ዩኬ በኬንያ ወታደሮቿ በስልጠና ወቅት ባስነሱት ቃጠሎ 2.9 ሚሊዮን ፓውንድ ካሳ ለመክፈል ተስማማች

የፎቶው ባለመብት, British Army Training Unit Kenya (Batuk)
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በኬንያ ያሉ ወታደሮቹ በስልጠና ላይ እያሉ ካስነሱት ቃጠሎ ጋር ተያይዞ ጉዳት ለደረሰባቸው ኬንያውያን 2.9 ሚሊዮን ፓውንድ ካሳ ለመክፈል ተስማማ።
ከፍርድ ቤት ውጭ የተደረሰው ይህ ስምምነት በኬንያ ሪፍት ቫሊ ሎላዳይጋ በተሰኘ ስፍራ ከአራት ዓመት በፊት ለደረሰው የእሳት ቃጠሎ ነው።
ይህ ስምምነት 7 ሺህ 723 ኬንያውያን በዚህ ቃጠሎ ምክንያት ንብረታቸውን እንዳጡ እንዲሁም የጤና እክል እንደረሰባቸው በፍርድ ቤት ለረጅም ጊዜ ያደረጉትን የህግ ፍልሚያ ተከትሎ የተደረሰ ነው።
በኬንያ የብሪታንያ ከፍተኛ ኮሚሽን "እሳቱ እጅግ የሚያሳዝን ነው" ያለ ሲሆን ዩናይትድ ኪንግደም ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት "በቂ ጊዜ፣ ጥረት አና ሃብት መድባለች" ብለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ለተጎጂዎች ምን ያህል ገንዘብ እንደተከፈለ ባይገልጽም ጉዳዪን የተመለከቱት ጠበቃ 2.9 ሚሊዮን ፓውንድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኬቨን ኩባይ ተጎጂ ደንበኞቻቸው ካሳው አነስተኛ ነው የሚል ቅሬታ ቢያቀርቡም የተደረሰውን ስምምነት አሞካሽተዋል።
የህግ ባለሙያው እንደሚሉት አማራጩ "እያንዷን ጉዳይ በፍርድ ቤት አቅርቦ ለማስመስከር ተጨማሪ ሰባት ዓመታት ክርክር መቀጠል ነበር" ብለዋል።
ይህም ፈታኝ ነው ያሉት ጠበቃው ምክንያቱም መረጃዎች በዚህ አራት ዓመታት ውስጥ መጥፋታቸውን በመጥቀስ ነው።
ጠበቃው ተጎጂ ደንበኞቻቸው በሎላዳይጋ እሳት ምክንያት በተነሳው ጪስ የመተንፈሻ ችግር ስለመግጠሙ የህክምና ማስረጃ የላቸውም ብለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስቴር የእሳት ቃጠሎው በስልጠና ልምምድ ላይ የካምፕ ምድጃ ተፈንግሎ ሳይሆን አይቀርም ብሏል።
በዚህ ቃጠሎ ምክንያት 7 ሺህ ሄክታር መሬት የተቃጠለ ሲሆን ሆኖም የግል፣ የማህበረሰቡ መሬት ጉዳት አልደረሰበትም ብሏል።
በዚህ ቃጠሎ ምክንያት የከባቢው ጉዳት በዙሪያው በሚኖሩ ማህበረሰብ ላይ ተጽእኖ መፍጠሩን እንዲሁም ከስፍራው ያመለጡ የዱር እንስሳት በነዋሪዎች ንብረት ማውደማቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በኬንያ በሥልጠና ላይ ባሉ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ወታደሮች ጥሰቶች ተፈጽሞብናል የሚሉ ኬንያውያን ምስክርነታቸውን በአገሪቱ ለተቋቋመ አጣሪ ቡድን ምስክርነታቸውን የሰጡ ሲሆን ቃጠሎውም አንዱ ነበር።
