ሟቹ የዚምቧብዌ ፕሬዚዳንት ሙጋቤ በኢፕስቴን ዶሴ ውስጥ ስማቸው ተጠቅሶ ተገኘ

የቀድሞው የዚምቧብዌ ፕሬዚዳንት ከባለቤታቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በዚምቧብዌ ፖለቲካ ውስጥ ለአራት አስርት ዓመታት የቆየቱት ሮበርት ሙጋቤ እና ባለቤታቸው
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የቀድሞው የዚምቧብዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ከወሲብ ወንጀለኛው ሟች ጄፍሪ ኢፕስቴን ጋር የገንዘብ ትስስር ሊኖራቸው እንደሚችል በቅርቡ ይፋ የሆኑት ዶሴዎች አሳዩ።

ወንጀለኛው ጄፍሪ ኢፕስቴን እአአ በ2015 ከጃፓናዊው ሥራ ፈጣሪ ጆኢ ኢቶ ጋር በነበረው የኢሜል መልዕክት ልውውጥ ላይ ለዚምቧብዌ የመገበያያ ገንዘብ መውደቁን ተከትሎ አዲስ ገንዘብ ለማቅረብ ፕሬዚዳንት ሙጋቤን ቀርቦ እንዲያነጋግሯቸው ተጻጽፈዋል።

ዚምቧብዌ በወቅቱ በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የተነሳ የመገበያያ ገንዘቧ ወድቆ ነበር።

ኤፍቢአይ እአአ በ2017 ያደረገውን ምርመራ የሚያሳይ ዶሴ ላይም ያልተረጋገጡ "አስተማማኝ የሰው ምንጮችን" በመጥቀስ ኢፕስቴን ለፕሬዚዳንት ፑቲን የሀብት አስተዳዳሪያቸው እንደሆነ እና ለሙጋቤም ተመሳሳይ አገልግሎት እንደሰጠ ተጠቅሶ ነበር።

ግለሰቦች በኢፕስቴን ዶሴዎች ውስጥ ስማቸው ተጠቅሶ ተገኘ ማለት የሰሩት ጥፋት አለ ማለት እንዳልሆነ ተገልጿል።

ቢቢሲ የሙጋቤን ቤተሰብ ምላሽ ጠይቋል።

የዚምባብዌ የነፃነት መሪ እና የረዥም ጊዜ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሮበርት ሙጋቤ የሞቱት መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደባቸው ከሁለት ዓመታት በኋላ፣ እአአ በመስከረም 2019 በ95 ዓመታቸው ነበር።

ኤፕስቴን የተባለው እና ከበርካታ ቱጃሮች ጋር ግንኙነት ያለው አሜሪካዊ የፋይናንስ ባለሙያ ከፈጸማቸው የወሲብ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የተፈረደበት ሲሆን እአአ በነሐሴ ወር 2019 በወሲብ ንግድ ዝውውር ክስ ያለውን የፈርድ ቤት ቀጠሮ እየጠበቀ እያለ ራሱን እስር ቤት ውስጥ አጥፍቶ ተገኝቷል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2008 በፍሎሪዳ ውስጥ ከ14 ዓመት ልጅ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ለመፈጸም በመጠየቅ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የተፈርዶበት የነበረ ሲሆን እአአ በሐምሌ 2010 የእስራት ፍርዱን አጠናቋል።

የአሜሪካ የፍትህ ቢሮ የለቀቃቸው የቅርብ ጊዜ ሰነዶች ከአምስት ዓመታት በኋላ በጆይቺ "ጆይ" ኢቶ እና በኤፕስቴን መካከል የተደረጉ የኢሜይል ልውውጦችን ያሳያል።

