ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሳውዝአፕተን እና የአስቶንቪላ ጨዋታ በድሮን ምክንያት ለ10 ደቂቃዎች ተቋረጠ
በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ትላንት ቅዳሜ የተካሄደው የሳውዝአምፕተን እና የአስቶንቪላ ጨዋታ አንዲት ድሮን ስቴዲየሙ ውስጥ በመገኘቷ ምክንያት ለደቂቃዎች ተቋረጦ ነበር።
የእግር ኳስ ቡድኖቹ ሴንት ሜሪ በተባለው ስታዲየም ጨዋታቸውን እያከናወኑ ባሉበት ጊዜ ከእረፍት በፊት ድሮን በስታዲየሙ ሰማይ ስር ማንዧበቧ ከታወቀ በኋላ ጨዋታው ለደቂቃዎች ተቋርጧል።
የዕለቱን ጨዋታ በመሃል ዳኝነት የመሩት ማይክል ሳልስበሪ በሳውዝአምፕተን የግብ ክልል አካባቢ እያንዣበበ እንደሆነ ከተነገራቸው በኋላ ጨዋታውን ለማቋረጥ እና ተጨዋቾች ከሜዳ እንዲወጡ ለማዘዝ ተገደዋል።
ፖሊስ ነገሮች ሰላማዊ መሆናቸውን ካረጋገጠ እና ምንም ችግር እንደሌለ ከገለጸ በኋላ ለ10 ደቂቃዎች ተቋረጦ የነበረው ጨዋታ መልሶ ተጀምሯል።
በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት የውድድር ዘመን ብሬንትፎርድ እና ዎልቭስ ሲያደርጉት የነበረው ጨዋታ ተቋርጧ ነበር።
በወቅቱ የመሃል ዳኛ የነበሩት ፒተር ባንከስ ብሬንትፎርድ ሳታዲየም ድሮን መታየቱን ተከትሎ ጨዋታውን አቋርጠው ተጨዋቾች ከሜዳ እንዲወጡ አድርገው ነበር።
የዚያን ጊዜ ጨዋታው እንዲቋርጥ እና ተጨዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል እንዲመለሱ የመሃል ዳኛው ሲያዙ ዳጋፊዎች ግራ ተጋበተው ነበር።
ሆኖም ከደቂቃዎች በኋላ ጨዋታው በድሮን ምክንያት እንደተቋረጠ ለደጋፊዎች ተነግሯል።
ተጨዋቾች ዘለግ ላለ ጊዜ ከእንቅስቃሴ ውጪ ሆነው ስለነበር በድጋሚ አሟሙቀው ለ15 ደቂቃ የተቋረጠው ጨዋታ መልሶ ተጀምሯል።
በመጀመሪያው አጋማሽ በነበረው የከፋ የተጨዋቾች ግጭት ጨዋታው ቆሞ የነበረ ሲሆን ይህ ከሆነ ከስድስት ደቂቃ በኋላ ነው በድሮን ምክንያት ጨዋታው ዳግም የተቋረጠው።
በዚህም ምክንያት ለጨዋታው ከተያዘለት ጊዜ ባሻገር 19 ደቂቃዎች ተጨምሮ ጨዋታው በዎልቭስ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ቅዳሜ ጥር 13/2015 ዓ.ም. በተካሄደው እና በድሮን ምክንያት በተስጓጎለው ጨዋታ ደግሞ አቶን ቪላ ሳውዝአምፕተንን አንድ ለምንም ረቷል።
በሴንት ሜሪ ስትዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኦሌ ዋትኪንስ ከድሮኑ ክስተት በኋላ በጭንቅላት ያስቆጠራት ግብ ሳውዝአምፕተን በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የደረጃ ሰነጠረዥ ላይ ከታች እንዲቆይ አስገድዶታል።
ፎቶግራፍ ማንሳትን እና ቪዲዮዎችን መቅረጽን ጨምሮ ለተያዩ ተግባራት ጥቅም ላይ የሚውሉት ድሮኖች የደኅንነት ስጋትም እየሆኑ ነው።
ድሮኖች በአሸባሪዎች ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ ስላለ የተለያዩ አገራት የፀጥታ አካላት የድሮኖች እንቅስቃሴን በጥርጣሬ ይመለከታሉ።