በዚህ ምስክርነት ላይ የእሳት ቃጠሎው የተነሳ ሲሆን ለከፋ የጤና ችግር የተዳረጉ ነዋሪዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ለአራት ቀናት እንደቆየ የተነገረለት የእሳት ቃጠሎ ከ7 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ሲያወድም፣ ቢያንስ የአንድ ሰው ሕይወት ቀጥፏል።
በችሎቱ ላይ የተገኘው ሊፓሶ ሌጌይ እሳቱ የዱር እንሳሳቱን መኖሪያ ካወደመ በኋላ አንድ አንበሳ ሰዎች ወደሚኖሩበት ሰፈር ገብቶ ጥቃት እንዳደረሰበት ገልጿል።
የደረሰበት ጥቃት የከፋ እንደሆነ ተናግሮ በሕይወት በመትረፉ ዕድለኛ እንደሆነ መስክሯል።
ሊሞት ተቃርቦ እንደነበር የገለጸው ሊፓሶ ጀርባው ላይ ጉዳት ደርሶብኛል ብሏል።
በተጨማሪም ቃጠሎው መሬታቸው ላይ ባደረሰው ውድመት ምክንያት ማረስ እንደማይችሉም በዚህ ወቅት የተናገረው ሊፓሶ ጅብ እና ነብርን ጨምሮ የዱር እንስሳት ኑሯቸውን ስጋት ላይ ጥለውታል ብሏል።
በርካቶችም ከእሳት ቃጠሎው በኋላ የከፋ የአተነፋፈስ እና የዐይን እክሎች እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል። ሲሞን ካቡሩ የተባለው ግለሰብ በጭስ ምክንያት በገጠው የአተነፋፈስ ችግር ምክንያት ለመድኃኒት ጥገኛ እንደሆነ የህክምና ማስረጃዎቹን የፓርላማ አባላትን ለያዘው አጣሪ ቡድን አሳይቷል።
የብሪታንያ መንግሥት የተቃጠለውን ከባቢ እንደገና ያለማ ሲሆን ወታደራዊ ስልጠናዎችም በዚያው ይከናወናሉ።
የሎላዳይጋ ፓርክ ወደ 49 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬትን የሚሸፍን ሲሆን የላይኪፒያ ኮረብታማ መሬት አካል ነው። ይህ በመቶ ሺዎች ሄክታር ስፋት ያለው መሬት ብሪታንያ በቅኝ ግዛት ወቅት ተቆጣጥራው የነበረ ሲሆን እስካሁንም የመሬት ውዝግቡ ቀጥሏል።
ይህ ስፍራ ሌላኛው ብሪታንያ ወታደሮቿን የምታሰለጥንበት ባቱክ የተሰኘው ክፍል የሆነው ንያቲ ባራክስ በጥቂት ኪሎሜትሮች ይርቃል።
የባቱክ የጦር ሰፈር የተቋቋመው አገሪቱ ከቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ነጻነትዋን ከተጎናጸፈች በኋላ በአውሮፓውያኑ 1964 ሲሆን፣ ስፍራውም ከናይሮቢ 200 ኪሎሜትት ርቀት ላይ በምትገኘው ኛኙኪ ነው
በኬንያ በመሰልጠን ላይ ያሉት እና ባቱክ የተሰኙት የዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች አድርሰዋቸዋል የተባሉ ግፎችን እና በደሎችን ለማጣራት ህዝባዊ አጣሪ ቡድን ተቋቁሟል።ወታደሮቹ በመኪና ገጭቶ መግደልን ጨምሮ፣ ግድያ፣ ወሲባዊ ብዝበዛዎችና ሌሎች ጥሰቶች በመፈጸም ተወንጅለዋል።
ለዚህ አጣሪ ኮሚቴ መነሻ የሆነው ከአስራ ሶስት ዓመታት በፊት በዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች ተገድላ ተጥላ የተገኘችው ኬንያት የአግነስ ዋንጂሩ አስደንጋጭ ሁኔታ ነው።
በ21 ዓመቷ የተገደለችው አግነስ ዋንጂሩ አስከሬኗ በማዕከላዊ ኬንያ በሚገኝ ሆቴል በሽንት ቤት ፍሳሽ ማጠራቀሚያ ውስጥ የተገኘ ሲሆን፣ ይህ የሆነው ከዩኬ ወታደሮች ጋር አንድ ምሽት ላይ ስትዝናና ከታየች ከሦስት ወራት በኋላ ነው።















