ዚምባብዌ በአሜሪካ ምርቶች ላይ የተጣለውን ታሪፍ ልታነሳ ነው

የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋዋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋዋ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር "መልካም ግንኙነት" ለመፍጠር በሚል ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተጣሉ ታሪፎችን እንደሚያነሱ አስታወቁ።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚምባብዌ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ 18 በመቶ ታሪፍ ከጣሉ ከቀናት በኋላ ነው የዚምባብዌ መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው።

"ይህ እርምጃ ከአሜሪካ የሚገቡ ምርቶችን በዚምባብዌ ገበያ ውስጥ ለማስፋፋት እንዲሁም በምላሹ ዚምባብዌ ወደ አሜሪካ የምታደርገውን የወጪ ንግዷን ለማሳደግ ነው" ሲሉ ምናንጋዋ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።

ዚምባብዌ ቅኝ ግዛት ከወጣች በኋላ በጥቂት ነጮች ተይዞ የነበረውን መሬት ለአገሬው ጥቁር ህዝብ አከፋፍላለሁ በማለት ያወጣችው ፖሊሲ አሜሪካን ጨምሮ ከምዕራባውያን ጋር ያላት ግንኙነት እንዲሻክር አድርጓል።

ሁለቱ አገራት በአውሮፓውያኑ 2024 የነበራቸው የንግድ ልውውጥ 111.6 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደሆነ ከአሜሪካ መንግሥት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

አሜሪካ በዚሁ ዓመት ወደ ዚምባብዌ 43.8 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ንግድ ያደረገች ሲሆን ይህም ከዚያ ቀደም ከነበረው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 10.6 በመቶ ጭማሬ አለው።

ሆኖም ከዚምባብዌ ያስገባችው ምርት 67.8 ሚሊዮን ዶላር ቢሆንም ከቀደመው አመት 41 በመቶ አሽቆልቁሏል ተብሏል።

የዚምባብዌ መንግሥት ከአሜሪካ የሚገቡ ምርቶችን ታሪፍ ላለመጣል ያስተላለፈው ውሳኔ ለአገሪቱ ይህ ነው የሚባል ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደማያስገኝላት እና በተቃራኒው አሜሪካን ብቻ የሚጠቅም እንደሆነ የዚምባብዌ የፖለቲካ ተንታኝ ቴንዳይ ምባንጄ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ታዋቂው የዚምባብዌ ጋዜጠኛ እና የመንግሥት ተቺ ሆፕዌል ቺኖኖ በበኩሉ ፕሬዚዳንቱ የትራምፕን አስተዳደር "ለማስደሰት" እየሞከሩ ነው ሲል ወቅሷቸዋል።

አክሎም ምናንጋዋ የትራምፕ አስተዳደር በእርሳቸው ላይ የተጣለውን ማዕቀብ እንደሚያነሳ ተስፋ አድርገው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን "ይህ በጭራሽ የማይመስል ነው" ሲል ኤክስ ገጹ ላይ አስፍሯል።