ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኳታር በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የነበራትን የሽምግልና ሚና አቋረጠች
ኳታር በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የምታደርገውን የተኩስ አቁም እና ታጋቾችን የማስፈታት ሚናዋን አቋርጣለች ሲሉ ባለሥልጣናት ተናገሩ።
ሐማስ እና እስራኤል ለመደራደር "ፍቃደኛነታቸውን" ሲያሳዩ ሥራዋን እንደምትቀጥል ኳታር ተናግራለች።
አገሪቱ ከዚህ ውሳኔ የደረሰችው የፍልስጤሙ ቡድን በጋዛ የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም የቀረበውን አዲስ ሃሳብ ውድቅ አድርጓል በማለት የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሐማስ ተወካዮች በኳታር መገኘታቸውን እንደማትቀበል መግለጻቸውን ተከትሎ ነው።
ኳታር ከድርድሩ ራሷን ማግለሏን የተናገረች ሲሆን በዶሃ የሚገኘው የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ "ዓላማውን አላስፈጸመም" መባሉን "የተሳሳተ ነው" ስትል ተናግራለች።
“ኳታር ከ10 ቀናት በፊት የተደረገው ድርድር የመጨረሻ ሙከራ መሆኑን ለሁለቱ አካላት አሳውቃ ነበር። በዚህም ከስምምነቱ የማይደርሱ ከሆነ በሐማስ እና በእስራኤል መካከል ስታካሂድ የቆችውን የማስታረቅ ጥረቷን እንደምታቆም ገልጻለች” ሲል የኳታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አስታውቋል።
"ኳታር ጥረቶቿ እንደገና የምትቀጥለው ... ሁለቱ ወገኖች ጦርነቱን ለማቆም ያላቸውን ፍላጎት እና ቁርጠኝነት ሲያሳዩ" መሆኑን ገልጻለች።
በኦባማ አስተዳደር ጥያቄ መሠረት ሐማስ እአአ ከ2012 ጀምሮ በኳታር ዋና ከተማ መቀመጫ እንደነበረው ተዘግቧል።
በርካታ የዜና ወኪሎች ቅዳሜ ዕለት እንደዘገቡት ከሆነ ሐማስ “በቅን ልቦና ለመደራደር ፈቃደኛ ባለመሆኑ” በዶሃ የሚገኘውን የፖለቲካ ቢሮውን እንዲዘጋ ኳታር ከአሜሪካ ጋር ተስማምታለች።
የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርቶቹን "የተሳሳቱ ናቸው" ብሏል። ጉዳዩ በሐማስ ባለስልጣናት በኩልም ውድቅ ተደርጓል።
ትንሿ እና ተጽእኖ ፈጣሪ የባህረ ሰላጤዋ አገር በአካባቢው ቁልፍ ከሆኑ የአሜሪካ አጋሮች አንዷ ናት። ትልቁን የአሜሪካ አየር ኃይልን ከማስተናገድ ባለፈ ኢራን፣ ታሊባን እና ሩሲያን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ ድርድሮችን አስተናግዳለች።
በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በጋዛ ለአንድ ዓመት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም እስካሁን ያልተሳኩትን በርካታ የተኩስ አቁም ድርድሮች ኳታር ከአሜሪካ እና ከግብጽ ጋር በመሆን ስታሸማግል ነበር።
ሆኖም ግንኙነቱ እየተቀየረ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ እየጨመረ መጥቷል።
የሐማሱ መሪ የነበረው ያህያ ሲንዋር ከተገደለ በኋላ ሐማስ በዶሃ የሁለት ሰዓት የሐዘን ስነስርዓት አካሂዷል። ይህም በቅርቡ የሐማሱ መሪ ኢስማኢል ሃኒዬህ ከተገደለ በኋላ በመንግደስት ድጋፍ እና ጥበቃ ከተካሄደው የሦስት ቀናት የሐዘን ስነስርዓት በእጅጉ የሚቃረን ነው።
በጥቅምት ወር አጋማሽ በተካሄደው የመጨረሻው ዙር ድርድር ለአጭር ጊዜ የቀረበውን የተኩስ አቁም ሃሳብ ሐማስ ውድቅ አድርጎታል። ቡድኑ ጦርነቱ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም እና የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ እንዲወጡ ጠይቋል።
የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ “በዶሃ የሚገኘውን የሐማስ ቢሮን አስመልክቶ የሚወጡ የሚዲያ ዘገባዎች ትክክል አይደሉም” ብሏል።
