አልሸባብ በሶማሌ ክልል ስለፈፀማቸው ጥቃቶች የምናውቃቸው አምስት ነጥቦች

እንደሌሎቹ የሶማሊያ ጎረቤት አገራት ሁሉ አልሻባብ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ፍላጎቱ ቢኖረውም እስካሁን ከሙከራ ባሻገር ይህ ነው የሚባል ጥቃት አላደረሰም።

ነገር ግን ከሳምንት በፊት የእስላማዊ ቡድኑ ታጣቂዎች ለቁጥጥር አስቸጋሪ በሆነውና ረጅሙ የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ ድንበር በኩል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ታጣቂዎቹን በማስገባት ጥቃት ሰንዝሯል።

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቀው ከገቡ የአልሻባብ ታጣቃዎች ጋር ካለፈው ሳምንት ረቡዕ ጀምሮ በተለያዩ የድንበር አካባቢዎች ላይ መዋጋታቸውን የክልሉ መንግሥት ገልጿል።

አልሻባብም ጥቃት መሰንዘሩን ባለፈው ሳምንት ገልጾ የነበረ ሲሆን፣ ቢቢሲ የአካባቢውን ነዋሪዎች አነጋግሮ ማረጋገጥ እንደቻለው በአልሸባብ እና በክልሉ ልዩ ኃይሉ መካከል ውግያ ሲካሄድ ነበር።

ጥቃቱ የተፈፀመው ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንባቸው የድንበር ከተሞች ላይ ሲሆን በሁለቱም ወገኖች ዘንድ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት መድረሱን በወቅቱ ተዘግቦ ነበር።

አልሸባብ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜው ውስጥ በተከታታይ ስለፈፀማቸው ጥቃቶች ምን እናውቃለን?

1 - አልሸባብ ዳግም ጥቃት መሰንዘሩ

ሰኞ ሐምሌ 18/2014 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በሶማሌ ክልል ከፌርፌር ወረዳ ብዙም ሳይርቅ በሚገኘው ላስቁሩን በተባለ ስፍራ የልዩ ኃይል አባላት ከሶማሊያው እስላማዊ ቡድን ታጣቂዎች ጋር መዋጋታቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ሶማሊኛ ተናግረዋል።

የሶማሌ ክልል መስተዳደር ሰኞ ሐምሌ 18/2014 ዓ.ም. ሐመእለእንዳሳወቀው የክልሉ ልዩ ኃይል “ዳግም ድንበር አቋርጦ ለመግባት የሞከረው” ያለው የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን መደምሰሱን ገልጿል።

የአልሻባብ ታጣቂዎች ከአጎራባች ሶማሊያ ሂራን ግዛት ተነስተው ድንበር በማቋረጥ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን ፌርፌር ወረዳ ለመግባት እንደሞከሩና በልዩ ኃይሉ ኤል ቁዱን በሚባል ቦታ ላይ በተደረገ ውጊያ መመታቱን አመልክቷል።

ክልሉ እንዳለው በዚህ ውጊያ ከተገደሉት በተጨማሪ በርካቶች መማረካቸውን እንዲሁም የጦር እና የመገናኛ መሣሪያዎች መያዛቸው ተነግሯል።

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ባለፉት ቀናት በበርካታ መኪኖች የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው ከገቡት የአልሻባብ አባላትን ጋር ተዋግተው በርካታ የቡድኑን አባላት መግደላቸውን ገልጸው ነበር።

ስለሰኞ ዕለቱ ውጊያ ከአልሻባብ በኩል የተባለ ነገር የለም።

2 - በጥቃቱ የደረሰ ጉዳት

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት የአልሸባብ ታጣቂዎች ከሶማሊያ ተሻግረው ወደ የኢትዮጵያ ግዛት ሲገቡ፣ በሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ውስጥ ውጊያ ተደርጎ በርካታ የአልሻባብ አባላት መገደላቸው ተገልጿል።

የተቀሩት ደግሞ የክልሉ ልዩ ኃይል በሐረገሌ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው ሁልሁል በተባለው ስፍራ መከበባቸውን ቢቢሲ በወቅቱ ዘግቦ ነበር።

ለሦስት ቀናት በአልሻባብ እና በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል መካከል በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በተካሄደው ግጭት ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ በርካታ ተዋጊዎች መገደላቸው እና ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን ተነግሯል።

ስለጥቃቱ የፌደራል መንግሥቱና የሶማሌ ክልል መስተዳደር ምንም ባላሉበት ወቅት የአልሸባብ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ቃል አቀባይ አብዱያሲስ አቡ ሙሳብ በሶማሊያ ውስጥ ሁለት ቀበሌዎችን ቡድኑ በቁጥጥር ሥር ማድረጉን፣ በዚህ ውጊያም በርካታ የልዩ ፖሊስ ኃይል አባላትን መገደላቸውን ለሮይተርስ ተናግሮ ነበር።

