ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትራምፕ የግድያ ሙከራ፡ የአሜሪካ አደገኛ የፖለቲካ ጅማሬ እና የሕዳሩ ምርጫ አቅጣጫ ቀያሪ ክስተት
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የተፈጸመባቸው የግድያ ሙከራ ሕዳር 2017 ላይ የሚደረገውን የምርጫ ሂደትን ከመቀየሩም በላይ የአገሪቱን ፖለቲካ እስከወዲያኛው የሚቀይር ክስተት ነው ተብሏል።
የቢቢሲ የሰሜን አሜሪካ አርታይ የሆነችው ሳራ ስሚዝ፤ “ዶናልድ ትራምፕ የግድያ ሙከራ ከተፈጸመባቸው በኋላ ፊታቸው ላይ ደም እየታየ፣ በሴክሬት ሰርቪስ አባላት ተሸፍነው ከመድረክ እየወረዱ አይበገሬነታቸውን ለመግለጽ እጃቸውን ወደላይ አንስተው የሚታዩበት ምስል ለታሪክ ብቻ የሚቀመጥ ሳይሆን የአሜሪካን ፖለቲካ እስከወዲያኛው የሚቀይር ነው” ትላለች።
የሰሜን አሜሪካ ዘጋቢው አንቶኒ ዛከር ደግሞ የተተኮሰችው ጥይት ትራምፕን ጨርፋ ያለፈች ብቻ ብትሆንም፤ የአገሪቱ ፖለቲካ አደገኛ ጅማሬ ልትሆን ግን ትችላለች ይላል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ላይ ሳሉ የግድያ ሙከራ ተፈጽሞባቸው በጥይት መመታታቸው ይታወሳል።
ትራምፕ በአሜሪካዋ ፔንስልቬኒያ ከደጋፊዎቻቸው ፊት ቆመው ንግግር እያደረጉ ሳለ በርካታ ጥይቶች ወደ እርሳቸው የተተኮሱ ሲሆን፤ በቀኝ በኩል ያለው ጆሯቸው በጥይት ተመትቷል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት ክስተቱን የግድያ ሙከራ ብለው የገለጹት ሲሆን ጥቃት የፈጸመው ግለሰብ ከጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰበት ጥይት ተገድሏል።
በስም ያልተገለጸው የ22 ዓመት ወጣት በቀድሞ ፕሬዝዳንት ላይ የግድያ ሙከራ ለመፈጸም ምን እንዳነሳሳው ምርመራ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ሳራ ስሚዝ ይህ የፖለቲካ ፍላጎትን በኃይል ለማሳካት የተደገረ አስደንጋጭ የግድያ ሙከራ ሕዳር 2017 ዓ.ም. ለሚደረገው ምርጫ የሚደረጉ የምረጡኝ ዘመቻዎች የሚካሄዱበትን ሁኔታ የሚቀይር ይሆናል ትላለች።
አንቶኒ ደግሞ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ላይ የተፈጸመው የግድያ ሙከራ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ለአስርት ዓመታት የተገነባውን የደኅንነት ስሜት በቅጽበት ያፈረሰ ጥቃት ሆኗል ይላል።
ትራምፕ በዚህ ጥቃት የደረሰባቸው አደጋ ቀላል የሚባል ነው። ይሁን እንጂ ጆሯቸውን የመታችው ጥይት የፕሬዝዳንቱን ጭንቅላት ለጥቂት የሳተች ነበር።
በአሜሪካ ለመጨረሻ ጊዜ ስመ ጥር በሆነ ፖለቲከኛ ላይ የግድያ ሙከራ የተፈጸመው እአአ 1981 ላይ ነበር።
ከ43 ዓመታት በፊት ሮናልድ ሬጋን የግድያ ሙከራ ተፈጽሞባቸው ነበር። ከእርሳቸው በፊት ጆን ኤፍ ኬኔዲ እአአ 1963 ላይ ግድያ እንደተፈጸመባቸው ይታወሳል። ከ35ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ግድያ በተጨማሪ የማርቲን ሉተር ኪንግ እንዲሁም የማልኮም ኤክስ ግድያ የአሜሪካን የፖለቲካ ሂደት አቅጣጫ ቀያሪ ክስተቶች ሆነው ተመዝግበዋል።
ትራምፕ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ያወገዙት ጆ ባይደን፤ ከግድያ ሙከራው በኋላ ሁሉንም የምርጫ ቅስቀሳቸውን አቁመዋል። የባይደን የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ትራምፕ የግድያ ሙከራ ተፈጽሞባቸው ቅስቀሳ ማደረጉ አግባብ አይደለም በሚል የሚያደርጓቸውን ዘመቻዎች በጊዜያዊነት አቁመው ጥቃቱን እያወገዙ ነው።
በፖለቲካ ዓለም የተለያየ አመለካከት ያላቸው አሜሪካውያን ትራምፕ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በማውገዝ አንድ አይነት አቋማቸውን እያጸባረቁ ይገኛሉ። ሁሉም “በዴሞክራሲያችን ውስጥ አመጽ ቦታ የለውም” በሚል በአንድ ድምጽ አቋማቸውን እያሳወቁ ይገኛሉ።
የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ባራክ ኦባማ፣ ጆርጅ ደብሊው ቡሽ፣ ቢል ክሊንተን እና ጂሚ ካርተር የግድያ ሙከራውን አጥብቀው ተቃውመዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ትራምፕ ላይ ለተፈጸመው የግድያ ሙከራ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ተጠያቂ ያደረጉ ፖለቲከኞች አልጠፉም።
ትራምፕ ፕሬዝዳንት ሆነው ቢመረጡ ምክትላቸው ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉት ሴናተር ጄዲ ቫንስ ለግድያ ሙከራው ፕሬዝዳንት ባይደንን ተጠያቂ አድርገዋል።
ሴናተር ቫንስ በኤክስ ገጻቸው ላይ የባይደን ንግግር ትራምፕ ላይ “ግድያ እንዲፈጸም የሚያበራታታ ነው” ሲሉ ጠንከር ያለ ወቀሳ ሰንዝረዋል።
ከዚህ ሴናተር በተጨማሪ በቁጥር ጥቂት የማይባሉ የትራምፕ ደጋፊዎች የግድያ ሙከራውን የፈጸመው ግለሰብ በባይደን አስተዳደር ይሁንታ ያገኘ ነው ወደሚል የሴራ ትንተና እየገቡ ነው።
የቢቢሲዋ ሳራ ስሚዝ ይህ አስደንጋጭ ክስተት በቀጣይ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ጥሩ መንፈስ የሌለበት ፖለቲካዊ ፍትጊያን የሚያሳየን ይሆናል ትላለች።