"በኳታር የሚገኘው የጽህፈት ቤት ዋና ሚና የግንኙነት መስመር መሆን ነው... [ይህም] ቀደም ባሉ ጊዜያት የተኩስ አቁም እንዲኖር አስተዋጽኦ አድርጓል።"
እስራኤልም ስምምነቶችን ውድቅ አድርጋለች ተብላለች። በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከስልጣናቸው የተባረሩት የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ከቀናት በኋላ እንደተናገሩት ከሆነ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በደህንነት ኃላፊዎች የሠላም ስምምነት እንዲደረስ የተሰጣቸውን ምክር ውድቅ አድርገዋል ሲሉ ከሰዋል።
ሐማስ ከኳታር እንዲባረር የቀረበው ጥሪ የባይደን አስተዳደር በጥር ወር የስልጣን ዘመኑ ከማብቃቱ በፊት አንድ ዓይነት የሠላም ስምምነት እንዲደረስ ለማስገደድ የተደረገ ሙከራ ይመስላል።
ሐማስ ከዶሃ እንዲወጣ ከተገደደ የፖለቲካ ፅህፈት ቤቱን የት እንደሚያደርግ ግልጽ አይደለም። ኢራን አማራጭ ብትሆንም በሐምሌ ወር ቴህራን ውስጥ የቀድሞው መሪ እስማኤል ሃኒዬህ መገደላቸው ኃላፊዎቹ የእስራኤል ጥቃት ዒላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠቁማል። ከምዕራቡ ዓለም ጋር ለሚያገናኝ ተመሳሳይ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ቅርብ አያደርጋቸውም።
የበለጠ ተስማሚ ልትሆን የምትችለው አማራጭ ቱርክ ናት። የኔቶ አባል አገር ከመሆኗም በላይ አብዛኛዎቹ የሱኒ እስልምና ተከታይ በመሆናቸው ቡድኑ በአንፃራዊነት ደህንነት የሚንቀሳቀስበትን መሠረት ይሰጠዋል ። ባለፈው መጋቢት ፕሬዚደንት ኤርዶጋን በወቅቱ የሃማስ የፖለቲካ ኃላፊ ኢስማኢል ሃኒዬ እና የልዑካን ቡድናቸውን በኢስታንቡል አስተናግዶ ነበር። "በቂ እና ያልተቋረጠ ሰብአዊ ርዳታ ወደ ጋዛ ለማድረስ መደረግ ስላለበት ሥራ እና በአካባቢው ዘላቂ ሠላም ሂደት እንዲኖር" በወቅቱ ተወያይተዋል።
እርምጃው በምስራቁ እና በምዕራቡ ዓለም መካከል እራሷን እንደድልድይ ለማስቀመጥ ለምትጥረው አንካራ ትልቅ ዕድል ሊሆን ይችላል።
እንደ ኦሳማ ሃምዳን፣ ታሄር አል-ኑኑ እና ሌሎች በመገናኛ ብዙሃን ላይ በተደጋጋሚ የሚቀርቡ ቁልፍ የሐማስ ሰዎች ከወር በላይ በኢስታንቡል ቆይተዋል።
በቱርክ ውስጥ መቆየታቸው ቀደም ሲል ለአጭር ጊዜ ብቻ ከነበራቸው ቆይታ የተለየ ነው።
ከአራት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሁለት መሪዎቹ በመገደላቸው የሐማስ አመራር ደህንነት ለቡድኑ ቁልፍ ጉዳይ ሆኗል ተብሎ ይታሰባል። በሐምሌ ወር ከተገደሉት ሃኒዬ በተጨማሪ መስከረም 26 በደቡብ እስራኤል ላይ ለደረሰው ጥቃት ዋና አቀናባሪ የነበረውን ያህያ ሲንዋርን በጥቅምት ወር ተገድሏል።
እንደአውሮፓ የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት መሠረት “ሐማስ የእስራኤልን ግድያ ለመቅረፍ በሚል የጋራ አመራር ሞዴልን ተግበራዊ አድርጓል።”
በሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት (ሩሲ) ባልደረባ የሆኑት ኤች ኤ ሄሊየር ለቢቢሲ እንደተናገሩት “አሜሪካ በቀጠናው ትልቅ የሆነውን የጦር ሰፈር ባሰፈረችበት ዶሃ ውስጥ እንደነበረው ዓይነት ከእስራኤል የግድያ ሙከራ የሚጠብቃቸውም ቦታ የለም።"
የመጨረሻው እርምጃ የተወሰደው የአሜሪካ ባለስልጣናት የእስራኤል መንግስት ጦርነቱን ለማስቆም በወሰደው አካሄድ የተበሳጩ በሚመስሉበት ወቅት ነው። በጥቅምት ወር የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ሚንስትሮች እስራኤል ህዳር 12 ተጨማሪ ሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ ካልፈቀዱ ያልተገለጸ የፖሊሲ “ጫና” እንደሚጠብቃቸው ተናግረዋል.