ጥቃት መፈጸሙን በተመለከተ ከኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ሐሙስ ምሽት ባወጣው መግለጫ አሸባሪ ሲል የጠራው አልሻባብ ጥቃት ሰንዝሮ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንደደረሰና የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን ደንኅንት ለማስከበር አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።

የሶማሌ ክልል መስተዳደርም ድንበር አልፈው የገቡት የአልሻባብ ታጣቂዎች ለሦስት ቀናት ከክልሉ ልዩ ኃይል ጋር ባደረጉት ውጊያ ከ100 በላይ የሚሆኑት መገደላቸውን፣ 13 ተሽከርካሪዎቹ መውደማቸውንና ትጥቅና ስንቅ መማረኩንም አስታውቋል።

አልሸባብ በትናንትናው ዕለት በሸበሌ ዞን ፌር ፌር ወረዳ በከፈተው ውግያ ነዋሪዎች በልዩ ኃይሉና ድንበር ተሻግሮ በገባው ቡድን መካከል የተኩስ ድምጽ ከአካባቢው ርቀው በሚገኙ ቦታዎች ጭምር ይሰማ እንደነበር ተናግረዋል። ነገር ግን በዚህ ውጊያ ስለደረሰ ጉዳት እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

3 - የአገር መከላከያ ሠራዊት መሰማራት

 ባለፈው ሳምንት በአልሻባብ የተከፈተውን ጥቃት ለመከላከል የክልሉ ልዩ ኃይል ተሰማርቶ የነበረ ሲሆን፣ የሶማሌ ክልል እንዳስታወቀው በታጣቂዎቹ ላይ በሚካሄደው ዘመቻ ላይ ለመሳተፍ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ ክልሉ ተሰማርተዋል።

የክልሉ ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ ሙሐመድ ከድንበር ተሻግሮ የገባውን ቡድን ለመዋጋት የተሰማራውን የአገር መከላከያ ሠራዊት መጎብኘታቸውም ተነግሯል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን ጦርነት ተከትሎ በሶማሊያ ክልል የድንበር አካባቢዎች ሰፍሮ የነበረው የኢትዮጵያ ሠራዊት በክልሉ ልዩ ኃይል ተተክቶ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት ግን ሠራዊቱ ወደ ቀድሞ ስፍራው መመለሱ ተገልጿል።

4 - አልሸባብ ጥቃት ለምን ሊሰነዝር ቻለ?

አንድ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ለሮይተርስ የጥቃቱ ምክንያት ሊሆን ይችላል ያሉትን ሲናገሩ፣ አንድ የአልሻባብ ታጣቂዎች አዛዥ የቡድኑን ህዋስ በኢትዮጵያ ውስጥ ለማቋቋም ወደ የኢትዮጵያ ድንበር ገብቶ መገደሉን አስታውሰዋል።

በተጨማሪም ከጥቃቱ ቀደም ብሎ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በክልሉ በኤልከሬ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ ሂሎ ማዶው በተባለ መንደር ውስጥ ባካሄደው አሰሳ በጉድጓድ ውስጥ ተቀብረው የነበሩ የተለያዩ አይነት የጦር ማሳሪያዎችን አግኝቶ ነበር።

ከዚህም ጋር በተያያዘም የአልሻባብ አባላት ናቸው የተባሉ ሰዎችን ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን፣ አሁን አልሻባብ የሰነዘረው ጥቃትም ከዚሁ ጋር የተገናኘ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለ።

5 - የአልሸባብ ጥቃት ዓላማ ምንድን ነው?

የሶማሌ ክልል የፀጥታ ምክር ቤት ቅዳሜ ምሽት ባወጣው መግለጫ፣ የአልሻባብ ታጣቂዎች አላማ በክልሉ በኤልከሬ ወረዳ በኩል አልፎ ወደ “ኦሮሚያ ክልል በመግባት ከሸኔ ሽብርተኛ ቡድን ጋር ለመገናኘት አልሞ ነበር” ብሏል።

ይሁን እንጂ ታጣቂው አስላማዊ ቡድን ግን እስካሁን ለምን በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቆ እንደገባ እና ስለደረሰበት ጉዳት ያለው ነገር የለም።

የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያየ ወቅት የሶማሊያው አስላማዊ ቡድን አልሻባብ እና ዓለም አቀፉ የሽብር ቡድን አይኤስ አባላት በአዲስ አበባ ውስጥ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም እና ትርምስ ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ መያዛቸውን ማስታወቁ ይታወሳል።