ቢል እና ሒላሪ ክሊንተን በወሲብ ወንጀለኛ ኤፕስቲን ጉዳይ ለመመስከር ተስማሙ

ቢልአና ሒላሪ ክሊንተን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን እና ባለቤታቸው ሒላሪ ክሊንተን በወሲብ ወንጀለኛው ሟች ጄፍሪ ኢፕስቴን ጉዳይ ኮንግረስ ፊት ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን ለመስጠት ተስማሙ።

ባልና ሚስቱ ቃላቸውን ለመስጠት የተስማሙት ለወራት በምክር ቤቱ የቁጥጥር ኮሚቴ ፊት ለመቅረብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በወንጀል እንዲጠየቁ ለማድረግ ድምጽ ከመስጠቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ነው።

ቢል ክሊንተን እአአ በ2019 ከሞተው ከኤፕስቲን ጋር የሚተዋወቁ ቢሆንም በወሲብ ወንጀል ድርጊት ውስጥ ስለነበረው ተሳትፎ ምንም እውቀት እንደሌላቸው ገልጸዋል። ግንኙነታቸውን ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ማቋረጣቸውንም ይናገራሉ።

ክሊንተኖች ቃላቸውን መቼ እንደሚሰጡ ገና አልታወቀም። የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በኮንግረስ ኮሚቴ ፊት ቀርቦ ሲመሰክር እአአ በ1983 ከሞቱት ከጄራልድ ፎርድ በኋላ ይህ የመጀመርያው ይሆናል፥።

በሪፐብሊካኖች የሚመራው የቁጥጥር ኮሚቴ ባለፈው ወር ክሊንተንን በወንጀል ለመጠየቅ የሚያስችለውን እርምጃ ያጸደቀ ሲሆን ይህም ከበርካታ የዲሞክራት አባላት ድጋፍ አግኝቶ ነበር።

ሰኞ ዕለት ምሽት የክሊንተን ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አንጀል ኡሬኛ ጥንዶቹ በኮሚቴ ፊት ቀርበው ምስክርነታቸውን እንደሚሰጡ አረጋግጠዋል።

ኡሬኛ "በቅን ልቦና ተደራድረዋል" ሲሉ ከኮሚቴው ጋር ንግግር እንደነበር ጠቁመዋል።

"የሚያውቁትን በመሐላ ተናግረዋል፤ ግን ግድ አልሰጣችሁም። ነገር ግን የቀድሞው ፕሬዝዳንት እና የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እዚያ ይገኛሉ። ለሁሉም የሚሆን ምሳሌ ለማስቀመጥ በጉጉት ይጠባበቃሉ።"

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባልና ሚስቱ ከዚህ ቀደም ለኮሚቴው በቃለ መሃላ የተደገፈ ቃላቸውን እንዲሁም ስለ ኤፕስቲን ያላቸውን "ውስን መረጃ " ማጋራታቸውን ተናግረዋል።

ጥንዶቹ ሕጋዊ መጥሪያውን "ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባዘዙት መሠረት የፖለቲካ ተቀናቃኞችን ለማሸማቀቅ የሚደረግ ሴራ ነው" ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።

ቢል ክሊንተን ከኤፕስቲን ጥቃት በተረፉ ሰዎች ምንም ዓይነት ውንጀላ ቀርቦባቸው የማያውቅ ሲሆን ጄፍሪ ኤፕስቲን ከታዳጊዎች የወሲብ ንግድ ጋር ስላለው ግንኙነት ምንም ዕውቀት እንደሌላቸው ተናግረዋል።

የኤፕስቲን የአውሮፕላን በረራ መረጃ ቅጽ ክሊንተን እአአ ከ2002 እና 2003 መካከል አራት በረራዎቸን ማድረጋቸውን ያሳያሉ።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ከታዳጊዎች የወሲብ ንግድ ወንጀለኛው የጄፍሪ ኤፕስቲን መኖሪያ እንዲሁም ከሀብታም እና ኃያላን ሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያሳዩ ፎቶዎችን ይፋ ሆነዋል።

በፎቶዎቹ ላይ ከሚታዩት ታዋቂ ግለሰቦች መካከል የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ልዑል አንድሪው ማውንትባተን ዊንዘር እና የቀድሞው የትራምፕ አማካሪ ስቲቭ ባነን ይገኙበታል።

አንዱ ምስል የቀድሞው ፕሬዚዳንት በመዋኛ ገንዳ ውስጥ ሆነው የሚያሳይ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በሙቅ ውሃ ገንዳ ውስጥ መሆናቸውን በሚገልጽ ሁኔታ ዘና ብለው የሚታዩበት ምስል ነው።

የክሊንተን ቃል አቀባይ ኡሬኛ ፎቶዎቹ ይፋ የሆኑት በታህሳስ ወር መሆኑን በመግለጽ ክሊንተን የኤፕስቲን ወንጀሎች ይፋ ከመሆናቸው ዓመታት በፊት ግንኙነት ማቋረጣቸውን እና የቆዩ መሆናቸውን በመግለጽ አስተባብለዋል፥።

ክሊንተኖች ባለፈው ወር ጉዳዩን ለሚመለከተው የቁጥጥር ኮሚቴ ሊቀመንበር ጀምስ ኮመር የኤፕስቲን ምርመራ የተያዘበት መንገድን ተችተው ደብዳቤ ጽፈው ነበር።