በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ከ550 በላይ የሐጅ ተጓዦች ሕይወት አለፈ

በዘንድሮው የሐጅ ጉዞ ቢያንስ 577 የተለያዩ አገራት ዜጎች መሞታቸውን እና አብዛኞቹ ከሙቀት ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ማለፉን ኤኤፍፒ የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ ዘገበ።

ከሟቾች መካከል አብዛኞቹ አፍሪካውያን ናቸው።

ከሟቾቹ ውስጥ ቢያንስ 323ቱ ግብፃውያን መሆናቸውን ሁለት የአረብ ዲፕሎማቶች ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

ቢቢሲ በሟቾቹ ዙሪያ አስተያየት ለማግኘት የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ባለሥልጣናትን ቢጠይቅም እስካሁን ምላሽ አላገኘም። ቢቢሲ የግብፅ ባለሥልጣናትን አስተያየት ጠይቆ የማጣራት ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ምላሽ አግኝቷል።

በዚህ ዓመት አንድ ነጥብ 6 ሚሊዮን የውጭ አገር ዜጎችን ጨምሮ ከአንድ ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሐጃጆች ወደ ሳዑዲ አረቢያ በተደረገው የሐጅ ጉዞ መሳተፋቸውን የሳዑዲ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

እሑድ ዕለት 2 ሺህ 700 ከሙቀት ጋር የተያያዙ ክስተቶች ተመዝግበዋል።

የሐጅ ጉዞው ባበቃበት ሰኞ ዕለት በመካ ታላቁ መስጂድ የሙቀት መጠኑ እስከ 51.8 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ደርሶ እንደነበር የሳዑዲ አረቢያ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

በሙስሊሞች ሕይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነው የሐጅ ጉዞ ሥርዓት ከአምስቱ የእስልምና እምነት አምዶች መካከል አንዱ ነው።

አቅም ያላቸው ሙስሊሞች በሕይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ ይህንን ጉዞ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በጅዳ የሚገኘው የሞሮኮ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ባልደረባ የሆኑት አብደላህ ዳዳስ አምስት የሞሮኮ የሐጅ ተጓዦች ሕይወት ማለፉን አረጋግጠዋል።

የሞቱት ሰዎች “እንደ ስኳር ህመም እና የደም ግፊት የመሳሰሉ ሥር የሰደዱ በሽታዎች” እንደነበሩባቸው እና ሦስቱ ሕይወታቸው ያለፈው በሆቴላቸው ውስጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የሞሮኮ ባለሥልጣናት እንደገለጹት ከሆነ ወደ 34 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ለቅዱሱ ሃይማኖታዊ ጉዞ ወደ ሳዑዲ አረቢያ አቅንተዋል።

22 ሺህ 500 የሚሆኑት በኢንዶውመንት እና እስልምና ጉዳዮች ሚኒስቴር እና 11 ሺህ 500 በጉዞ ኤጀንሲዎች በኩል የተጓዙ ናቸው።

የቱኒዚያ ሪፐብሊክ ቆንስላ ጄኔራል በበኩሉ በሐጅ ጉዞ ወቅት ሕይወታቸውን ያጡ 23 የቱኒዚያ ዜጎችን ስም ዝርዝር በፌስቡክ ገጹ ይፋ አድርጓል።

የቱኒዚያ ሐጃጆች የጤና ልዑካን ቡድን ዋና አስተባባሪ እንዳሉት ሆስፒታሎችን ለማነጋገር ጥረት ቢደረግም የተወሰኑ ምዕመናን ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ አልተቻለም።

ቅዳሜ ዕለት ደግሞ የቱኒዚያ የሰብአዊ መብቶች ታዛቢ ቡድን ፕሬዝዳንት ሙስጠፋ አብደል ከቢር 5 ምዕመናን መሞታቸውን አረጋግጠዋል።

በዚህ ዓመት 11 ሺህ 227 ቱኒዚያውያን ወደ መካ ተጉዘዋል።

የሴኔጋል የአፍሪካ ውህደት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በግል አስጎብኚ የተጓዙ ሦስት ሴኔጋላውያን በመካ ሞተዋል ብሏል።

የሴኔጋል መንግሥት በጂዳ የሚገኘው የአገሪቱ ኤምባሲ ከሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት ጋር በመነጋገር “በእስልምና ሕግ መሠረት” የቀብር ሥርዓታቸው እዚያው እንዲፈጸም ጠይቋል።

በዚህ ዓመት በሐጅ ጉዞ 12 ሺህ 860 ሴኔጋላውያን ተሳትፈዋል።

ሁለት ናይጄሪያውያን ተጓዦችም ሞተዋል ተብሏል።

ከባድ ሙቀት

ባለፈው ዓመት 240 ሰዎች በሐጅ ጉዞ ወቅት ሕይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው።

የሳዑዲ አረቢያ የጤና ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ “ጥንቃቄ አስፈላጊ ነው። ሐጃጆች አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር በሞቃታማ ሰዓት ወደ ውጪ መውጣት ማቆም ወይም ዣንጥላ መጠቀም አለባቸው” ብሏል።

“ለሚቀጥሉት ቀናት የእኛ የጤና መመሪያ ግልጽ እና ቀላል ነው። ዣንጥላ ይያዙ፣ ውሃ አዘውትረው ይጠጡ እና ለፀሐይ ከመጋለጥ ይቆጠቡ።”

የሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን በበኩላቸው አገራቸው “አማኞች በአስተማማኝ እና በልበ ሙሉነት እንዲያመልኩ ለመርዳት የተቻላቸውን ሁሉ አንደሚያደርጉ” ገልጸዋል።

በየዓመቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሐጃጆች ይፋዊ የቪዛ ዋጋ ውድ በመሆኑ መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች ሐጅ ለማድረግ ይሞክራሉ።

እነዚህ ምዕመናን የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት የሚያቀርቡትን የአየር ማቀዝቀዣ አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸው ለከፍተኛ ሙቀት ይጋለጣሉ።