሬን በሆቴል የውሃ ታንክ ውስጥ መገኘቱ አይዘነጋም።
የአግነስ አስክሬን ከመገኘቱ ከሦስት ወራት በፊት ከዩኬ ወታደሮች ጋር ማምሸቷ ተገልጿል።
የኬንያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቋቋመው ኮሚቴ "ፍትሕ ዘግይቷል፤ ፍትሕ ለማግኘት የተደረገው ጥረት ተስፋ አስቆራጭ ሆኗል" ሲልም ወንጅሏል።
"የምርመራ ሒደቱ በወታደሮቹ በርካታ መሰናክሎች ገጥመውታል። ፍትሕ እንዳይሰፍን ያደረገው ዋነኛ ምክንያት ይሄው ጣልቃ ገብነት ነው" ሲልም አክሏል።
ባለፈው ወር በአግነስ ግድያ የተጠረጠረ ወታደር በዩኬ የታሰረ ሲሆን ለኬንያ ተላልፎ እንደሚሰጥም ተገልጿል።
እአአ በ2012 አርብቶ አደሩ ቲላም ለርሽ በዩኬ ወታደሮች መገደሉ ቢገለጽም እስከአሁን ድረስ ክስ አልተመሠረተም።
የዩኬ መንግሥት በሥራ ላይ የነበረ ወታደር አርብቶ አደሩን ተኩሶ በመግደሉ የተሰማውን ሐዘን ገልጿል።
ሆኖም ግን የዩኬ ዐቃቤ ሕግ ክስ ለመመሥረት የሚያበቃ ማስረጃ አለማግኘቱን መግለጹን የኬንያ ሪፖርት ያመለክታል።
በወታደሮች ወሲባዊ ጥቃት ከመፈጸሙ ባሻገር ተጎጂዎች ፍትሕ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ውጤታማ አለመሆኑ ተገልጿል።
በተለይም የሳምቡሩ እና ማሳይ ሴቶች ላይ "ሰፊ ወሲባዊ ጥቃት" መፈጸሙን ሪፖርቱ ያሳያል።
"ወታደሮች ሴቶችን ደፍረዋል፤ ወሲባዊ ጥቃትም ፈጽመዋል። እነዚህ ሴቶች አሁንም ድረስ ፍትሕ አላገኙም" ሲልም ያትታል።
ሴቶቹ እንጨት ሲለቅሙ፣ ውሃ ሲቀዱ እንዲሁም ከብት ሲያግዱ በወታደሮቹ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የዐይን እማኞች ተናግረዋል።
እአአ በ1977 አርቸርስ ፖርት በተባለ አካባቢ "ወታደሮች 30 ሴቶችን በስለት በማስፈራራት መድፈራቸው" ተገልጿል። አንዳንዶቹ ሴቶች ቤታቸው ሳሉ ነበር የተደፈሩት።
ወታደራዊ ዕዙ "ወሲባዊ ጥቃትን እንደማይታገስ" እና "ክሶቹን ችላ እንደማይል" ገልጿል።
ወታደሮቹ አልኮል ጠጥተው በአደባባይ ሰውነታቸውን እንደሚያጋልጡ እና ወሲባዊ ትንኮሳ እንደሚፈጽሙ ሪፖርቱ ያመለክታል።
የኬንያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቋቋመው ኮሚቴ "አባት አልባ ሆነው የቀሩ" ልጆችን ጉዳይም መርምሯል።
"በርካታ ልጆች ከዩኬ ወታደሮች ተወልደዋል። ወታደሮቹ ልጆቻቸውን ስለማይንከባበኩ እናቶቹ እንግልት ደርሶባቸዋል። ማኅበረሰቡም አግልሏቸዋል" ብሏል።
ወታደሮቹ ሥልጠና ሲያካሂዱ የሚጠበቅባቸውን የአካባቢ ጥበቃ ምዘና እንዳላደረጉ ሪፖርቱ ያትታል። ነጭ ፎስፈረስ መጠቀማቸው ከባቢ አየር ላይ ጉዳት ማድረሱም ተገልጿል።
በመሣሪያ ተረፈ ምርት እና መርዛማ ጭስ ምክንያት የአካቢው ነዋሪዎች ለመተንፈሻ አካል ሕመም እና ለውርጃ ከመጋለጣቸው ባሻገር የቀንድ ከብቶች ሞተዋል።
ወታደራዊ ዕዙ የኬንያን የአካባቢ ጥበቃ መርሕ ተከትሎ መሥራቱን ገልጿል።
ወታደሮቹ ለመርማሪ ኮሚቴው ምላሽ እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ጥሪ ቢደረግላቸውም "ዲፕሎማት" መሆናቸውን በመጥቀስ "ከተጠያቂነት ነጻ" እንደሆኑ ተናግረዋል።
በኬንያ የዩኬ ከፍተኛ ኮሚሽን አዲስ ማስረጃዎች መገኘታቸውን ተከትሎ ምርመራ እንደሚያደርግ አስታውቋል።