በርካታ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣናት በሰሜናዊ ጋዛ ያለው ሁኔታ "የፍጻሜ" ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ቅዳሜ ዕለት ደግሞ ገለልተኛው ፋሚን ሪቪው ኮሚቴ "ረሃብ ሊነሳ የሚችልበት ዕድል ከፍተኛ ነው" ብሏል።
በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና በኔታንያሁ መካከል ያለው ግንኙነት በጋዛ ጦርነት ወቅት ተባብሷል። ለፍልስጤማውያን የሚደርሰውን ሰብዓዊ ድጋፍን ማሻሻል እና አንድ ዓይነት ስምምነት እንዲደረስ ከዋሽንግተን ግፊቱ አይሏል።
ዶ/ር ሄሊየር እንደሚሉት ከሆነ ዩናይትድ ስቴትስ ለድርድር የምታደርገው ጥረት በጣም የተሳሳቱ ናቸው።
"ቀይ መስመሮችን በማዘጋጀት እና ኔታንያሁ ያለምንም ችግር እንዲሻገሩ በመፍቀድ የባይደን አስተዳደር ተጨማሪ ቅጣትን አበረታቷል። እነዚህ ጉዳዮች በሚቀጥሉት 10 ሳምንታት ውስጥ የሚቀየሩ አይመስለኝም" ብለዋል።
ኔታንያሁ እና ቀኝ ዘመም ጥምረታቸው ስምምነቶችን በተደጋጋሚ ውድቅ ከማድረግ ባለፈ በዶናልድ ትራምፕ በፕሬዝዳንትነት መመረጥ የበለጠ ልብ ሙሉነት ተስምቷቸዋል።
ትራምፕ በቀጣናው ዙሪያ የሚወስዱት አካሄድ በትክክል ባይታወቅም፤ እስራኤል በፍላጎቷ መሠረት እንድትተገብር የመፍቀድ ዕድላቸው ሰፊ ነው ተብሎ ይታሰባል።
ቀደም ሲል እስራኤል በጋዛ ውስጥ "የጀመረችውን መጨረስ" እንዳለባት ተናግረዋል። በመጀመሪያው Yስልጣን ዘመናቸው የአሜሪካን ኤምባሲ ወደ እየሩሳሌም ማዛወርን ጨምሮ ለእስራኤል በጣም ጥሩ ናቸው የተባሉትን በርካታ እርምጃዎችን ወስዷል።
ትራምፕ ስልጣን በሚይዙበት ወቅት ግጭቱን ማቆም እንደሚፈልጉም ለኔታንያሁ መናገራቸውም ተዘግቧል።
ያም ሆነ ይህ አሁን ያለው የአሜሪካ አስተዳደር በእየሩሳሌም ባለው መንግስት ላይ ያለው ተጽእኖ አነስተኛ ይመስላል።
ስለዚህ ስምምነት እንዲደረስ ለማስገደድ የተሻለው መንገድ በሐማስ ላይ ጫና ማድረግ ነው ብለው ያምናሉ። ስኬቱ የሚወሰነው ግን ኳታር ሃሳቡን በመደገፏ ላይ ይወሰናል።