ብዙ የተባለለት የዱባይ “ዓለም” ግዙፍ ፕሮጀክት ከምን ደረሰ?

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ዱባይ በግዙፍ ፕሮጀክቶቿ ዓለምን ጉድ አሰኝታለች። የዓለማችን ረዥሙ ህንጻ ቡርጀ ካሊፋ፤ የዓለማችን ስማርት ሆቴል ቡርጀ አል አረብ እና ግዙፉ “የፓልም ደሴቶች” መኖሪያ ስፍራን እንካችሁ ብላ ዓለምን አስደምማለች።

በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች የፈሰሱበት አንድ ዕቅድም ይፋ አድርጋ ነበር። ይህ ውስብስብ በዓለም አህጉራት ቅርፅ የተሠራ የ260 ሰው ሰራሽ ደሴቶች ስብስብ ከሃያ ዓመታት በላይ ቢያስቆጥርም በአብዛኛው በባዶ ቀርቷል።

ለመሆኑ “የዓለም ደሴቶች ከምን ደረሱ?”

ሃሳቡ የተፀነሰው በዓለም አህጉራት - በአፍሪካ፣ በአንታርክቲካ፣ በእስያ፣ በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በኦሺኒያ እና በደቡብ አሜሪካ ቅርፅ የሚገነቡ የ260 ሰው ሰራሽ ደሴቶች ስብስብ ነው።

ሊተገበር የታቀደው ከዱባይ የባሕር ዳርቻ 4 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው።

እያንዳንዱ ደሴት ስም ተሰጥቶታል። ስያሜዎቹ የተሰጡት እያንዳንዱ አህጉር ውስጥ ባለ አገር፣ ከተማ ወይም ክልል ነው።

የግል ኩባንያዎች በዓለም ዙሪያ ያሉ ጎብኚዎችን የተለያዩ ባህሎች እንዲያገኙ የሚያግዙ እንደ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ሪዞርቶች ወይም መኖሪያ ቤቶችን በደሴቶቹ ላይ እንዲገነቡ ነበር ዕቅዱ።

በመንግሥት የሚደገፈው ናክሂል ፕሮፐርቲስ የተባለው ድርጅት አራት ሺህ ቅንጡ ቤቶችን እና በደርዘን የሚቆጠሩ ሆቴሎች ያሉት ፓልም ጁሜራህ የተባለ ሰው ሠራሽ ደሴት በቅርቡ አጠናቋል።

የዓለም ደሴቶች ግን ከዚህ የበለጠ እጅግ በጣም ግዙፍ የባሕር ዳርቻ ልማት እንዲሆኑ ታስቦ ነበር ሥራው የተጀመረው።

ደሴቶቹ ለዱባይ ተጨማሪ 230 ኪሎ ሜትር የባሕር ዳርቻ ያስገኙላታል።

የቱሪስቶችንም ቁጥር እንደሚያሳድግ ተስፋ ተሰንቆ ነበር።

ዎርልድ ዱባይ ፕሮጀክት በ2003 በአገሪቱ ገዥ ሼክ መሐመድ አል ማክቱም ነበር ይፋ የተደረገው።

እንዴት ተገነባ?

ናክሂል የደሴቶቹን ግንባታ በተመሳሳይ ዓመት ማከናወን ጀመረ።

ደሴቶቹ የተሠሩት ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ በመጣ 321 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር አሸዋ ነው።

የሥነ-ምህዳር ተመራማሪዎች ግን የቁፋሮ ሥራው በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ውስጥ የሚገኙ የውሃ አካላትን ጎድቷል። ለጉዳት ተጋልጠዋል የተባሉት ስፍራዎች እንደገና እንዲያገግሙ እና እንዲያንሰራሩ ለማድረግ የባሕር ባዮሎጂስቶችን ናክሂል ቀጥሯል።

ፕሮጀክቱ እንዴት ችግር ውስጥ ገባ?

ናክሂል የደሴቶቹን እና በዙሪያው ያለውን የውሃ ስፍራ በ2008 ገንብቶ አጠናቀቀ። 70 በመቶ የሚሆነውንም ለግል ባለሃብቶች መሸጥ መቻሉን አስታወቀ።

ይሁን እንጂ በ2007 በዱባይ በተጀመረው እና እስከ 2010 ድረስ በዘለቀው በከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ምክንያት በደሴቶቹ ላይ የታቀዱት ፕሮጀክቶች የግንባታ ሥራ ተቋረጠ።

በዚህ ጊዜ ውስጥ ዱባይ በቤቶች ዋጋ ላይ ትልቅ ቅናሽ አስመዘገበች። ይህም ብዙ የግል አልሚዎች ዕቅዶቻቸውን ገታ እንዲያደርጉ ወይም እንዲሰርዙ አስገድዷቸዋል።

ናክሂልም በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ዕዳ ውስጥ ተዘፈቀ። የፕሮጀክቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታው አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ወቅት እአአ በ2009 ጎረቤት አቡዳቢ ደረሰች። አቡዳቢ 10 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ በማድረግ ኃላፊነቱን ከናክሂል ተረከበች።

ምን ተገነባ?

