"ሠራዊታችን በሶማሊያ ተልዕኮ መሰማራቱ የትኛውንም ሀገር የማስፈራራት ዓላማን አላነገበም" የግብፅ ፕሬዚዳንት

ግብፅ ሠራዊቷ በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (ኤዩሶም) ስር መሰማራቱ "የትኛውንም ሀገር የማስፈራራት ዓላማ" የለውም ሲሉ ፕሬዚዳንት አብደል ፈታህ አል ሲሲ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ይህንን የተናገሩት የሶማሊያውን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድን ካይሮ ውስጥ በአል ኢትሃዲያ ቤተ መንግሥት ተቀብለው ካናገሩ በኋላ ሐሙስ፣ ጥር 15/2017 ዓ.ም. በሰጡት የመሪዎቹ የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

ሠራዊቷ በኤዩሶም መካተቱን አስመልክቶ ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ ለአራተኛ ጊዜ ከሶማሊያው ፕሬዚዳንት ጋር በተገናኙበት በዚህ ቆይታቸው ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው መወያየታቸውን ፕሬዚዳንት አል ሲሲ መግለጻቸውን የግብፅ የመረጃ አገልግሎት ያሰፈረው ንግግራቸው ያስረዳል።

ሀገራቸው በአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮን (ኤዩሶም) በተመለከተ "ያለን ተሳትፎ በሶማሊያ ውስጥ ደኅንነትን እና መረጋጋትን ለማምጣት እንጂ የትኛውንም ሀገር የማስፈራራት ዓላማ የለውም" ብለዋል።

አክለውም "ተሳትፏችን አዎንታዊ ገጽታ ያለው ነው። ባለፉት 30 ዓመታት በሶማሊያ ያለው ሁኔታ እያሳሰበን ይገኛል። የእኛ ተልዕኮ በዋናነነት አላማው ለሶማሊያ ሕዝብ አጋርነታችንን ለማሳየት ነው" ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ኤዩሶም የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮን (አትሚስ) እንዲተካ ያሳለፈውን ውሳኔ በቅርቡ ማጽደቁ ይታወሳል።

በውሳኔው መሠረት የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት እስከ መጪው የአውሮፓውያኑ ሰኔ መጨረሻ ድረስ 1,040 የፖሊስ አባላትን ጨምሮ እስከ 12 ሺህ ገደማ መለዮ ለባሽ የፀጥታ አካላት በአዲሱ ተልዕኮ እንዲያሰማሩ ፈቅዷል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ላይ በትብብር ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ታኃሣሥ መጨረሻ ላይ ያወጣው መግለጫ በደፈናው ሀገራቱ በተልዕኮው ላይ በጋራ ይሠራሉ ቢልም፤ የኢትዮጵያ ወታደሮች አዲስ በሚሰማራው የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ውስጥ ስለ መሳተፋቸው ያለው ነገር የለም።

በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ውዝግብ በአንካራ ስምምነት መፈታቱን ተከትሎ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮችን በኤዩሶም ውስጥ ላለማካተት አሳልፋው የነበረውን ውሳኔ ልትቀለብስ እና በተልዕኮው ለማካተት እያጤነች እንደሆነ ተዘግቧል።

ኢትዮጵያ ሶማሊኣ የግዛቴ አካል ናት ከምትላት እና እራሷን ነጻ ሀገር ነኝ ብላ ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የገባችውን የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ካልሰረዘች ጦሯ በሰላም አስከባሪው ተልዕኮ ውስጥ እንደማይካተት የሶማሊያ ባልሥልጣናት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያን ውጥረት ያረገበውን የአንካራ ስምምነትን ተከትሎ በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በአዲስ አበባ ተገናኝተው የተወያዩት የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ሐሙስ ወደ ግብፅ ያቀኑት በፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ጋባዥነት እንደሆነ የሶማሊያ የዜና ወኪል ሶና ዘግቧል።

