በሁለት ዓመት ውስጥ ቢያንስ 94 ፍልስጤማውያን በእስራኤል እስር ቤቶች መሞታቸውን የሰብአዊ መብት ተቋም ገለጸ

ከሁለት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ቢያንስ 94 ፍልስጤማውያን እስረኞች እና ታጋቾች በእስራኤል እስር ቤቶች መሞታቸውን የሰብአዊ መብት ተቋም አስታወቀ።

'ፊዚሽያንስ ፎር ሂውማን ራይትስ እስራኤል' የተባለው ታዋቂ የእስራኤል የሰብአዊ መብት ተቋም እንደገለጸው፤ ፍልስጤማውያኑ የሞቱት ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግላቸው እስር ቤቶች ውስጥ ነው።

"ስልታዊ የሆነ ግድያ እና ግድያዎችን መሸፈን ተፈጽሟል" በማለት ተቋሙ ገልጿል።

ሪፖርቱ የሚሸፍነው ሐማስ ጥቃት ካደረሰበት ወቅት ማለትም ከጥቅምት 7/2023 እስከ ነሐሴ 7/2025 ያለውን ጊዜ ነው።

ባለፉት 10 ዓመታት ወደ 30 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ይዞታ ሥር ሳሉ መሞታቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል።

የእስራኤል የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር "ቁጥጥር በሚያደርጉ አመራሮች ክትትል መሠረት እና ሕግን ተከትሎ ይሠራል" ሲል ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቷል።

"ሁሉም ታራሚዎች የሚያዙት ሕግን በተከተለ መንገድ ነው። ሕክምና የማግኘት፣ ንጹህ ቦታ የመቆየት እና ተስማሚ የኑሮ ሁኔታ የማግኘት መብታቸው ሥልጠና በወሰዱ ባለሙያዎች አማካኝነት ይጠበቃል" በማለትም አክሏል።

ሆኖም ግን ከውጭ አካላት በተሰነዘሩ ክሶች እና ቁጥሮች ላይ አስተያየት እንደማይሰጥ አስታውቋል።

ከሐማስ ጥቃት በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን የተለያየ ውንጀላ ቀርቦባቸው በጋዛ እና በዌስት ባንክ በእስራኤል ተይዘዋል። አብዛኞቹ በይፋ አልተከሰሱም።

የሰብአዊ መብት ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት ስልታዊ የሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አጋልጧል።

እስራኤል "የደኅንነት እስረኞች" በምትላቸው ፍልስጤማውያን ላይ የሚፈጸሙ ጥሰቶችን ያጋለጠው ተቋሙ፤ እየደረሰ ያለው አስጊ የሆነ ስልታዊ የመብት ጥሰት ነው ብሏል።

ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ የሰብአዊ መብት ጥሰቱ እየተፈጸመ ያለው ይፋዊ የሆነ ፖሊሲን በመከተል እንደሆነም ጠቅሷል።

እስራኤል በይዞታዋ ሥር ስላሉ ፍልስጤማውያን ለቀይ መስቀል መረጃ መስጠት እንዲሁም እስረኞችን ማስጎብኘት አቁማለች።

የእስራኤሉ የሰብአዊ መብት ተቋም ያወጣው ሪፖርት ይፋዊ መረጃ ላይ የተመረኮዘ እንደሆነ ጠቅሷል።

መረጃውንም ከፎረንሲክ ምርመራ ውጤት፣ ከእረኞች፣ ከቤተሰቦቻቸው እና ከጠበቆቻቸው እንዲሁም ከሌሎች ሰብአዊ መብት ተቋማት ሪፖርት ጋር አመሳክሯል።

በሪፖርቱ መሠረት፤ 52 ፍልስጤማውያን የሞቱት በእስራኤል ወታደራዊ እስር ቤት ውስጥ ሳሉ ሲሆን፤ 42 የሚሆኑት ፍልስጤማውያን የሞቱት በእስራኤል የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሥር በሚገኙ ሲቪል እስር ቤቶች ነው።

የእስራኤል ቀኝ ዘመም ብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር እና የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ፓርቲ ቁልፍ አባል ኢታማር ቤን-ጊር ፖሊሲዎች በዋነኛነት በሪፖርቱ ተጠቅሰዋል።

በሚኒስትሩ አስተዳደር ሥር ያሉ የግዳጅ ማቆያዎች "ወደ ስቃይ እና ብዝበዛ ማዕከልነት" መለወጣቸውን ይገልጻል።

በየዕለቱ አካላዊ ጥቃት እና ስልታዊ ስቅይት እንደሚፈጸም፤ በዚህም ምክንያት በርካታ ፍልስጤማውያን ለሞት እንደተዳረጉ ሪፖርቱ ያሳያል።

በብዛት የፍልስጤማውያን ሞት የተመዘገበው በጋዛ አቅራቢያ በደቡባዊ እስራኤል በሚገኘው በስዴ ታሚን ወታደራዊ እስር ቤት ነው።

በዚህ እስር ቤት አንድ ፍልስጤማዊ ተደብድቦ፣ በፊንጢጣው ስለት መከተቱ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ፤አምስት የእስራኤል ተጠባባቂ ወታደሮች በብዝበዛ እና የከፋ አካላዊ ጉዳት በማድረስ ተከስሰዋል።

ወታደሮቹ ፍልስጤማዊውን በፖሊስ ሺልድ ከበው ጥቃት ሲያደርሱበት የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል ወጥቷል። ተጠባባቂ ወታደሮቹ ክሱን አስተባብለዋል።

ፍልስጤማዊው ላይ የደረሰው ጥቃት አገሪቱን ለሁለት ከፍሏል። አንዳንድ ቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች ወታደሮቹን አውግዘው ድርጊቱ ላይ ምርመራ እንዲደረገግ ሲጠይቁ፤ ሌሎች በተቃራኒው በእስር ቤቶች አካባቢ ባደረጉት ሰልፍ "የመድፈር መብትን" ደግፈዋል።

የሰብአዊ መብት ተቋሙ እንዳለው የእስራኤል ባለሥልጣናት የደረሱት ጥቃቶች እና ሞቶች እንዳይመረመሩ "ለመሸፈን" ሞክረዋል።

የፍልስጤማውያኑ ሞት ለቤተሰቦቻቸው እንዳልተነገረ እና አስከሬናቸውም እንዳልተሰጣቸው ሪፖርቱ ያሳያል።

እስራኤላውያን የእስር ቤት ጠባቂዎች እና ወታደሮች ላይ ክስ አልተመሠረተም።

እስራኤል በፖሊሲ ደረጃ "የግዳጅ ስወራ" እንደምትፈጽም እና በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ያለ ቤተሰቦቻቸው ዕውቅና እንደታገቱ በሪፖርቱ ተካትቷል።

ቤተሰቦቻቸው፤ ፍልስጤማውያኑ የት እንደሚገኙ መረጃ አይሰጣቸውም።

በዚህ "ከፍተኛ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት" እስራኤል የፈጸመችው ድርጊት በትክክል እንዳልታወቀ እና የፍልስጤማውያኑ እጣ ፈንታ የከፋ እንደሆነ ጠቁሟል።

የሞቱት ፍልስጤማውያን ቁጥር በሪፖርቱ ከተጠቀሰውም በላይ እንደሚሆን ተገልጿል።

የእስራኤል የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር "እነዚህ ክሶች የእስራኤል እስር ቤትን ድርጊት አይወክሉም" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

በእስራኤል እስር ቤት "የሚከሰት ሁሉም ሞት በተቀመጠው አሠራር መሠረት ምርመራ ይደረግበታል" ሲልም ገልጿል።

"ግላዊ መረጃን ለመጠበቅ፣ ደኅንነት እና ሕግን ለማክበር ሲባል የእስራኤል የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ስለ እስረኞች ሁኔታ መረጃ አይሰጥም" በማለትም አክሏል።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት እና ኦፕሬሽኖቹ "ዓለም አቀፍ ሕግን የሚከተሉ እና በሽብር በተጠረጠሩ የጋዛ ነዋሪዎች ላይ የሚፈጸሙ" እንደሆኑም ገልጿል።

በአንዳንድ ሁኔታዎች "የእስራኤል ሕግን እና የጄኔቫ ስምምነትን በመከተል ለቅድመ ጥንቃቄ ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንደሚውሉ" አክሏል።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት እንዳለው፤ በእስር ቤት ሳሉ የሞቱ ሰዎች እንዲሁም የአካል ጉዳት እና ሕመም የገጠማቸው እንዳሉ መረጃ ደርሶታል።