ለፕሮጀክቱ ትኩረት ለመሳብ በሚል ናክሂል በላፕላንድ ደሴት ማሳያ አዘጋጀ። አንድ ቤት ደግሞ ለስኬታማነቱ ዕውቅና ይሆነው ዘንድ ለፎርሙላ 1 የመኪና ውድድር የዓለም ሻምፒዮን ለነበረው ማይክል ሹማኽር በስጦታ አስረከበ።

እአአ በ2012 የሮያል አይስላንድ ቢች ክለብም በሊባኖስ ደሴት ተቋቋመ። ሬስቶራንቶች እና ባር ያሉት ሪዞርት ነው።

በ2022 ደግሞ አናንታራ የዓለም ደሴቶች ተከፈተ። ይህ ሪዞርት የሆቴል ክፍሎች፣ ቪላዎች እና ስፓዎችን ይዟል።

ቀሪዎቹ ደሴቶች ግን ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ አሸዋ ለብሰው ተቀምጠዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም የኒውካስል ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊ ፕሮፌሰር የሆኑት አልስተር ቦኔት የፕሮጀክቱ “አንዱ ትልቅ ችግር ከፓልም ደሴቶች በተለየ መልኩ ከዱባይ ጋር በመሬት ግንኙነት የሌለው መሆኑ ነው” ብለዋል።

“አንድ ሰው ወደ ደሴቶቹ በመኪና የሚደርስበት ድልድይ የለም። በተጨማሪም ደሴቶቹን የሚያገናኝ መሠረተ ልማት የላቸውም” ይላል።

አልሚዎች ሠራተኞችን እና ቁሳቁሶችን ወደ ግንባታ ቦታዎች ማጓጓዝ እና በደሴቶቹ ላይ ውሃ እና ኤሌክትሪክ ለማቅረብ ተቸግረዋል።

ጎብኚዎች ወደ ደሴቶቹ የሚሄዱበት ብቸኛው የሕዝብ ማመላለሻ ከፓልም ጁሜራህ የሚነሳው ጀልባ ብቻ ነው።

ለወደፊት ምን ተስፋ አለው?

በኦስትሪያዊው ሥራ ፈጣሪ ጆሴፍ ክላይንዲየንስት የተመሠረተው እና የሚመራው፣ መቀመጫውን በዱባይ ያደረገው ክላይንዲየንስት ግሩፕ ላለፉት አስርት ዓመታት “ዘ ኽርት ኦፍ ዩሮፕ” የተሰኘ ፕሮጀክት ላይ እየሠራ ነው።

አምስት ቢሊዮን ዶላር በማውጣት በጀርመን፣ በሞናኮ፣ በስዊድን እና በቬኒስ [የደሴቶቹ ስሞች ናቸው] ደሴቶች ላይ እጅግ ቅንጡ ሆቴሎች፣ የግል መኖሪያ ቤቶች እና ተንሳፋፊ ቪላዎች ለመገንባት ታቅዷል።

አየሩ በጣም ሲሞቅ ደግሞ ጎብኚዎች ሰው ሠራሽ በሆነ ዝናብ ስር የሚንቀሳቀሱበት “የዝናብ ጎዳና” አለው።

ፕሮጀክቱ በ2026 ይከፈታል ተብሎ ታቅዷል።

ናኪህል ሁሉንም 260 ደሴቶች ወደ “አህጉራቱ” የሚያገናኙ መሠረተ ልማቶችን እንዲሠሩ ተቋራጮችን እየቀጠረ ነው።

በመጀመሪያው ዕቅድ መሠረት እያንዳንዱ ደሴት የራሱ የኤሌክትሪክ እና የውሃ አቅርቦት እንዲኖረው ታስቦ ነበር። ይህ ግን በጣም ውድ እና ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ ነው።

ደሴቶቹን በመሠረተ ልማት የማገናኘቱ አንድ ዓላማም የኤሌክትሪክ እና የውሃ አቅርቦትን ከአንድ ማዕከል እንዲያገኙ ለማድረግ ነው።