ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፖሊስ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንትን በቁጥጥር ስር ለማዋል ያደረገው ሙከራ ከሸፈ
ፖሊስ ከስልጣናቸው የታገዱትን የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ዩን ሱክ ዮልን በቁጥጥር ስር ለማዋል ያደረገው ሙከራ ከጠባቂዎቻቸው ጋር ለስድስት ሰዓታት ከወሰደ አስገራሚ ፍጥጫ በኋላ ከሸፈ።
ወታደሮች እና የቀድሞው ፕሬዚዳንት የደህንነት መኮንኖች ዮን ሱክ ዮልን የሰው አጥር በመስራት ከለላ በመስጠት እንዲሁም ፖሊስ እንዳያልፍ መንገድ ለመዝጋት ተሽከርካሪዎችን መጠቀማቸውን የሃገር ውስጥ የዜና አውታር ዮንሃፕ ዘግቧል።
ስልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ወታደራዊ አገዛዝን አውጀዋል የተባሉት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዮን ምርመራ ተከፍቶባቸዋል።
ፕሬዚዳንቱ ለአጭር ጊዜ የቆየውን ይህንን ድንጋጌ በፓርላማው እምቢተኝነት ቢቀለብሱትም በተቃዋሚዎች በሚመራው ፓርላማ ከስልጣን እንዲታገዱ እና ክስ እንዲመሰረትባቸው ውሳኔ ላይ መደረሱ ይታወሳል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ለጥያቄ እንዲቀርቡ የቀረበላቸውን ሶስት ጥሪ አልቀበልም ማለታቸውን ተከትሎ የሴኡል ፍርድ ቤት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በቁጥጥር ስር ውለው እንዲቀርቡ ብያኔ አስተላልፏል።
ፖሊሶች ስኬታማ ቢሆኑ ዮን በደቡብ ኮሪያ ታሪክ ውስጥ ለመጀመረያ ጊዜ በስልጣን ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉ ፕሬዚዳንት ይሆኑ ነበር።
አርብ ከማለዳ ጀምሮ በማዕከላዊ ሴኡል ከሚገኘው የዮን መኖሪያ ውጭ በርካታ የፖሊስ መኪኖች በመንገድ ላይ ተሰልፈው ይታዩ ነበር። ጥዋት 2 ሰዓት ላይ ፖሊሶች እና የጸረ ሙስና ኮሚሽነሮች የተውጣጣ ቡድን የቀድሞውን ፕሬዚዳንት በቁጥጥር ስር ለማዋል ወደ ግቢው ተጠግተው ነበር።
በቁጥጥር ስር ለማዋል የተደረገው ሙከራ የተጀመረው በ20 ፖሊሶች የነበረ ቢሆንም ትንሽ ቆይቶ ቁጥራቸው ወደ 150 አድጎ ነበር። ይህም ቢሆን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ደህነንት ጠባቂዎች ቁጥር ከፖሊሶች በከፍተኛ ሁኔታ የበለጠ ነበር ተብሏል።
የቀድሞውን ፕሬዚዳንት በቁጥጥር ስር ለማዋል ከመጣው ቡድን ውስጥ ግማሽ ያህሉ ወደ ግቢው ውስጥ መግባት ቢችሉም ከጸጥታ ኃይል ጠባቂዎቻቸው ጋር ለሰዓታት ፍጥጫ ውስጥ ገብተው ነበር። ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን ቢለቁም አሁንም የሚጠብቋቸው ወታደሮች እና የደህንንት መኮንኖች ናቸው።
የዮን የደህንነት ቡድን ከመርማሪ መኮንኖች ጋር "ግጭት" ውስጥ ገብተው እንደነር የሴኡል ጠቅላይ አዛዥ ባለስልጣን ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተደረገው ሙከራ"በተግባር የማይቻል መሆኑን ወስነናል" ሰሉሉ የሙስና ምርመራ ቢሮው አስታውቋል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንቱ "በህጋዊ ሂደቱ" አለመገዛታቸው እንደሚያሳዝን ገልጾ ቀጣይ እርምጃዎች ከግምገማ በኋላ እንደሚወሰኑ ተገልጿል።