ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያን ጨምሮ የፌስቡክ ይዘቶችን የሚቆጣጠረው ተቋም አገልግሎቱን ሊያቆም ነው
ኢንስታግራም፣ ፌስቡክን እና ዋትስአፕን የሚያስተዳድረው ሜታ ይዘት ተቆጣጣሪ የሆነው የምሥራቅ አፍሪካው ድርጅት፣ ሳማ በፈረንጆቹ ሚያዝያ ወር መጨረሻ የይዘት ቁጥጥር ሥራውን ለማቆም ማቀዱን አስታወቀ።
ድርጅቱ ለሠራተኞቹ በላከው መልዕክት ትኩረቱን ዳታ ማደራጀት ላይ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ድርጅቱ ከኢትዮጵያ የሰሜኑ ጦርነት ጋር የተያያዙትን ጨምሮ በቀጠናው በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩ የሚተላለፉ ጎጂ ይዘቶችን እየተቆጣጠረ ይገኛል።
የሜታ ቃል አቀባይ፣ ሳማ የይዘት ቁጥጥር አገልግሎቱን ለማቆም ያሳለፈውን ውሳኔ እንደሚያከብሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ ባለቤት የሆነው ሜታ፣ ሽግግሩ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩ ላይ ተፅዕኖ እንዳይኖረው እንደሚያረጋግጥ ገልጿል።
ሜታ እንዳለው አሁንም ቢሆን ጎጂ የሆኑ ይዘቶች ከቁጥጥር አያመልጡም።
ሜታ ውሳኔው የሳማ እንደነበር የገለጸ ሲሆን ሳማ በበኩሉ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ምክንያት አድርጓል።
ሳማ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩ ላይ የሚሰራጩ ከጥላቻ አዘል ይዘቶች እስከ አሰቃቂ የሆኑ ምስሎችንና ቪዲዮዎችን ላይ ቁጥጥር ሲያደርግ ነበር።
ግንቦት ወር ላይ በድርጅቱ ውስጥ ተቀጥሮ ይሠራ የነበረው የቀድሞው የይዘት ተቆጣጣሪ፣ ሥራው የአዕምሮ ጤናውን እንደጎዳው በመግለጽ ሁለቱንም ድርጅቶች ላይ ክስ መስርቶ ነበር።
ዳንኤል ሞታንግ እንዳለው በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹ የተሰራጩና ሰዎች ሲቀሉ እና ህጻናት ላይ ጥቃት ሲፈፀም የሚያሳዩ ይዘቶችን ተመልክቷል። በዚህም የተነሳ ለአዕምሮ ጤና ችግር በመዳረጉ የአዕምሮ ሕክምና ማድረጉንና ለዚህ ለዳረገው ሥራውም በሰዓት 2.20 ዶላር ይከፈለው እንደነበር ገልጿል።
ሳማ ናይሮቢ ካለው ቢሮ 3 በመቶ ሚሆኑ ሠራተኞቹን እንደሚያሰናብት የገለጸ ሲሆን ለሠራተኞቹም በመሥሪያ ቤቱ የሚኖራቸውን ጊዜ ካጠናቀቁ በኋላ ለ12 ወራት የጤና ድጋፍ እሰጣለሁ ብሏል።
ሜታም በበኩሉ በዚህ የሽግግር ወቅት የይዘት ቁጥጥር ላይ ችግር እንዳይከሰት ለማረጋገጥ ከአጋር ድርጅቶች ጋር እንሰራለን ብሏል።
ሜታ በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ጥላቻ እና ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ይዘቶችን በማሰራጨት የ2 ቢሊየን ዶላር ክስ ቀርቦበታል።
ሜታን ከከሰሱት መካከል ፌስቡክ ላይ በተለጠፈ ጽሑፍ ምክንያት አባቱ የተገደለበት አብርሃም ማዕረግ ይገኝበታል። በፌስቡክ ጽሑፍ ምክንያት አባቱ ጥቃት ደርሶበታል፣ በጥይትም ተገድሏል።
ከሳሾቹ በፌስቡክ ላይ ከተሰራጨው ጥላቻ ጋር በተያያዘ ለደረሰባቸው ጉዳት የሁለት ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈላቸው እንዲሁም የፌስቡክ አልጎሪዝም ላይ ለውጥ እንዲደረግም ጠይቀዋል።
ይህ የሆነው ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ተወዳዳሪ ለመሆንና ገቢው በመቀነሱ ምክንያት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞቹን ለማሰናበት ማቀዱን ካስታወቀ ከወራት በኋላ ነው።