የኢሜል ልውውጡን የሚያሳይ ምስል

የፎቶው ባለመብት, US Department of Justice

ይፋ የሆነው ሰነድ ላይ የኢቶ የኢሜይል አድራሻ የተሰረዘው ሲሆን ለዚምባብዌ አዲስ የመገበያያ ገንዘብ ስለመስጠት ያወራል።

"ለፍለጋ የሚሆን ለም መሬት" በሚል ርዕስ የተጻፈው መልዕክት ላይ ኤፕስቴን ከሙጋቤ ጋር ወዳጅ እንደሆነ ሲጠየቅ "አይደለሁም፣ ግን ትኩረቱን በቀላሉ ማግኘት ቢቻል ዚምባብዌ በጣም ጥሩ ቁርስ ትሆናለች፣ እንዲሁም ውብ መሆን አለበት" ሲል መልሷል።

ኢቶ በመስከረም 2019 የኤምአይቲ ሚዲያ ላብራቶሪ ኃላፊ ከነበረበት የአካዳሚክ ማዕከሉ ከኤፕስቴን በተቀበለው ልገሳ ምክንያት ከሥልጣኑ ለቅቋል።

የአሜሪካ የፋይናንስ ባለሙያው የሙጋቤ ሀብት አስተዳዳሪ ቢሆን ኖሮ ፕሬዚዳንቱ የተጣለባቸውን ማዕቀቦች የጣሰ ስለሚሆን ቢቢሲ በቅርቡ በተለቀቀው የኤፕስቴን ዶሴዎች ውስጥ ስለተካተቱት ሰነዶች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ኤፍቢአይን ጠይቋል።

ሙጋቤ እአአ ከ2003 ጀምሮ በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎባቸው ነበር። በዚህም የተነሳ የአሜሪካ ኩባንያዎች እና ዜጎች ከሙጋቤ ጋር እንዳይነግዱ ወይም የገንዘብ ግብይቶችን እንዳያደርጉ ተከልክለዋል።

ዚምባብዌ እና ሙጋቤ በኤፕስቴን ዶሴዎች ውስጥ በሌሎች ደብዳቤዎች ላይም ስማቸው ተጠቅሶ ተገኝቷል።

እአአ በሚያዚያ ወር 2012 የተጻፈ ኢሜይል ላይ በስህተት ሙጋቤ በጣሊያን ሆስፒታል ውስጥ እያጣጣሩ መሆኑ ተጠቅሷል።

የላኪው ሙሉ ስም እና የኢሜይል አድራሻ እንዳይታይ የተደረገ ሲሆን ነገር ግን መልዕክቱ ከ"ጆናታን" እንደተላከ ይገልጻል።

ኤፕስቴን በአገሪቱ ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉት ሰዎች አድራሻ እንዲልክለት ተይቆ "ይህ ሰው በእርግጥ ከሞተ አንዳንድ ጥሩ ኩባንያዎች አሏቸው" ሲል አክሏል።

የኢፕስቴን የኢሜል ልውውጥን የሚያሳይ ሰነድ

የፎቶው ባለመብት, US Department of Justice

ሙጋቤ በዚያን ወቅት የ88 ዓመት አዛውንት የነበሩ ሲሆን ከቀናት በኋላም ከሲንጋፖርተ እነደተመለሱ የአገሪቱን የነፃነት በዓል ላይ ተገኝተው ነበር።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የፕሬዚዳንቱ የቀድሞ አጋር ለቢቢሲ እንደተናገሩት እንዲህ ያሉት ስህተቶች ስለ ሙጋቤ የተነገረው መረጃ የፈጠራ ወሬ መሆኑን ያመለክታሉ።

ዚምባብዌ አሁንም በሙጋቤ ዛኑ-ፒኤፍ ፓርቲ የምትመራ ሲሆን እአአ በ2009 የዚምባብዌ ዶላር የመግዛት አቅም ከወደቀ በኋላ ለአስርተ ዓመታት በዋጋ ግሽበት ውስጥ ቆይታለች።

አዲስ የመገበያያ ገንዘብ ለማስተዋወቅ የተደረጉ በርካታ ሙከራዎች አልተሳኩም።

ነገር ግን ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው ዚግ የተባለው የመገበያያ ገንዘብ. ምንም እንኳን ብዙ ሰዎች አሁንም በአሜሪካ ዶላር ላይ ጥገኛ ቢሆኑም፣ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት ችሏል።