ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በትግራይ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ተፈጽመዋል ተባለ

ጾታዊ ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነትን ያስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በትግራይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እንደተፈጸመባቸው አንድ ሪፖርት አመለከተ።

ፊዚሺያንስ ፎር ሂዩማን ራይትስ እና ኦርጋናይዜሽን ፎር ጀስቲስ ኤንደ አካውንተቢሊቲ ኢን ዘ ሆርን ኦፍ አፍሪካ የተባሉ ድርጅቶች ባደረጉት ጥናት እና ላንሴት የተባለው እውቅ የሕክምና መጽሔት (ጆርናል) በተሳተፈበት ሪፖርት ከስላም ስምምነቱ በኋላ ቢያንስ 128 ሴቶች ጥቃት እንደተፈጸመባው አሳይቷል።

በጦርነቱ በክልሉ የነበሩ የጤና ተቋማት በመዘረፋው ወይም በመውደማቸው ምክንያት በርካታ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶች የጤና ክትትል ማግኘት ሳይችሉ ወራት ማለፋቸው ተገልጿል።

በሪፖርቱ ተዋጊዎች በሆኑ ጾታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው በርካታ ሴቶች በኤችአይቪ ቫይረስ መያዛቸውን እና የደፋሪዎቻቸውን ልጆች ለማሳደግ መገደዳቸውም ተመላክቷል።

ጥናት አድራጊዎቹ ከትግራይ ጤና ተቋማት ጾታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው 300 ሴቶችን በነሲብ (randomly) መርጠው ነው ጥናታቸውን የሠሩት።

ከእነዚህ መካከል 128 በሚሆኑት ላይ ጾታዊ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው የሰላም ስምምነቱ ጥቅምት 2015 ዓ.ም. ከተፈረመ በኋላ ሲሆን፣ 76 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ደግሞ ጾታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሁለት እና ከሁለት በላይ በሆኑ ሰዎች ነው ያለ ሲሆን፣ አንዲት ሴት በ19 ወንዶች ጥቃት ተፈጽሞባታል።

የመድፈር ወንጀሎች ሲፈጸሙ 94 በመቶው በደፋሪዎቹ ኮንዶም ጥቅም ላይ አልዋለም። በርካታ ደፋሪ ወንዶቹ ጥቃቱን ሲፈጽሙም ሴቶችን በጦር መሳሪያ፣ በስለት ወይም በዱላ እያስፈራሩ ነው።

ሪፖርቱ ጨምሮ አንዳንድ ሴቶች በተደጋጋሚ ታፍነው እየተወሰዱ ጾታዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

በሪፖርቱ ላይ የተጠቀሱ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶች ጥቃት አድራሾቹ አብዛኛዎቹ የጎረቤት አገር ኤርትራ ወታደሮች ናቸው ብለዋል።

የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሳባቸው አካባቢዎች መካከል ዋነኛ የበሆነው ምዕራብ ትግራይ ከጥቅምት 2013 ጥቅምት 2015 ድረስ ባሉት ጊዜያት በ86 ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃቶች መከሰታቸውን እና ከእነዚህ መካከል በ68ቱ ሴቶች ላይ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው በቡድን ነው ብሏል ሪፖርቱ።

በትግራይ ክልል ተጀምሮ ወደ አማራ እና አፋር ክልል በተሻገረው የእርሰ በእርስ ጦርነት የኤርትራ ኃይሎች ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ተሰልፈው መዋጋታቸው ይታወሳል።

የኤርትራ ሠራዊት አባላትን ጨምሮ በዚህ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑት የፌደራል መንግሥቱ፣ የአማራ ኃይሎች እና የትግራይ ኃይሎች በሙሉ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲከሰሱ ቆይተዋል።

ጥናት አድራጊዎቹ ጥናቱ ጥቃቶቹ አስገድዶ መድፈርን እንደ ጦር መሳሪያ አድርጎ ለመጠቀም ጥቅም ላይ የዋለ ስልታዊ ጥቃት መሆኑን አሳይቷል ብለዋል።

ይህ ሪፖርት ከወጣ በኋላ ከኢትዮጵያም ሆነ ከኤርትራ የተሰጠ ምላሽ የለም። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት በጦርነቱ ወቅት እና ከጦርነቱ በኋላ በሠራዊቱ አባላት ተፈጽመዋል የተባሉ ጾታዊ ጥቃቶች ላይ የራሴን ማጣራት አደርጋለሁ ብሎ ነበር።