የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአገሪቱ የኒውክሌር ተቋማት ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን አመኑ

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቅርቡ በአሜሪካ እና በእስራኤል የቦምብ ጥቃት የአገሪቱ የኒውክሌር ተቋማት "ከመጠን በላይ እና ከባድ" ጉዳት እንደደረሰባቸው አመኑ።

አባስ አራግቺ ሐሙስ ምሽት ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የጉዳቱ መጠን በኢራን የአቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት መገምገሙን ተናግረዋል።

ከጥቂት ሰዓታት በፊት ግን የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኒ ጥቃቱ የአሪቱን የኒውክሌር መርሃ ግብር አላስተጓጉልም ብለዋል።

ኻሜኒ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በጥቃቱ ሦስቱ የኒውክሌር ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ሲሉ ለተናሩት የሰጡት ምላሽ ነበር።

ኻሜኒ የአሜሪካ ጥቃቶች "ምንም ጠቃሚ ነገር ማከናወን አልቻሉም" ብለዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሰኔ 13 እስራኤል ኢራንን ማጥቃት ከጀመረችበት ዕለት አንስቶ ተደብቀው የሚገኙት ጠቅላዩ መሪ፣ ትራምፕ የቦምቡን ተፅዕኖ "አጋንኖታል" በማለት በአሜሪካ እና በእስራኤል ላይ ድል እንዳደረጉ ተናግረዋል ።

የአራግቺ አስተያየት ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአሜሪካ ጋር የኒውክሌር ድርድርን ለመቀጠል ምንም ዕቅድ እንደሌለ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢራን የእስራኤል ጥቃት ተከትሎ ሊካሄድ የነበረውን ስድስተኛ ዙር ድርድር ሰርዛለች።

"አዲስ ድርድር ለመጀመር ስምምነት፣ ዝግጅት ወይም ውይይት እንዳልተደረገ በግልፅ መናገር እፈልጋለሁ።"

አክለውም መንግሥት "የኢራን ሕዝብ ጥቅም" ምንድን ነው የሚለውን እየፈተሸ መሆኑን ገልፀው የዲፕሎማሲው አካሄድ "አዲስ መልክ" እንደሚይዝ ተናግረዋል ።

ምን ለማለት ፈልገው እንደሆነ ግን አላብራሩትም።

ኢራንን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ለማገዝ የትራምፕ አስተዳደር አገሪቱ የ30 ቢሊየን ዶላር እርዳታ እንድታገኝ እና ኃይል ማመንጨት የሚያስችል የኒውክሌር መርሃ ግብር መገንባት እንድትጀምር፣ ማዕቀቡን ለማላላት እና የተያዘባትን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መልቀቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየቱን ሲኤንኤን ዘግቧል።

ነገር ግን በኢራን ውስጥ እየታዩ ያሉ ለውጦች እንዲህ ያለውን እርምጃ ሊያደናቅፉ ይችላሉ።

ረቡዕ እለት የኢራን ፓርላማ ከዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ድርጅት እና ከዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር ያለውን ትብብር የሚያቆም ረቂቅ ሕግ አጽድቋል።

ይህ ሕግ ተግባራዊ ከሆነ ኢራን ከአሁን በኋላ የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎችን ወደ ተቋማቷ እንዲገቡ አትፈቅድም ማለት ነው።

እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸመችው ጥቃት የኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ የማልማት ዕቅድን ለማክሸፍ አስፈላጊ ነበር ስትል ተናግራለች።

ኢራን ሁልጊዜ የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ የታሰበ እንደሆነ አበክራ ትናገራለች።

ባለፈው ሳምንት አሜሪካ የኢራን ሦስት የኒውክሌር ተቋማትን ፎርዶን፣ ናታንዝ እና እስፋሃንን በማጥቃት ተቀላቅላለች።

ከዚያ በኋላ ፕሬዚደንት ትራምፕ በእስራኤል እና ኢራን መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርስ ወዲያውኑ አሸማግለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግሴዝ እንዳሉት በአሜሪካ እና በእስራኤል የተሰበሰቡ መረጃዎች ጥቃቱ "የኒውክሌር መርሃ ግብሩን በእጅጉ በመጎዳቱ ለዓመታት ወደኋላ እንዲመለስ አድርጓል" ብለዋል።

ከፔንታጎን ሾልኮ የወጣ የመጀመሪያ ደረጃ የግምገማ ሪፖርት ግን የጉዳቱን መጠን አሳንሶ የአሜሪካ ጥቃቶች የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ወደ ኋላ እንዲመለሱ ማድረግ የቻለው በጥቂት ወራት ብቻ ነው ብሏል።

የትራምፕ አስተዳደር ሾልኮ የወጣውን መረጃ ውድቅ አድርጓል።

የኢራን የጤና ሚኒስቴር በእስራኤል በ12 ቀናት የአየር ጥቃት 610 ሰዎች መሞታቸውን የገለፀ ሲሆን፣ የእስራኤል ባለሥልጣናት ደግሞ በኢራን ጥቃት 28 ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል።