ትራምፕ በቫቲካን ከዜሌንስኪ ጋር ከተወያዩ በኋላ ፑቲን ለሰላም ያላቸው ፍላጎት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ገለፁ

ዶናልድ ትራምፕ እና ዜሌንስኪ

የፎቶው ባለመብት, Andriy Yermak/Telegram

ዶናልድ ትራፕም የዩክሬኑ አቻቸውን ቮሎድሚር ዜሌንስኪን በፖፕ ፍራንሲስ ቀብር ላይ አግኝተው ካነጋገሩ በኋላ የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱን ለማቆም ያላቸው ፍላጎት ላይ ጥርጣሬ እንደገባቸው ገለፁ።

ትራምፕ ሮምን ለቅቀው ከሄዱ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ "ፑቲን ሰላማዊ ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ ሚሳዔል የሚተኩስበት አንዳችም ምክንያት የለም" ያሉ ሲሆን "እያታለለኝ ሳይሆን አይቀርም" ብለዋል።

የሮማው ሊቀ ጳጳስ ቀብር ከመፈጸሙ በፊት የተገናኙት ዶናልድ ትራምፕ እና ዜሌንስኪ በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስትያን ውስጥ ጥልቅ ውይይት ሲያደርጉ ተስተውለዋል።

ዋይት ሐውስ ሁለቱ መሪዎች ያደረጉትን የ15 ደቂቃ ውይይት "በጣም ውጤታማ" ሲል ገልጾታል። የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው "ታሪካዊ የመባል አቅም ያለው" ሲሉ ውይይታቸውን አንቆለጳጵሰዋል።

ሁለቱ መሪዎች በዋይት ሐውስ የነበራቸው ውይይት ባለመግባባት ከተቋጨ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው ፊት ለፊት የተገናኙት።

በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ሩሲያ በዩክሬን ከተሞች ላይ ስለፈጸመችው ጥቃት የጻፉት ዶናልድ ትራምፕ "ምናልባት ጦርነቱን ማቆም አይፈልግ ይሆናል ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል። እያታለለኝ ሳይሆን አይቀርም፤ ስለዚህ በተለየ ሁኔታ መስተናገድ አለበት በ'ባንክ' ወይንም 'በሁለተኛ ደረጃ ማዕቀብ'? በጣም ብዙ ሰው እየሞተ ነው።" ብለዋል።

አርብ ዕለት የአሜሪካው ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ጋር መወያየታቸውን ተከትሎ ትራምፕ ሩሲያ እና ዩክሬን "ስምምነት ላይ ለመድረስ በጣም ተቃርበዋል" ብለው ነበር።

ቅዳሜ ዕለት ክሬምሊን በበኩሉ ፑቲን ለአሜሪካው ልዑክ ዊትኮፍ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር "ያለምንም ቅድመ ሁኔታ" ቀጥተኛ ውይይት ለመጀመር ዝግጁ መሆኗን ማረጋገጣቸውን ገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ እና ዜሌኒስኪ በዋይት ሐውስ ተገናኝተው ፍሬ አልባ ውይይት ካደረጉ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው በሮም ፊት ለፊት የተገናኙት።

በወቅቱ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ለዩክሬኑ አቻቸው ሩሲያን ለማሸነፍ "ምንም የቀረህ አማራጭ የለም" ብለዋቸው ነበር።

በዚህ ሳምንትም ያንኑ ተመሳሳይ መልዕክት የደገሙት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ የዩክሬኑ መሪ "የቀረው አማራጭ የለም" ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ ዩክሬንን ጦርነት በመጀመር እና ለሰላም ስምምነቱ እንቅፋት አድርገው ሲከስሷት ተሰምተዋል።

ቅዳሜ ዕለት የሁለቱ አገራት መሪዎች በሮም ያደረጉትን ውይይትን በተመለከተ ዋይት ሐውስ አዎንታዊ ድምጸት የያዘ መልዕክት ሲያስተላልፍ፣ ዜሌንስኪ በበኩላቸው "በጋራ ውጤት ማምጣት ከቻልን ታሪካዊ ሊባል የሚችል በጣም ትዕምርታዊ የሆነ ውይይት" ብለውታል።

ሁለቱ መሪዎች ፊት ለፊት ተቀምጠው በጥልቀት ሲወያዩ የሚያሳይ ምስልም ይፋ ሆኗል።

የዩክሬን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አድሪ ሲቢሃ በኤክስ ገጻቸው ላይ ምስሉን ያጋሩ ሲሆን "ይህንን ታሪካዊ ውይይት ለመግለጽ ምንም ዓይነት ቃላት አያስፈልግም። ሁለቱ መሪዎች በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስትያን ለሰላም እየሰሩ ነው" ብለዋል።

ትራምፕ ከዩክሬኑ አቻቸው ጋር በሮም ፊት ለፊት ከተወያዩ በኋላ ያንጸባረቁት አቋም ከዚህ በፊት ዜሌንስኪን በጠንካራ ቃላት ሲሸነቁጡ፣ስለ ፑቲንን ደግሞ አዎንታዊ አስተያየት ሲሰጡ ከነበረበት በተቃራኒው የቆመ ነው።

ዜሌንስኪ በቴሌግራም ገጻቸው ላይ "ጥሩ ውይይት ነበር። አንድ ለአንድ የተደረገ ጥሩ ውይይት ነበር። ብዙ ነገር ተነጋግረናል።የተነጋገርናቸው ነገሮች በሙሉ ውጤታማ ይሆናሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።

አክለውም ውይይታቸው ያተኮረው "የሕዝባቸውን ሕይወት መታደግ፣ ምንም ቅድመ ሁኔታ የሌለበት ሙሉ ተኩስ አቁም እና በተደጋጋሚ የሚከሰት ጦርነትን የሚከላከል አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም" ላይ እንደነበር ገልጸዋል።

ዜሌንስኪ አክለውም " በጋራ ድሎችን ማስመዝገብ ከቻልን ታሪካዊ ሊባል የሚችል ትዕምርታዊ ውይይት ነበር ያካሄድነው። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አመሰግናለሁ!" ብለዋል።

ሁለቱ መሪዎች ከተወያዩ በኋላ ከቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ውጪ ከሌሎች የዓለም መሪዎች ጋር ተገናኝተዋል።

ትራምፕ ሞስኮን እና ኪየቭን የተኩስ አቁም ላይ እንዲደርሱ እና የሰላም ስምምነት እንዲያደርጉ ጫና ሲያደርጉ ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ በፊት የሁለቱ አገራት መሪዎች በቅርቡ የሰላም ስምምነት ላይ የማይደርሱ ከሆነ አስተዳደራቸው ራሱን ከጉዳዩ ላይ እንደሚያርቅ አስጠንቅቀው ነበር።