ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የመጀመሪያዋ የአሜሪካ ሴት ፕሬዝዳንት ይሆናሉ ተብለው የነበሩት የካማላ ሃሪስ ሕይወት በምሥሎች
በተጠናቀቀው የአሜሪካ ምርጫ ላይ አዲስ ታሪክ ያስመዘግባሉ ተብለው ተጠብቀው የነበሩት ካማላ ሃሪስ ድል ሳይቀናቸው በዶናልድ ትራምፕ ተሸንፈው ተሰናብተዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንት ሃሪስ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አንጻር በብዙ መልኩ የተሻሉ ሆነው የመመረጥ ዕድል ይኖራቸዋል በሚል በርካቶች ቢጠብቁም አብላጫው መራጮች ድምጻቸውን ለትራምፕ ሰጥተዋል።
የመጀመሪያዋ ሴት፣ ጥቁር እና የሕንድ ዝርያ ያላቸው ድርብርብ ታሪክ በማስመዝገብ ወደ ኃያሏ አገር የመሪነት መንበር ይመጣሉ ቢባልም ሁሉም በነበር ቀርቷል።
ካማላ ዴቪ ሃሪስ ስደተኛ ከሆኑት ወላጆቻቸው ከትውልደ ሕንዳዊቷ እናታቸው ሽያማላ እና ትውልደ ጃማይካዊ ከሆኑት አባቷ ዶናልድ በካሊፎርኒያ ግዛት ኦክላንድ ውስጥ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 20/1964 ነው የተወለዱት። ካማላ ማያ የተባለች ታናሽ እህት አለቻቸው።
የካማላ አባት በስታንፈርድ ዩኒቨርስቲ ኃላፊነት ካገኙ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ነበር ካማላ ሰባት ዓመት እያሉ ነበር ወላጆቻቸው ፍቺ የፈጸሙት። ሁለቱ ሴት ልጆችም ጊዜያቸው ለሁለት ተከፍሎ ከተለያዩት ወላጆቻቸው ጋር ያሳልፉ ነበር።
የካማላ ሁለቱም ወላጆች በሰብአዊ መብቶች መከበር እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳታፊዎች ስለነበሩ፤ ካማላም ገና በለጋ ዕድሜያቸው ተመሳሳይ አመለካከት እንዲያራምዱ ረድቷቸዋል።
ካማላ በአሜሪካ ውስጥ ካሉ በታሪክ የጥቁሮች ናቸው ከሚባሉ ቀዳሚ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ በሆነው ሃዋርድ ዩኒቨርስቲ ፖለቲካል ሳይነስ እና ኢኮኖሚክስት አጥንተዋል።
በአውሮፓውያኑ 1990 ሃሪስ ከዩኒቨርስቲ ከወጡ በኋላ በካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ ዐቃቤ ሕግ በመሆን ነበር ሥራ የጀመሩት። በመጀመሪያ አላሜዳ በተባለው አካባቢ ዐቃቤ ሕግ የነበሩ ሲሆን፣ በኋላ ደግሞ ወደ ሳንፍራንሲስኮ ዞረዋል።
በ2011 ደግሞ በአሜሪካ በሕዝብ ብዛቷ ቀዳሚ የሆነችው የካሊፎርኒያ ግዛት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሆነው ሲመረጡ፣ የመጀመሪያዋ ሴት እና ጥቁር ለመሆን በቅተዋል።
በተጨማሪም የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት እና የተያያዥ ጉዳዮች መብቶች እንቅስቃሴ ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ መሪ የነበሩ ሲሆን፣ በግዛቲቱ የመጀመሪያውን የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን እንዲካሄድ አድርገዋል።
