"የአሰብ ወደብ ጥያቄን ትክክል እንዳልሆነ ለመቀላመድ መሞከር ባንዳነት ነው" - የመከላከያ ሚኒስቴር

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደራዊ ትርዒት ሲያቀርብ

የፎቶው ባለመብት, PM Office

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ የአሰብ እና የቀይ ባሕር ጥያቄ ትክክል እንዳልሆነ "መቀላመድ"፤ "ባንዳነት" ነው አለ።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቅዳሜ መስከረም 17/2018 ዓ.ም. "ወደን እና ፈቅደን ስለምንሞትላት ኢትዮጵያችን ጠንቅቀን እናውቃለን" በሚል ርዕስ ባሰፈረውና በፌስቡክ ገጹ ላይ ባጋራው መልዕክት የቀይ ባሕር እና የአሰብ ጉዳይ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ "የኢትዮጵያችን ሕመም ሆኖ የታላቅ አገርነቷን ክብር አሳንሷል። የጂኦ ፖለቲካ ብሔራዊ ወሳኝ ጥቅሟን ቀምቷል" ብሏል።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ስለማረጋገጥ የሚያትተው የመከላከያ ሚኒስቴር መልዕክት "የኢትዮጵያ ወታደሮች የቀይ ባሕርን ጥያቄ በዓለም አደባባይ በይፋ መጠየቁ በታላቅ የደስታ ስሜት ሞልቶናል" ብሏል።

የመከላከያ ሚኒስቴር በይፋዊ የፌስ ቡክ ገፁ ላይ ባሰፈረው በዚህ መልዕክቱ ሠራዊቱ "ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መረጋገጥ የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ለሰከንድ እንደማያቅማም" ገልጿል።

ጷግሜ 4፣2017 ዓ.ም. የተመረቀውን የሕዳሴውን ግድብ በመጥቀስ "የቀይ ባሕር ጉዳይም ዕውን የማይሆንበት ምክንያት እንደሌለ በጽኑ እናምናለን" በማለት አቋሙን አሳውቋል።

በመሆኑም "የቀይ ባሕር ብሎም የአሰብ ወደብ ጥያቄን በየትኛውም መነፅር ትክክል እንዳልሆነ ለመቀላመድ መሞከር ከባንዳነት ውጭ አንዳች ውኃ የሚያነሳ አመክንዮ ሊኖረው አይችልም" ሲል መከላከያ ሚኒስቴር መልዕክቱን አስተላልፏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁን አስመልክቶ በብሔራዊ ቴሌቪዥን በተላለፈ ውይይታቸው ላይ ቀይ ባሕር ከሰላሳ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ እጅ እንደነበረ ጠቅሰው "ስህተቱ ነገ ይታረማል" ማለታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ ውይይታቸው ላይ "ቀይ ባሕር እኮ የዛሬ 30 ዓመት እኛ እጅ ነበር። ቀይ ባሕር የዛሬ 30 ዓመት የትናንት ታሪክ ነው። የተፈጠረው ስህተት ትናንትና ነው። ነገ ይታረማል፤ ብዙ ከባድ አይደለም" ነበር ያሉት።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. በተመረቀው የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ግንባታ ዙሪያ ባደረጉት ውይይት ላይ የሺህ ዓመታት የአባይ ታሪክ እንደተቀየረው ሁሉ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት ሁኔታም እንደሚስተካከል ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት ለ66 ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች የወታደራዊ ማዕረግ እድገት የሰጠች ሲሆን ይህንን በማስመልከት ለኢትዮጵያ የዜና አገልግሎት ማብራሪያ የሰጡት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄነራል ጌትነት፣ ሠራዊቱ እንደ "በውሃ የመጠቀም መብት" እና "የወደብ ጥያቄ" ያሉ ብሔራዊ ጥቅሞችን በማስከበር ሂደት ውስጥ ሊከሰት ለሚችል "የደኅንነት አጣብቂኝ" መዘጋጀት አለበት ብለዋል።

ኤርትራ ነጻነቷን ስታገኝ ከቀይ ባሕር የተነጠለችው ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት እንዳላት ይፋ ካደረጉ በኋላ በኤርትራ በኩል ስጋት ተፈጥሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስለባሕር በር እና ስለወደብ ያሳዩት ፍላጎት እና ያደረጓቸው ንግግሮች የኤርትራ ባለሥልጣናትን አላስደሰተም።

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ጦሮቻቸውን በጋራ ያዘመቱት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነታቸው የተቀዛቀዘው የፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረምን ተከትሎ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "የባሕር በር ለኢትዮጵያ የኅልውና ጉዳይ ነው" ማለታቸውን ተከትሎ ደግሞ የሁለቱ አገራት ግንኙነት የበለጠ ሻክሯል።

ከዚያ በኋላም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በሕዳሴ ግድብ ውዝግብ ውስጥ ከምትገኘው ግብፅ ጋር ትብብር መፍጠሯን ተከትሎ ውጥረቱ ተባብሷል።

ከዚህ ቀደም የባሕር በር ጉዳይ የኅልውና ጉዳይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ስትል የመዋጋት ፍላጎት እንደሌላት ተናግረው ነበር።

ኤርትራ ግን በተቃራኒው ኢትዮጵያን በጠብ አጫሪነት የወነጀለች ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ "ሉዓላዊ የባሕር በር" ማግኘት የሚለው ትኩረት መሳቢያ ሌላ ጂኦፖለቲካዊ ገጽታዎች አሉት በማለት ከዚህ ግድየለሽ ጀብደኝነት ጀርባ ሌሎች ኃይሎች አሉ በማለት ከስሰው ነበር።

ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ "የመልክዓ ምድር እስረኛ" ሆና አትቀጥልም ማለታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ "አይቀሬ" መሆኑን የተናገሩት ዐቢይ አሕመድ፤አገራት "በፈጠነ ጊዜ ራሳቸውን ለድርድር ዝግጁ" እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቋ ግን የባሕር በር የሌላት አገር የሆነችው ከ30 ዓመት በፊት ኤርትራ ነጻ መውጣቷን ተከትሎ ነው።

ከዚያ በኋላ አገሪቱ ለገቢ እና ለወጪ ንግዷ የትንሿን ጎረቤት አገር ጂቡቲን ወደብ በመጠቀም ላይ ትገኛለች።