ኔታንያሁ ጋዛን በሙሉ የመውረር ዕቅዳቸውን ለጸጥታ ካቢኔያቸው ሊያቀርቡ ነው-ሪፖርት

ቤንያሚን ኔታንያሁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የጋዛ ሰርጥን በሙሉ በድጋሜ የመውረር ዕቅዳቸውን ለጸጥታ ካቢኔያቸው ሊያቀርቡ እንደሆነ የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

"ውሳኔው ተወስኗል። የጋዛ ሰርጥን በሙሉ ለመቆጣጠር እና ሃማስን ለማሸነፍ ነው የምንሄደው" ሲሉ አንድ የእስራኤል ከፍተኛ ባለስልጣን መናገራቸውን የሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች ዘግበዋል።

የአገሪቱ ኤታማዦር ሹም እና ሌሎች ወታደራዊ አመራሮች ይህንን እቅድ ይቃወማሉ የሚሉ ዘገባዎችን በተመለከተ ይህ ስማቸው ያልተጠቀሰው ባለስልጣን ሲመልሱ" ይህ እቅድ ለጦር አዛዡ የማይሰራ ከሆነ ስራውን መልቀቅ አለበት ብለዋል።

የታጋቾች ቤተሰቦች እንዲህ አይነት እቅዶች የቤተሰቦቻቸውን ህይወት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ብለው ይሰጋሉ።

በአሁኑ ወቅት ከ20- 50 ታጋቾች በጋዛ በህይወት አሉ ተብሎ የሚታመን ሲሆን፤ ታጋቾችን ለመመለስ የተኩስ አቁም ስምምነትን ማድረግ ከአራት እስራኤላውያን ሶስቱ እንደሚመርጡት በቅርቡ የተሰበሰበ የህዝብ አስተያየት ጠቁሟል።

በርካታ የእስራኤል የቅርብ አጋሮች በጋዛ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ እንዲቃለል ጦርነቱ እንዲቆም እየጠየቁ ሲሆን እስራኤል ይህንን እርምጃ የምትወስድ ከሆነ ውግዘት ይጠብቃታል።

ሰሞኑን እየወጡ ያሉ የሚዲያ ሪፖርቶች ሐማስ አዲስ ስምምነት እንዲቀበል ለማስገደድ የሚደረግ የጫና ስትራቴጂ ነው የሚሉ መላምቶች ተሰጥተዋል።

የእስራኤል ጦር 75 በመቶውን የጋዛን ሰርጥ ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ነገር ግን በታቀደው መሰረት መላውን ጋዛን እንደገና የሚጠቀልል ከሆነ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ፍልስጤማውያን የተሰባሰቡባቸውን አካባቢዎች ይይዛል።

ይህ ጋዛን በሙሉ የመውረር ዕቅድ የፍልስጤማውያኑ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚለውን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።

በዚህ አውዳሚ ጦርነት ከ2.1 ሚሊዮን ከሚሆነው የጋዛ ህዝብ መካከል 90 በመቶ ወይም 2.1 ሚሊዮን ህዝብ ተፈናቅሏል። አንዳንዶች በተደጋጋሚ ሲሆን የተናፈናቀሉት በርካታዎቹ በተጨናነቀ እና በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚኖሩት።

የእስራኤል ጦር በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን በሙሉ አፈናቅሎ በደቡባዊ ክፍል በሚዘጋጅ ካምፕ ለማስገባት እቅድ እንዲያዘጋጅ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ትዕዛዝ መስጠታቸውን ከዚህ ቀደም ተዘግቦ ነበር።

በራፋህ ከተማ ፍርስራሽ ላይ ይቋቋማል የተባለው ይህ ካምፕ በመጀመሪያ 600 ሺህ ፍልስጤማውያን

በመቀጠልም አጠቃላይ የጋዛን ህዝብ፣ 2.1 ሚሊዮን የሚያኖር እንደሆነ ተገልጾ ፍልስጤማውያኑ ከካምፑ መውጣት እንደማይፈቀድላቸው ተገልጿል።

