የዩክሬን አጋሮች በቡድን 20 ስብሰባ ላይ ስለ አዲሱ የአሜሪካ የሰላም ዕቅድ ሊነጋገሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዩክሬን አጋሮች አሜሪካ ከሩሲያ ጋር እየተደረገ ያለውን ጦርነት ለማስቆም ያቀረበችውን ዕቅድ ደቡብ አፍሪካ የቡድን 20 ስብሰባ ላይ ሲገናኙ "ለማጠናከር" እንደሚፈልጉ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ተናገሩ።
የቡድን 20 የመሪዎች ጉባዔ የሚጀምረው ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ ዩክሬን ዕቅዱን እንድትቀበል ግፊት በመደረጉ "በታሪካችን ውስጥ ካሉት በጣም አስቸጋሪ ጊዜያት አንዱ ነው" በማለት ካስጠነቀቁ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ሾልከው የወጡት የዕቅዱ ዝርዝር ነጥቦች ለሞስኮ ያደሉ ናቸው ተብሏል።
ዜሌንስኪ አርብ ዕለት ከሰር ኪር ስታርመር፣ ከፈረንሳይ እና ከጀርመን መሪዎች ጋር በስልክ ተወያይተዋል።
በመቀጠልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዩክሬን "ወዳጆች እና አጋሮች"፤ "ዘላቂ ሰላም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ" ለማረጋገጥ ቁርጠኞች ናቸው ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ሆኑ የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የቡድን 20 አገራት ጉባዔ ላይ አይገኙም።
ሾልኮ የወጣው የአሜሪካ የሰላም ዕቅድ ኪየቭ ቀደም ሲል ውድቅ ያደረገቻቸውን ሃሳቦች ያካተተ ነው። ዩክሬን በአሁኑ ሰዓት የምትቆጣጠረው የአገሪቱን ምሥራቃዊ አካባቢዎችን ለቅቃ እንድትወጣ ይጠይቃል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በቀረቡት ምክረ ሀሳቦች ላይ ለመወያየት ከፍተኛ የፔንታጎን ባለሥልጣናትን ዩክሬን ደርሰዋል።
ነገር ግን ለሞስኮ ያደላ ነው የተባለው የሰላም ዕቅድ በአውሮፓ ከፍተኛ መደናገጥ ፈጥሯል።
የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ካጃ ካላስ የሰላም ዕቅዱ የቀረበበትን ወቅት "በጣም አደገኛ ጊዜ" ብለውታል።
"ሁላችንም ይህ ጦርነት እንዲያበቃ እንፈልጋለን፤ ነገር ግን [ያላስማማን] ጉዳዩን የሚያስቆምበት መንገድ ነው"ሲሉ ለጋዜጠኞች መናገራቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
አክለውም "ሩሲያ ከወረረችው አገር ምንም ዓይነት ስምምነት የማግኘት ሕጋዊ መብት የላትም። በዋናነት በስምምነቱ ነጥቦች ላይ መወሰን የዩክሬን ምርጫ ነው" ብለዋል።
ሰር ኪር ስታርመር በቡድን 20 ጉባዔ ላይ መሪዎች ስለ ዩክሬን ከመወያየታቸው በፊት፤ "ጠረጴዛው ላይ ስለቀረበው ምክረ ሃሳብ ይወያያሉ፤ የፕሬዚዳንት ትራምፕን የሰላም ጥረት በመደገፍ ለቀጣዩ የድርድር ምዕራፍ እንዴት ይህን ዕቅድ ማጠናከር እንደሚቻል ይመልከታሉ" ብለዋል።
በመቀጠልም "በዚህ ጦርነት ዩክሬን ሩሲያ ሕገ ወጥ ወረራዋን እንድታቆም፣ ታንኮቿን ወደ ኋላ እንድትመልስ እና ጠመንጃዋን እንድታስቀምጥ ሳትጠይቅ የቀረችበት ቀን የለም" ብለዋል።
"ዩክሬን ለወራት ለድርድር ዝግጁ ነበረች፤ ሩሲያ ግን ዳተኛ በመሆን ግድያዋን ቀጥላለች። ለዚህም ነው ሁላችንም ከአሜሪካ እና ከዩክሬን ጋር በመሆን ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላምን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስጠበቅ በጋራ መስራት ያለብን" በማለት አቋማቸውን ገልጸዋል።
በዋይት ሐውስ ዕቅድ መሠረት ዩክሬን የጦር ሠራዊቷን ቁጥር የምትቀንስ ሲሆን፣ ክሬምሊን በተደጋጋሚ ስትጠይቀው በነበረው መሰረት የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) ላለመቀላቀል ቃል መግባት አለባት።
ዶናልድ ትራምፕ አርብ ዕለት ዩክሬን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ ግዛትን እንደምታጣ በመግለጽ፣ ዜሌንስኪ ዕቅዱን እንዲያጸድቁ አስጠንቅቀዋል።
ትራምፕ፤ ዩክሬን ዕቅዱ ላይ ለመስማማት እስከ ሐሙስ ጊዜ እንዳላት ተናግረው፤ ይህ "ተገቢ" የሆነ ቀነ ገደብ ነው ብለዋል።
ሩሲያ እንደ አውሮፓውያኑ በ2022 ዩክሬንን ሙሉ ወረራ ከከፈተች በኋላ ኪየቭ ዋሽንግተን በምትሰጣት የደህነንት መረጃ ላይ እንዲሁም ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ላይ ጥገኛ ነች።
ሩሲያ በአሁኑ ጊዜ 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት ትቆጣጠራለች።
ወታደሮቿ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰባቸው ቢነገርም በውጊያ ግንባሮች አዝጋሚ በሆነ ሁኔታ ወደፊት እየገፉ ነው።
ምንም እንኳን ዝርዝር መግለጫ ባይሰጥም ኪየቭ "አስተማማኝ የደህንነት ዋስትናዎች" እንደምታገኝ የሰላም ዕቅዱ ላይ ሰፍሯል።
ሰነዱ አክሎም ሩሲያ ጎረቤቶቿን እንደማትወር "ይጠበቃል" የሚል ሲሆን፣ እንዲሁም ኔቶ ከዚህ በላይ እንደማይስፋፋ ይገልጻል።
ረቂቅ የሰላም ዕቅዱ በተጨማሪም ሩሲያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ በማንሳት እና ወደ ቡድን 7 ዳግም እንድትቀላቀል በማድረግ "ወደ ዓለም ዓቀፉ ኢኮኖሚ" ትዋሃዳለች ይላል።















