ቤተክርስቲያን ውስጥ ምዕመናንን የገረፈው ነብይ በኡጋንዳ ፖሊስ ታሰረ

ነብይ ኪንቱ ዴኒስ
የምስሉ መግለጫ, ነብይ ኪንቱ ዴኒስ

እራሱን ነብይ ነኝ ብሎ የሰየመው ኡጋንዳዊ በቤተ ክርስቲያኑ አባላት ላይ አካላዊ ጥቃትን በመፈጸም እና በሰዎች ዝውውር ታስሮ ክስ ቀረበበት።

ነብይ ኪንቱ ዴኒስ የተከሰሰው የ‘ሆይማ ኢምፓወርመንት’ ዓለም አቀፍ ቤተክርስቲያን አባላትን በበትር ሲገርፍ የሚያሳይ ቪዲዮ በኢንተርኔት ላይ በስፋት ከተሰራጨ በኋላ ነው።

የኡጋንዳ ፖሊስ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የታየውን ተንቀሳቃሽ ምስልን ተከትሎ በቀረበው አቤቱታ መሠረት የ42 ዓመቱን ነብይ እና ሌሎች አራት ሰዎችን ረቡዕ ዕለት በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል።

በስፋት በታየው ቪዲዮ ላይ ነብይ ኪንቱ የቤተ ክርስቲያኑን ሌሎች አባላትን ወደ ፊት መጥተው እንዲገረፉ ካልሆነም በፀሎት ሥነ ሥርዓት ላይ እና በሌሎች አገልግሎቶች ላይ የመሳታፍ ዕድልን እንደማያገኙ ሲናገር ይሰማል።

ከዚያም በቤተክርስቲያኑ የተሰበሰበው ምዕመን ከአባላቱ መካከል አንድ በአንድ ወደ ፊት እየቀረቡ ሲገረፉ ሲመለከቱ የሚታይ ሲሆን፣ ከበስተጀርባም ለስላሳ የፒያኖ ድምጽ ይሰማል።

በፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋለው ነብይ ኪንቱ በምርመራ ወቅት እንደተናገረው፣ በተንቀሳቀቃሽ ምስሉ ላይ የሚታየው በበትር መገረፍ ትዕይንት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትን ምሳሌን መሠረት ያደረገ ነው ብሏል።

በዚህም ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ መቅደስ ውስጥ ሸቀጦችን ሲነግዱ የነበሩትን ሰዎች እንዴት አድርጎ በጅራፍ እየገረፈ እንዳስወጣቸው የሚያሳየውን ሁኔታ በተግባር ለማሳየት የተደረገ መሆኑን መናገሩን የፖሊስ መግለጫ አመልክቷል።

ይህንንም ክስተት ተከትሎ የኡጋንዳ ባለሥልጣናት ግለሰቡ በሕገ ወጥ መንገድ ሥራውን እያከናወነ ነው ሲሉ ከሰውታል።

ክሱን ተከትሎ ፖሊስ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ባደረገው ፍተሻ በቪዲዮው ላይ በምዕመናኑ ላይ በተፈጸመው ግርፋት ጥቅም ላይ የዋሉ ሳይሆኑ አይቀሩም የተባሉ ሦስት በትሮች መገኘታቸው ተነግሯል።

ነብይ ኪንቱ ዴኒስ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራው አስከሚጠናቀቅ ድረስ አስከ መጪው ሐሙስ ጳጉሜ 1 ድረስ በእስር ላይ እንደሚቆይ ተገልጿል።

በኡጋንዳ ውስጥ በርካታ የኢቫንጀሊካል አብያተክርስቲያናት በመላው አገሪቱ የሚገኙ ሲሆን፣ አብዛኞቹ በሕግ ያልተመዘገቡ እና ብዙዎቹ ደግሞ እራሳቸውን የአግዚአብሔር ሰው አድርገው በሰየሙ ግለሰቦች የሚመሩ እንደሆነ ይነገራል።