በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባዔ ምንድን ነው? አስተናጋጅ አገራትስ እንዴት ይመረጣሉ?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ

የፎቶው ባለመብት, ABIY AHMED

የምስሉ መግለጫ, በጉባኤው ለመሳተፍ አዲስ አበባ የገቡት የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቀባበል ሲደረግላቸው

ኢትዯጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ እና በማደግ ላይ ባለ አገር የተሰናዳውን ሁለተኛውን የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባዔ ከትናንት እሁድ ሐምሌ 20/2017 ዓ.ም. ጀምሮ እያስተናገደች ነው።

ኢትዮጵያ እና ጣሊያን በጋራ ያዘጋጁት ጉባዔ ከአራት ዓመታት በፊት በመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ቢሮ በኩል የተዘጋጀ ነው።

"ድሃ ይሁን ሀብታም፤ ልጅ ይሁን አዋቂ በዚህ ዓለም ሁሉም ሰው ምግብ ማግኘት አለበት። ደኅንነቱ የተጠበቀ እና የተመጣጠነ ምግብ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ጤና እና ተስፋም ነው" የሚል መልዕክት በመግለጫው መግቢያ ላይ ሰፍሯል።

እአአ በ2021 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የምግብ ሥርዓት ጉባኤ በዋና ፀሐፊው አስተባባሪነት ሲሰናዳ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የምግብ ሥርዓትን ድጋሚ ማጤን ወሳኝ ተደርጎ ታይቷል።

የፖለቲካ ቁርጠኝነትን እና ተጠያቂነትን ለማሳደግ የተመድ ዋና ፀሐፊ ጉባኤው በየሁለት ዓመቱ እንዲደረግ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም መሠረት ከሁለት ዓመታት በፊት እአአ በ2023 የመጀመሪያው የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባኤ (UNFSS+2) በሮም ጣሊያን በዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት ዋና መሥሪያ ተካሂዷል።

ጉባኤውን ጣሊያን እና የተመድ የተለያዩ ኤጀንሲዎች ተባብረው ያሰናዱት ሲሆን፤ የምግብ ሥርዓት ዓለም አቀፍ ቅድሚያ የሚሰጠው እንደሆነ በማረጋገጥ የተፋጠነ የምግብ ሥርዓት ሽግግር እንዲካሄድ ስድስት የእርምጃ ጥሪዎችን በማቅረብ ተጠናቋል።

ይሁን እንጂ ከዚህ ጊዜ በኋላ የዓለም ዓውድ የተቀየረ ሲሆን፤ በዩክሬን፣ በሱዳን እና በመካከለኛው ምሥራቅ የቀጠለው ግጭት የምግብ ዋስትናን ታይቶ በማይታወቅ መንገድ ቀይሮታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሁለተኛውን ጉባኤ (UNFSS+4) ኢትዮጵያ ከጣሊያን ጋር ለማዘጋጀት እንዴት እንደተመረጠች በዝርዝር ባይነገርም ከኢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የተመድ የምግብ ሥርዓት አስተባባሪ ምክትል ኃላፊ ሊና ሳቪሊ ኢትዮጵያ ጉባኤውን ለማዘጋጀት በወሰደችው ኃላፊነት ክብር ይሰማናል ሲሉ በአገሪቱ ጠያቂነት እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከተመድ ጋር የተያያዙ ከፍተኛ ጉባኤዎችን የሚያዘጋጁ አገራት ፍላጎታቸውን በማንፀባረቅ እና ዝርዝር ዕቅድ በማቅረብ የሚመረጡ ሲሆን፣ ተመድ አገራቱ መስፈርቶችን ማሟላታቸውን አረጋግጦ ፈቃድ ይሰጣል።

ኢትዮጵያ ለዚህ ጉባኤ "መሪ ዕቅድ" በማውጣት ሰፊ ዝግጅት ማድረጓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያሳወቀ ሲሆን፤ አስፈላጊውን የፀጥታ እና የሎጂስቲክ ዝግጅት ማድረጓን ገልጿል።

ከአራት ሺህ በላይ ጉባኤተኞች ይሳተፉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተነገረለት ጉባኤው፤ ከ4,700 በላይ ተሳታፊዎች በበይነ መረብ (ኦንላይን) መመዝገባቸው ተነግሯል።

እስከ ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም. ለሦስት ቀናት የሚቆየው ጉባኤው በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) እየተካሄደ ሲሆን፤ ዘላዊ፣ አካታች እና ቋሚ የምግብ ሥርዓትን ለሰዎች እና ለምድር እንዲጠቅም ማፋጠን አጠቃላይ ግብ የሰነቀ ነው።

ጉባኤው የአገራትን የምግብ ሥርዓት ሽግግር ቀረብ ብሎ ማየት ስኬት እና ድክመቶችን ለመገምገም ዓላማ መያዙን ምክትል ኃላፊዋ ገልፀዋል።

የአዲስ አበባው ጉባኤ ሮም በተካሄደው የመጀመሪያው ጉባኤ ተፈፃሚ እንዲሆኑ የተወሱ ውሳኔዎች አፈፃፀማቸውን መገምገም እና ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ያተኮረ ነው።

ጉባኤው በዋናነት ሦስት ዓላማዎች ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ እድገትን እና የተወሰዱ ትምህርቶችን መገምገም የመጀመሪያው ነው።

ይህም አባል አገራት የምግብ ሥርዓት ግባቸውን ከሚያዩበት መንገድ ጀምሮ፤ ስኬቶቻቸውን እና የገጠሟቸውን መሰናክሎች ማስረዳትን ያካትታል።

ሁለተኛው ዓላማ እድገትን መከታተል እና ክፍተቶችን ለመለየት ተጠያቂነትን የማጠናከሪያ መንገድ ሲሆን፣ ሦስተኛው ደግሞ ለመዋዕለ ነዋይ በርን መክፈት ነው።

ይህም ለመፍትሔዎችን ማሳደግ፣ አስቻይ ከባቢ መፍጠር፣ ሽግግርን ለመደገፍ የመንግሥት እና የግል ትብብር ያካትታል።

ኃላፊ ሊና ሳቪሊ ይህን ሲያብራሩ በርካታ አገራት የምግብ ሥርዓታቸውን ለማሸጋገር ቁርጠኛ ቢሆኑም የሚያስፈልጋቸው የገንዘብ ሀብት ግን እንደሚያጥራቸው ገልፀው መዋዕለ ነዋይን ማንቀሳቀስ ሌላኛው የጉባኤው ግብ ነው።

በዚህ ጉባኤ መንግሥታት፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የተመድ ኤጀንሲዎች፣ የገንዘብ እና የግል ዘርፉ ወኪሎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ባለድርሻዎች እና ተመራማሪዎች ይሳተፋሉ።

በጉባኤው መጨረሻ የዓለም የምግብ ሽግግር እድገት ሪፖርት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትንተና፣ እናዲሁም የአዘጋጆች ማጠቃላያ ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጉባኤው ከተጠናቀቀ በኋላ ውጤቶች የተመድን ጠቅላላ ጉባኤ እና በወራት በኋላ በብራዚል በሚካሄደው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ጨምሮ በትላልቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤያት አባሪ እንዲሆን ይደረጋል።