ቱርክ ወደ ሶማሊያ የላከችውን ወታደራዊ ቁሳቁሶች የጫነች መርከብ በፑንትላንድ በቁጥጥር ሥር ዋለ

የፎቶው ባለመብት, Puntland government
የሶማሊያ አንድ ግዛት የሆነችው የፑንትላንድ ከቱርክ ለሶማሊያ መንግሥት የተላኩ ከፍተኛ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን የጫነች መርከብ መያዙ በሁለቱ ወገኖች መካከል ውዝግብ አስከትሏል።
በዚህም የተነሳ የሶማሊያ መንግሥት የፑንትላንድ አስተዳደር በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ወታደራዊ ጭነት የያዘችውን መርከብ መያዙ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ላይ የተፈጸመ ጥሰት እና የባሕር ላይ ውንብድና ፈጽሟል በሚል ወንጅሏል።
የፌደራሉ መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ የተያዘው መርከብ በሶማሊያ እና በቱርክ መካከል በተደረገው የመከላከያ ትብብር ስምምነት መሠረት የቱርክ ሶማሊያ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ (ቱርክሶም) ንብረት የሆኑ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን እያጓጓዘ ነበር ብሏል።
የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጭነቱ በሕጋዊ መንገድ እና የአገሪቱንም ሆነ ዓለም አቀፍ ሕጎችን የተከተለ መሆኑን ተናግረዋል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ ምሥሎች በፑንትላንድ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋለችው የኮሞሮስ ደሴቶች ሰንደቅ ዓላማን የምታውለበልብ ወርልድ የተሰኘች የጭነት መርከብ ወታደራዊ እና የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጪ ተሽከርካሪዎችን ጭና ትታያለች።
መርከቧ በፑንትላንድ የባሕር ኃይል ፖሊስ ኃይል የተያዘች ሲሆን፣ እአአ ሐምሌ 18 በአሉላ ዲስትሪክት ሰሜን ምሥራቅ ወደብ አካባቢ ወሳኝ በሆነው የኤደን ባሕረ ሰላጤ ባሬዳ የባሕር ዳርቻ ላይ መልህቋን እንድትጥል ተደርጋለች።
የፑንትላንድ የማስታወቂያ ሚኒስቴር እርምጃውን በመደገፍ የፀጥታ ስጋት ተደርገው ሊታዩ የሚችሉ የጦር መሳሪያዎችን በመያዝ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሶማሊያ ግዛት በመግባት የዓለም አቀፍ የባሕር ላይ ሕግጋትን ጥሳለች ሲል ገልጿል።
ፑንትላንድ በተጨማሪ መርከቧ የምትንቀሳቀሰው ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድኖች በሚንቀሳቀሱበት የግጭት ቀጠና ተብሎ በተፈረጀ አካባቢ ሲሆን፣ በዚህም በፑንትላንድ መረጋጋት እና ደኅንነት ላይ ቀጥተኛ ስጋት ፈጥሯል ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Rich Tedd/X
ግጭቱ በሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት እና በፌዴራል አባል አገራቱ መካከል ያልተለመደ እና ከባድ አለመግባባት መፈጠሩን ያሳያል።
በአሁኑ ውዝግብም የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ የአገሪቱ አባል የሆነ ግዛት ኃይሎችን በባሕር ላይ ውንብድና ወንጅሏል።
ሲ ወርልድ በመባል የምትጠራው መርከቧ "ያለምንም ቅድመ ሁኔታ፣ በፍጥነት" እንድትለቀቅ የሶማሊያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ላይ ጠይቋል።
አክሎም መርከቧ " ለመከላከያ ዓላማ የሚውል ሕጋዊው ጭነት" መያዟን በመግለጽ ዓላማውም "ለአገሪቱ፣ ፑንትላንድን ጨምሮ መረጋጋት እና ፀጥታ" ታቀደ መሆኑን አስታውቋል።
የሶማሊያ መንግሥት ፑንትላንድን ጨምሮ ሁሉም የፌዴሬሽኑ አባል የሆኑ ክልሎች የባሕር አስተዳደር እና መከላከያን በተመለከተ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርቧል።
የፑንትላንድ አስተዳደር የጦር መሳሪያ እና የጦር መኪኖችን የጫነችው መርከብ "በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሌላ ግዛት የባሕር ክልል መግባት እንደማይችል የሚገልጸውን ዓለም አቀፍ ደንብጥሳለች፤ በተለይም ለፀጥታ ስጋት ሊፈጥር የሚችል በግልጽ የሚታይ ጦር መሳሪያ ጭና ነበር" ሲል ገልጿል።
በሶማሊያ ፌደራል መንግሥት እና በፑንትላንድ ክልላዊ መስተዳደር መካከል ከዚህ ቀደምም አለመግባባት ተከስቶ ፍጥጫ ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ በመካከላቸው ያለው ችግር አሁንም መፍትሄ አላገኘም።
ሶማሊያ ባለፈው ዓመት ከቱርክ ጋር ወታደራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ትብብር ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሷ የሚታወስ ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት በመርከብ እና በአውሮፕላን የጦር መሳሪያ ከቱርክ በኩል እየቀረበላት ነው።















