ኢትዮጵያ ለከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት የተጋለጠ በርካታ ሕዝብ ካለባቸው አምስት አገራት አንዷ ሆነች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሁለተኛውን የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባኤን እያስተናገደች የምትገኘው ኢትዮጵያ ለከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት የተጋለጠ በርካታ ሕዝብ ካለባቸው አምስት አገራት መካከል መሆኗን አንድ ሪፖርት አመለከተ።
"2025 Global Report on Food Crises" በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ሪፖርት በመካሄድ ላይ ባለው በአዲስ አበባ ጉባኤ ላይ በቀረበ ሌላ ሪፖርት ተጠቅሷል። ሪፖርቱ የምግብ ችግር ያለባቸውን 53 ሀገራት እና ግዛቶችን ያጠቃልላል።
ጉባኤው ላይ የቀረበው "የዓለም የምግብ ዋስትና እና የተመጣጠነ ምግብ ሁኔታ 2025" በሚል ርዕስ ያለው ሪፖርት ሲሆን፣ የተዘጋጀው በዓለም ምግብ እና የእርሻ ድርጅት፣ በዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ የዓለም የጤና ድርጅት እና ሌሎች የተመድ ድርጅቶች በጋራ የወጣ ነው።
ካለፈው ሳምንት መጨረሻ እሁድ ሐምሌ 20/ 2017 ዓ.ም. መካሄድ የጀመረውን ጉባኤ ኢትዮጵያ ከጣሊያን ጋር በጋራ ነው ያዘጋጀቸው።
በጉባኤው ላይ የቀረበው ሪፖርት አሁንም እየተባባሱ ያሉ የሰብዓዊ ቀውሶች "ምግብ ዋስትናን እና በብዙ ሀገራት በቂ ምግብ የማግኘት መብት መረጋገጡን በእጅጉ እየሸረሸሩ" እንደሚገኙ ያትታል።
በ234 ገጾች የተዘጋጀው ሪፖርቱ "ስር የሰደደ የምግብ ዋስትናን የመከታተል ሰፊ ዓላማ" እንዳለው ሰፍሯል። ስር ሰደድ የምግብ ዋስትና አብዛኛውን ጊዜ በመዋቅራዊ ምክንያቶች የሚከሰት እና ቀጣይነት ያለው የምግብ ዋስትና እጦትን እንደሚያካትት በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
ከዚህ በተጨማሪም ስር የሰደደ የምግብ ዋስትና እጦት ሕይወትን ወይም ሕይወትን የማያሰጋ፤ ነገር ግን በጊዜ ሂደት የሚቀጥል እና የሰዎችን ደኅንነት እና የማኅበረሰብ እና የሀገራትን የረዥም ጊዜ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድሩ አነስተኛ የከፋ የምግብ ዋስትና እጦቶችን እንደሚያጠቃልል ሪፖርቱ ያብራራል።
ይህ ሪፖርት ባለፈው ግንቦት ወር አጋማሽ ላይ የወጣውን "2025 Global Report on Food Crises" ጠቅሶ ኢትዮጵያ ለከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት የተጋለጠ በርካታ ሕዝብ ካለባቸው አምስት አገራት አንዷ መሆኗን አስፍሯል።
በሪፖርቱ መሠረት 22 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት የተጋለጡ ናቸው።
ከኢትዮጵያ ጋር ለከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት የተጋለጠ ሕዝብ አላቸው ተብለው የተጠቀሱት ሌሎች አራት አገራት በቅደም ተከተል ናይጄሪያ፣ ሱዳን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ባንግላዴሽ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪም ፍልስጤም (የጋዛ ሰርጥ)፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ የመን እና ሄይቲ ደግሞ ከጠቅላላ ሕዝባቸው አብዛኛው ለከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት የተጋለጠባቸው አገራት ናቸው።
በሪፖርቱ መሠረት መቶ በመቶው የጋዛ ሰርጥ ሕዝብ ከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት ገጥሞታል።
በደቡብ ሱዳን እና ሱዳን ከሚኖሩት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት፣ እንዲሁም ግማሽ የሚጠጋው የየመን እና የሄይቲ ሕዝብ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ መሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል።
ኢትዮጵያ እአአ ከ2016 ጀምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝባቸው ከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት የሚጋለጥባቸው ተብለው በቋሚነት ከሚጠቀሱ ሀገራት ከመካከል እንደምትጠቀስ ሪፖርቱ ያመለክታል።
ሌሎቹ አገራት ናይጄሪያ፣ የሶሪያ አረብ ሪፐብሊክ እና የመን፣ አፍጋኒስታን እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ናቸው።
ዓለም አቀፍ ተቋማት ይህን ቢሉም ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ግን የሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊዎች ቁጥር ባለፉት አምስት ዓመታት "በሀገር አቀፍ ደረጃ በ86 በመቶ ቀንሷል" ይላል።
የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከዚህ ሪፖርት መውጣት አንድ ወር በፊት በሚያዝያ 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ዘጠኝ ክልሎች "ሰብአዊ ድጋፍን በራሳቸው አቅም [ሸፍነዋል]" ብሏል።















