የሩሲያ ባለሥልጣናት ፑቲን እና ዜሌንስኪ ሊገናኙ ይችላሉ መባሉን አጣጣሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የክሬምሊን ባለሥልጣናት፤ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በቅርቡ ሊገናኙ እንደሚችሉ የቀረበውን ገለጻ አጣጣሉ።
ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ሁለቱ መሪዎች በዩክሬን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት መቋጨት ያለመ ውይይት ለማድረግ እንዲገናኙ የሚያቀርቡትን ጥሪ አጠናክረው ቀጥለዋል።
ሁለቱ መሪዎች እንዲገናኙ የሚደረገው ግፊት የመጣው ባለፈው ሳምንት ትራምፕ እና ፑቲን በአላስካ ከተገናኙ እንዲሁም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሰኞ ዕለት ዜሌንስኪ እና ሰባት የአውሮፓ መሪዎችን በዋይት ሐውስ ከተቀበሉ በኋላ ነው።
የግጭቱ መቋጨት "ከባድ" መሆኑን ያመኑት ትራምፕ፤ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ግጭቱን የማቆም ፍላጎት ላይኖራቸው እንደሚችልም ገልጸዋል።
"የፕሬዝዳንት ፑቲንን [አቋም] በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ እናውቃለን" ሲሉ ማክሰኞ ዕለት ተናግረዋል። "ስምምነት ላይ መድረስ ላይፈልግ የሚችልበት ዕድል አለ" ሲሉም ተደምጠዋል።
ትራምፕ በዝርዝር ባይናገሩም፤ ጉዳዩ ይህ ከሆነ ፑቲን "ከባድ ሁኔታ" ይገጥመዋል ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ማክሰኞ ምሽት ከወግ አጥባቂው የራዲዮ ፕሮግራም አቅራቢ ማርክ ሌቪን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ፑቲን እና ዜሌንስኪ እርሳቸው በሌሉበት ቢገናኙ "የተሻለ እንደሚሆን" ገልጸዋል።
አክለውም "አስፈላጊ ከሆነ" የሁለቱ መሪዎች ስብሰባ ላይ እንደሚገኙ፤ አሁን ግን "ምን እንደሚከሰት ለማየት" እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ከዩክሬን መሪ ጋር በቀጥታ ለመወያየት ሀሳብ "ክፍት" መሆናቸውን ሰኞ ዕለት ለትራምፕ ቢገልጹም፤ በቀጣዩ ቀን ግን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ቀድሞውኑም በግልጽ ያልቀረበውን የፈቃደኝነት ጉዳይ አቃልለው አቅርበውታል።
ማንኛውም ስብሰባ "ደረጃ በደረጃ... በባለሙያዎች ደረጃ ጀምሮ እና ከዚያ በኋላ ሁሉንም አስፈላጊ እርምጃዎች" በማለፍ መካሄድ አለበት ሲሉ በተደጋጋሚ በክሬምሊን የሚቀርበውን አቋም ደግመዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የሩሲያ ምክትል ተወካይ የሆኑት ዲሚትሪ ፖሊያንስኪ በበኩላቸው ቀጥታ የሚደረግ ውይይትን "ማንም አልተቃወም"፤ "ነገር ግን ስብሰባ ለማካሄድ ሲባል ብቻ ስብሰባ መደረግ የለበትም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኔቶ ወታደራዊ አዛዦች ዛሬ ረቡዕ በኦንላይን ስብሰባ ያደርጋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የብሪታንያ ወታደራዊ አዛዥ አድሚራል ቶኒ ራዳኪን ደግሞ በዩክሬን ውስጥ መረጋጋት ለመፍጠር ኃይል የሚሰማራበትን ሁኔታ በተመለከተ ውይይት ለማድረግ ወደ ዋሽንግተን ተጉዘዋል።
ማክሰኞ ዕለት ፑቲን፤ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ወደ ሞስኮ በመሄድ ውይይት እንዲደረግ ለትራምፕ ሀሳብ ማቅረባቸው ተዘግቧል። ይህ ዓይነቱ ሀሳብ ግን ዩክሬን የምትቀበለው አይደለም።
ሩሲያ ይህንን ሀሳብ ያቀረበችው ከዩክሬን አቋም እጅጉን የራቀ አማራጭ በማቅረብ ኪየቭ እንዳትስማማ ለማድረግ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት የተደረጉት ውይይቶች፤ ትራምፕ የጦርነቱን ውስብስብነት እንዲሁም በሞስኮ ጥያቄዎች እና በኪየቭ አቋም መካከል ያለውን ልዩነት እንዲገነዘቡ ያደረጋቸው ይመስላል።
ትራምፕ እንደሚያሳኩት ሲገልጹ የነበረውን ተጠባቂ የተኩስ አቁም ስምምነት እውን ማድረግ አልቻሉም። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት አሁን ዩክሬን እና ሩሲያ ከተኩስ አቁም ይልቅ በቀጥታ ዘላቂ የሰላም ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው ብለዋል።
ለዩክሬን የሚሰጠውን የደኅንነት ዋስትናን በተመለከተ ግን የተወሰነ መሻሻል ታይቷል።
ዜሌንስኪ እና የአውሮፓ መሪዎች የደኅንነት ዋስትና መስጠት የሰላም ስምምነት በሚኖርበት ጊዜ ለኪየቭ ሉዓላዊነት ወሳኝ እንደሚሆን ትራምፕን ያሳመኗቸው ይመስላል።