የግብፁ ፕሬዚዳንት የሶማሊያ አቻቸውን የጋበዟቸው "ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሚደረጉ የጋራ ጥረቶችን ለማጠናከር እና በፀጥታ እና በቀጣናው ሰላም ላይ ትብብሮች" ላይ ለመወያየት እንደሆነ ሶና አክሏል።

ሀገራቱ ከዚህ ቀደም ከፈረሙት ወታደራዊ ስምምነት በተጨማሪ ሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ እና ምጣኔ ሀብትን ባካተተ መልኩ ወደ ስልታዊ አጋርነት የሚያሳድግ የጋራ የፖለቲካ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ተብሏል።

ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ግንኙነት ለመከታተል እና በተለያዩ መስኮች ያለውን ትብብር የበለጠ ለማሳደግ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለመፈተሽ በመሪዎች ደረጃ ዓመታዊ የፖለቲካ ጉባኤ ማድረግን እንደ አንድ ግብ አስቀምጧል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማተራመስ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በዝምታ እንደማትመለከት ከዚህ ቀደም ማስታወቋ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ይህንን ያለችው ወታደሮችን እንዲሁም የጦር መሳሪያዎችን የጫኑ ሁለት የግብፅ የጦር አውሮፕላኖች በላፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በሞቃዲሾ የአየር ማረፊያ ደርሰዋል መባላቸውን ተከትሎ ነው።

በተጨማሪ የሶማሊያ መንግሥት "ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሠራ ይገኛል" ስትል መክሰሷ ይታወሳል።

በአሁኑ ጉብኝት ሁለቱ መሪዎች አፍሪካ ቀንድ የፀጥታ እና የፖለቲካ ሁኔታዎች እና የቀይ ባሕር ደኅንነትን ጨምሮ በተለያዩ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ባወጡት መግለጫ አትተዋል።

በሶማሊያ፣ በግብፅ እና በኤርትራ መሪዎች መካከል መስከረም 30/2017 ዓ.ም. በአሥመራ የተካሄደው ጉባኤ በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት እና ቅንጅት ከፍተኛ መሻሻል በማምጣት ረገድ አስተዋጽኦ እንዳለው መስማማታቸውንም ነው አል ሲሲ የገለጹት።

አገራቱ በነበራቸው ውይይት ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት መሠረታዊ የሆነውን ሶማሊያን መደገፍን ማዕከል አድርጎ በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ቅንጅታዊ አሠራርን ማጎልበት የሚቻልባቸው መንገዶች ላይ መወያየታቸው ተገልጿል።

ነጻነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ከተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረው ቁርሾ ሞቃዲሾ ከግብፅ እና ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታጠናክር አድርጓታል።

ግብፅ እና ኤርትራ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት በተለያዩ ምክንያቶች የሻከረ ነው።

ግብፅ ግንባታው ሊጠናቀቅ በተቃረበው የሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከአስር ዓመታት በላይ ከኢትዮጵያ ጋር አለመግባባት ውስጥ መቆየቷ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከኤርትራ ጋር ያላቸው ግንኙነት ምንም ችግር እንደሌለበት ቢናገሩም፤ በትግራይ የተካሄደው ጦርነት ካበቃ በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት መቀዛቀዙ ሲነገር ቆይቷል።

ሦስቱ መሪዎች "ከውስጥ እና ከውጭ የሚመጡ ተግዳሮቶችን መቋቋም ለማስቻል፣ የሶማሊያን ተቋማት ለማጠናከር እና የሶማሊያ ብሔራዊ ፌዴራል ሠራዊት ሽብርተኝነትን መዋጋት እንዲችል ለማድረግ" መስማማታቸው ተገልጾ ነበር።

የግብፁ ፕሬዚዳንት ሐሙስ ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ጋር በነበራቸው ውይይት አጋርነታቸውን የማጠናከርን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተው ግብፅ፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ የሚሳተፉበት ሁለተኛው የሦስትዮሽ ጉባኤ ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑን መሪዎቹ መስማማታቸውን ገልጸዋል።