በቀላሉ ለጉዳት ተጋላጭ የሆነውን ዐይናችንን እንዴት መንከባከብ እንችላለን?

የዐይን ህመም የሌለባቸው ሰዎች የዐይን እንክብካቤ እምብዛም ላያሳስባቸው ይችላል።

የዐይን ህመም ላለባቸው ሰዎች ግን የዘወትር ጉዳይ ነው።

የዐይን ሕክምና ባለሙያ ሳራ ሜሊንግ “ዐይናችንን ከእንቅልፍ ከተነሳንበት ሰዓት አንስቶ ተመልሰን እስክንተኛ እንገለገላለን። የልባችንን ያህል ነው የሚጠቅሙን” ትላለች።

ስንሮጥ ልባችን በፍጥነት ይመታል። ስለዚህ ዝግ እንላለን። “ነገር ግን ዐይናችን ስለደከመው ማየት አናቆምም” ትላለች ሳራ።

ጨምራም “ዐይናችንን ስለመታከም አብዝተንም አናስብም” በማለት ለዐይናችን ጤና ቸልተኛ መሆናችንን ትገልጻለች።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ዐይነ ስውርነትን ለመከላከል የሚሠራው ተቋም ዋና ኃላፊ ፒተር ሆላንድ “ዐይንን መንከባከብ ጠቃሚ እንደሆነ ሰዎች እንዲያውቁ እንሻለን” ይላል።

ሉሲ ኦወን የቢቢሲ ጋዜጠኛ ናት። መደበኛ የዐይን ምርመራ አድርጋ ዐይኗን አድናለች።

ከ16 ዓመቷ ጀምሮ ኮንታንክት ሌንስ ታደርግ ነበር። አሁን በ50ዎቹ ዕድሜ ናት።

በቀኝ ዐይኗ አማካይነት ነጭ ብርሃን መሰል ይታያት እንደጀመረ አስተዋለች።

“ብዙ አይከሰትም ነበር። በቀን ሁለት ሦስቴ ነበር የሚገጥመኝ። ያልተለመደ ስለሆነ ተመረመርኩ። 52ኛ ዓመት ልደቴ እየደረሰ ነበር። ምናልባት ከእርጅና ጋር ተያይዞ የመጣ ይሆናል ብዬ አሰብኩ” ትላለች።

ዓመታዊ ምርመራ ማድረግ ትዘነጋ እንደነበር ታስታውሳለች። በስተመጨረሻ ዐይን ሐኪም ጋር ስትሄድ የቀኝ ዐይኗ ረቲና እየተላቀቀ እንደሆነ ተነገራት።

ነጭ ብርሃን መሰል ማየቷ የዚህ ምልክት ነበር። በአፋጣኝ የ40 ደቂቃ ቀዶ ሕክምና ተደረገላት።

በተከታዩ ሳምንትም ዐይኗ እስከሚያገግም ጠበቀች። ዕይታዋም ቀስ በቀስ ተሻሻለ።

አሁን ወደ ሥራ ተመልሳለች።

“ምን ያህል ዕድለኛ እንደሆንኩ ነው የማስበው። በፍጥነት ቀዶ ሕክምና በማድረጌ ዕድለኛ ነኝ” ትላለች ሉሲ።

የዐይን ጤና ጉዳይ ሲታሰብ ከሚነሱ ነጥቦች መካከል አንዱ የዐይን ሕክምና የማግኘት ዕድል ነው።

ሉሲ ያገኘችው ዓይነት ጥሩ የዐይን ሕክምና ማግኘት ለበርካቶች ቀላል አይደለም።

ፒተር እንደሚለው ከዐይን ሕክምና ጋር በተያያዘ በአነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ አገራት ብሔራዊ ዕቅድ ያስፈልጋል።

“የዐይን ሕክምና በብሔራዊ ሕክምና ውስጥ መካተት አለበት። በዚህ መንገድ ከአጠቃላይ የጤና ሥርዓት ጋር መዋሃድ ይችላል። ሕክምናውን የሚፈልጉም ማግኘት ይችላሉ” ይላል።

ከዓለማችን ሕዝብ መካከል 2.2 ቢሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የዕይታ ችግር አለባቸው ወይም ዐይነ ስውር ናቸው።