የእስራኤል ጦር ማዕከላዊ ጋዛን ጨምሮ አንዳንድ የጋዛ አካባቢዎችን ሙሉ በሙሉ ከመቆጣጠር የታቀበው እዚያ ያሉ ታጋቾች አሉ በሚል እንደሆነ ተገልጿል።

እስራኤል በወረራ በያዘቻት ዌስት ባንክን የተወሰኑ ግዛቶች የሚያስተዳድረው የፍልስጤም አስተዳደር የእስራኤልን እቅድ አውግዘው ይህንን የወረራ እቅድ ለመከላከል አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀዋል።

ቀኝ አክራሪ የእስራኤል ሚኒስትሮች ጋዛን በሙሉ በመጠቅለል አዲስ የአይሁድ ሰፈራዎችን የመገንባት ፍላጎታቸውን በግልጽ መሟገታቸውን ፍልስጤማውያን ሲናገሩ ቆይተዋል።

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ያለውን ሰፈራ በማፍረስ በአውሮፓውያኑ 2005 ጦሯን አስወጥታ ነበር።

ሆኖም ከግብጽ ጋር በጋራ በመሆን የጋዛን ጸጥታና መዳረሻ ተቆጣጥራ ትገኛለች። ይህ የእስራኤል እንደገና የመጠቅለል እቅድ የተሰማው ለአስርት ዓመታት የቀጠለውን የእስራኤልና ፍልስጤም ጦርነት እልባት ለመስጠት የሁለት ግዛት መፍትሄ ሃሳቦች እንደገና እየቀረቡ ባሉበት ወቅት ነው።

የፍልስጤም አገር ምስረታ እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው ዌስት ባንክና ምስራቅ እየሩሳሌምን ጨምሮ ጋዛን ያካተተ ዕቅድ ነው።

እስራኤል በአገርነት፣ በአውሮፖውያኑ 1948 ስትመሰረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ያፈናቀለች ሲሆን ይህንንም "ናቅባ" (ትልቁ እልቂት) ሲሉ ይጠሩታል።

በአሁኑ ወቅትም ፍልስጤማውያኑ ይኸው ይደገማል በሚል ፍራቻ ላይ ናቸው።

ከቀያቸው የተፈናቀሉት ፍልስጤማውያኑ አብዛኛዎቹ በጋዛ ሰፍረዋል።

በአሁኑ ወቅት ካሉ የጋዛ ነዋሪዎች መካከል ሶስት አራተኛውን የሚይዙት በዚያን ወቅት የተፈናቀሉ የልጅ ልጆች ናቸው።

ሌሎች 900 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አሁን እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ ይኖራሉ።

3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በዮርዳኖስ፣ ሶሪያ እና ሊባኖስ እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።

እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 በተደረገው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ነው የፍልስጤማውያኑ ግዛት የሆኑትን ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን የተቆጣጠረችው።

ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ለ700 ሺህ አይሁዳውያን መኖሪያ የሚሆኑ 160 ሰፈራዎችን ገንብታለች። በዌስት ባንክ 3.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ይኖራሉ።

አብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እስራኤል እያደረገችው ያለውን ሰፈራ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ነው ሲል ይኮንናል።

እስራኤል ይህንን አትቀበልም።

በእስራኤል በተከታታይ የመጡ አስተዳደሮች ሰፈራዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል።

ይሁን እንጂ ሰፈራን የሚደግፈው የቅኝ ክንፍ አክራሪ ጥምረት የሆነውን መንግሥት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድጋሚ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሰፈራዎች እየተስፋፉ ይገኛሉ።

የጋዛ ጦርነትም እንዲሁ ለእነዚህ ሰፈራዎች መጨመር በር መክፈቱም ተነግሯል። ሰፈራዎች መስፈፋት ብቻ ሳይሆን ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያኑ ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች መባባሱም ተገልጿል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ የጋዛ ጦርነት ከተነሳ ጀምሮ በዌስት ባንክ ቢያንስ 975 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጸጥታ ኃይሎች እና በእስራኤል ሰፋሪዎች ተገድለዋል።