የእግር ኳስ ዳኞች ማኅበር ከአውሮፓ ሊግ ፍፃሜ በኋላ እንግሊዛዊው ዳኛ ላይ የደረሰው “አሳዛኝ” ነው አለ

እንግሊዛዊው ዳኛ አንተኒ ቴይለር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፒጂሞል በመባል የሚታወቀው የእንግሊዝ እግር ኳስ ዳኞች ማኅበር አንተኒ ቴይለር ላይ የደረሰውን ድርጊት ወቅሷል።

እንግሊዛዊው ዳኛ አንተኒ ቴይለር፤ የአውሮፓ ሊግ ፍፃሜን ዳኝተው ሲመለሱ ሃንጋሪ ቡዳፔስት አየር ማረፊያ በደጋፊዎች ተዋክበዋል።

አንተኒ በዳኙት በዚህ የፍፃሜ ጨዋታ የስፔኑ ክለብ ሲቪያ የጣሊያኑን ሮማ በፍፁም ቅጣት ምት መርታት ችሏል።

ዳኛው እና ቤተሰቦቻቸው አውሮፕላን ማረፊያው ሲደርሱ በተቆጡ የእግር ኳስ ደጋፊዎች የቃላት ውርጅብኝ ደርሶባቸዋል።

የሮማው አሠልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆም ከጨዋታው በኋላ የመኪና ማቆምያ ውስጥ ጠብቀው ዳኛውን በስድብ ሸንቁጠዋቸዋል።

ፒጂሞል ባወጣው መግለጫ “በማኅበራዊ ሚድያ እየተሠራጩ ያሉ ዳኛ አንተኒ ቴይለር እና ቤተሰቦቻቸው በቡዳፔስት አየር ማረፊያ የቃላት ጥቃት ሲደርስባቸው የሚያሳዩ ምስሎችን ተመልክተናል” ብሏል።

አክሎ መለግጫ “ዳኛ አንተኒ ቴይለር እና ቤተሰቦቻቸው ከፍፃሜው ጨዋታ በኋላ ወደአገራቸው ሲመለሱ በደረሰባቸው ፍትህ አልባ ጥቃት እጅጉን አዝነናል” ብሏል።

“ለአንተኒ እና ለቤተሰቦቻቸው የሚገባቸውን ሙሉ ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን።”

በሌላ በኩል የአውሮፓ እግር ማኅበር ከፍፃሜው ጨዋታ በኋላ የዳኞችን የጨዋታ ሪፖርት እየጠበቀ ነው።

ማኅበሩ ይህን የሚያደርገው አሠልጣኝ ሞሪንሆ ላይ ቅጣት ለመጣል በማሰብ ነው።

በተለይ ደግሞ ሞሪንሆ በስታድየሙ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ጠብቀው ዳኛ አንተኒን መውቀሳቸው የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል።

ሞሪንሆ ከጨዋታው በኋላ በሰጡት ቃለ-ምልልስ እንግሊዛዊውን ዳኛ አብዝተው የወቀሱ ሲሆን፣ አንተኒ እና የሥራ አጋሮቻcው ሚኒባስ ሲሳፈሩ ጠብቀውም ሐሳባቸውን በኃይለ ቃል ገልጸዋል።

ፖርቹጋላዊው አሠልጣኝ በተደጋጋሚ “አሳፋሪ” ነው የሚል ቃል ከአፋቸው ሲወጣ ተሰምቷል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር የዳኞች መኮንን ሮቤርቶ ሮሴቲ ጉዳዩን ለማረጋጋት ሲሞክሩ ተስተውለዋል።

በጣም የጋለ በነበረው የፍፃሜ ጨዋታ ሞሪንሆ የዳኛን ውሳኔ በመቃወማቸው የቢጫ ካርድ ተመልክተዋል።

አንተኒ ቴይለር በጨዋታው ለሞሪንሆ ብቻ ሳይሆን ለ13 ተጫዋቾች ቢጫ ካርድ በማሳየት ክብረ-ወሰን ሰብረዋል።