በምጥ ላይ በነበረች እናት እና በልጇ ሞት ሦስት ሴኔጋላውያን ሐኪሞች ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሦስት ሴኔጋላውያን የህክምና ባለሙያዎች በምጥ ላይ ለነበረች እናት እና ለልጇ ሞት ተጠያቂ ናቸው በሚል ተይዘው ታሰሩ።
የህክምና ባለሙያዎቹ ለእስር የበቁት በምጥ ላይ የነበረችውን እናት በተገቢው ሁኔታ በቀዶ ህክምና ለማዋለድ ሳይረዷት በመቅረታቸው ነው ተብሏል።
የአገሪቱ የጤና ባለሙያዎች ማኅበር ባለሥልጣን እንዳሉት በእናት እና በልጇ ላይ ካጋጠመው ሞት ጋር ተያይዞ የታሰሩት ሐኪሞች ሦስት ናቸው።
ባለሙያዎቹ የጽንስና የማህጸን፣ የሰመመን እና ነርስ ሲሆኑ በህክምና ወቅት ግዴለሽነት በማሳየት ለእናት እና ለልጇ ሞት ምክንያት ሆነዋል ተብለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው ተብሏል።
የሴኔጋል መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የመውለጃ ጊዜዋ ደርሶ ወደ ሆስፒታል የሄደችው እናት ለሞት የበቃችው በከፍተኛ ሁኔታ ደም ከፈሰሳት በኋላ ነው።
በተጨማሪም የተወለደው ጨቅላ በቀዶ ህክምና ወቅት በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ህይወቱ አልፏል ተብለዋል።
የሴኔጋል የማህጸን እና ጽንስ ባለሙያዎች ማኅበር ግን የህክምና ባለሙዎቹ መታሰርን “ትክክል ያልሆነ” እርምጃ ነው ሲል በመተቸት ሐኪሞቹን ተከላክሏል።
የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ማኅበሩ ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው የህክምና ባለሙያዎቹ ቡድን በቀዶ ህክምናው ወቅት ለእናትየውና ለህጻኑ ደኅንነት የሚጠበቀውን “ተገቢውን ውሳኔ” ሰጥተዋል ብሏል።
ባለፈው ዓመት የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል የአገሪቱን የጤና አገልግሎት ሥርዓት ማርጀቱን በመግለጽ፣ በተለይ በእናቶች እና በህጻናት ጤና አገልግሎት ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ማሻሻያ እንዲደረግ አዘው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ትዕዛዝ ያስተላለፉት አንዲት በምጥ ላይ የነበረች እናት ሕይወቷ ማለፉን ተከትሎ በመላው አገሪቱ ከፍተኛ ቁጣን ከተቀሰቀሰ በኋላ ነበር።
በዚህም ሳቢያ ሦስት አዋላጅ ነርሶች በአደጋ ላይ ያለን ሰው ባለመርዳት ክስ ጥፋተኛ ተብለዋል።