ሃሪስ በአውሮፓውያኑ 2013 በጓደኞቻቸው አማካኝነት ከዳግ ኤምሆፍ ጋር ከተዋወቁ ከዓመት በኋላ ጋብቻ መሥርተዋል። ሃሪስ ልጆች ባይኖሯቸውም የባለቤታቸው ኤምሆፍ ሁለት ልጆች የእንጀራ እናት ናት።
በዐቃቤ ሕግነት በሠሩባቸው ጊዜያት ያሳዩት ጽኑ የሕግ አቋም ወደ ፖለቲካው መድረክ እንዲሸጋገሩ በር ከፍቶላቸዋል። በአውሮፓውያኑ ደግሞ 2017 ለካሊፎርኒያ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባልነት ተመርጠዋል።
ሃሪስ በ2020 ላይ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ቢቀርቡም የምታራምዱትን ርዕዮተ ዓለም እና የፖሊሲ አማራጭ በአግባቡ ለማቅረብ ችግር ስለገጠማቸው ብዙም አልገፉበትም። ነገር ግን የጆ ባይደን ምክትል በመሆን በምርጫው ውስጥ ቀጥለው ለአሸናፊነት በቅተዋል።
ባይደን ትራምፕን በማሸነፍ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ፣ ሃሪስ የምክትል ፕሬዝዳንትነት ቦታን በመያዝ የመጀመሪያዋ ሴት፣ ጥቁር ሴት፣ እና የደቡብ እስያ ዝርያ ያላቸው በመሆን ቦታውን ለመያዝ ችለዋል።
ሃሪስ በምክትል ፕሬዝዳንትነት አሜሪካ እና ሜክሲኮ በሚዋሰኑበት ድንበር በኩል የሚጎርፉትን ስደተኞችን የመቆጣጠር ኃላፊነት ቢሰጣቸውም በቂ ሥራ አልሠሩም በሚል ሲተቹ ቆይተዋል።
በጽንስ ማቋረጥ መብት ላይ ትኩረት የሚያደርጉት ሃሪስ ቀደም ሲል ከነበሩ ፕሬዝዳንቶችም ሆነ ምክትል ፕሬዝዳንቶች በተለየ በሥልጣን ዘመናቸው የጽንስ ማቋረጫ ክሊኒክን በመጎብኘት የመጀመሪያዋ ሆነዋል።
ለ2024 ምርጫ የዲሞክራቶች ዕጩ ሆነው ቀርበው የነበሩት ጆ ባይደን በዕድሜ መግፋት ምክንያት እራሳቸውን በድንገት ከፉክክሩ ሲያገሉ ሃሪስ ባልተጠበቀ ሁኔታ ዕጩ ፕሬዝዳንት ሆነው የመቅረብ ዕድል አግኝተው ነበረ።
በአጭር ጊዜ ውስጥም ዲሞክራቶች የፓርቲያቸው አዲስ ተስፋ የሆኑትን ካማላ ሃሪስ ዕጩ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ በመደገፍ የምርጫ ዘመቻውን አጧጡፈውት የቆዩ ቢሆንም ለማሸነፍ ሳይችሉ ቀርተዋል።
ለምርጫ ቅስቀሳ ከአንድ ግዛት ወደ ሌላ ግዛት፣ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ እየከነፉ የነበሩት ሃሪስ በጥቅምት ወር 60ኛ የልደት በዓላቸውን አውሮፕላን ላይ ነበር ያከበሩት።
ሃሪስ በዘንድሮው ምርጫ ማሸነፍ ቢችሉ ኖሮ በድጋሚ በበርካታ መልኩ በአሜሪካ ታሪክ ላይ ስማቸው እንዲሰፍር ማድረግ ይችሉ ነበር።
ካማላ ሃሪስ በዶናልድ ትራምፕ በማያሻማ ሁኔታ ባይሸነፉ እና የአሜሪካውያንን ይሁንታ ቢያገኙ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት፣ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ፕሬዝዳንት እና የመጀመሪያዋ የሕንድ ዝርያ ያላቸው ፕሬዝዳንት ለመሆን ይችሉ ነበር።