ከእነዚህ በተጨማሪ ደግሞ 1.1 ቢሊዮን ሰዎች ሊታከም የማይችል የዐይን ህመም እንዳለባቸው ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ተቋም ባወጣው ሪፖርት ተጠቅሷል።

“የዐይን ህመምን መከላከያ መንገዶች ካልተተገበሩ ይህ ቁጥር ይጨምራል። በተለይም ደግሞ በአነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ አገራት በሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች እና ቀደምት ማኅበረሰቦች” ይላል።

ዓለም አቀፉ የዕይታ ደኅንነት ተቋም ሁሉም ሰው ለዐይን እንክብካቤ አስተዋጽኦ እንዳለው ይገልጻል፤ በተለይም በሥራ ቦታ።

በአውሮፓውያኑ 2020 ወደ 13 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ በሥራ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ለዕይታ ችግር እንደተዳረጉ ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ተቋም ይገልጻል።

“ከዕይታ ጋር በተያያዘ ከሚገጥም ችግር መካከል የሥራ ሁኔታ ለዐይን ህመም አጋላጭነት ከሆኑ ምክንያቶች ሦስተኛውን ደረጃ ይይዛል” ይላል።

ከሥራ ጋር በተያያዘ ለዕይታ አደጋ የሚሆኑ ተብለው ከተጠቀሱ መካከል የሚታይ ወይም የማይታይ ብርሃን፣ ለዩቪ እና ለኢንፍሬድ ጨረር መጋለጥ ይጠቀሳል።

በግብርና፣ በደን ጥበቃ፣ በግንባታ፣ በዓሣ ማርባት እና በመሳሰሉ መስኮች ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችም ተጋላጭ ናቸው።

የወጣው ሪፖርት እንደሚለው፣ የተለያዩ ቁሳቁሶች ዐይን ውስጥ ሊገቡ በሚችሉባቸው ወይም ከፍተኛ ሙቀት በሚፈጠርባቸው የሥራ ዘርፎች ዐይን መጠበቂያ (መከላከያ መነጽር) ሊኖር ይገባል።

የዚህ ዘመን የሥራ ቦታ ዋነኛ ችግር ከሚባሉት መካከል ኮምፒውተር ወይም ላፕቶፕ ላይ ዘለግ ላለ ጊዜ በመቆየት የሚመጣ የዐይን መድከምሌላው የዕይታ ጠየና ጠንቅ ነው።

“በስክሪን እና በዐይን መካከል ሰዎች ርቀት ሳይፈጥሩ ሲቀሩ የዐይን ጡንቻ በዘላቂነት አለመቀጠል ይፈጠራል” ይላል ሪፖርቱ።

ይህም ለዕይታ ችግር እንደሚዳርግ ተጠቅሷል።

ዐይንን እንዴት መንከባከብ ይቻላል?

በአነስተኛ ወጪ ዐይንን መንከባከብ የሚቻልባቸውን መንገዶች እንመልከት።

የዐይን ሕክምና ባለሙያ ሳራ ሜሊንግ ዕይታን ለመጠነቅ መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎችን በተመለከተ ቀጣዩቹ ነጥቦች ተግባራዊ ማድረግን ትመክራለች።

  • በዓመቱ ልደትዎን ሲያከብሩ ዐይንዎን መንከባከብን ያስታውሱ።
  • ዐይንዎ ደኅና መሆኑን ለማወቅ፡ አንድ ቦታ ላይ ሁለቱንም ዐይንዎን ተክለው ይመልከቱና ከዚያ ደግሞ አንዱን ዐይንዎን ጨፍነው እዚያው ቦታ ይመልከቱ። በሁለት ዐይን ሲያዩ እና በተለያየ ዐይንዎ ለየብቻ ሲመለከቱ ልዩነት ካለ ወደ ሐኪምዎ ይሂዱ።
  • ዋናው የዐይን መንከባከቢያ መንገድ ዐይንን ከህመም መጠበቅ ነው።
  • ከሰባት ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ካለዎት እና ወደ ሕክምና መውሰድ ካልቻሉ፡ ራቅ ያለ ቦታ እንዲያዩ አድርገው በሁለቱም ዐይናቸው ማየት ይችሉ እንደሆነ ያረጋግጡ። በዚህም እንደ አምብሊዮፒያ ያሉ ሕመሞች ካሉባቸው ማወቅ ይቻላል።