በሙዚቃው የተለያዩ ትውልዶችን ያስተሳሰረው ጌታቸው ካሳ አረፈ

‘አገሬን አትንኳት’፣ ‘አዲስ አበባ’ እና ‘ትዝታ’ በተሰኙ ሙዚቃዎቹ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈው አንጋፋው ሙዚቀኛ ጌታቸው ካሳ ከዚህ ዓለም ማረፉ ተሰማ።

ሙዚቀኛው ባደረበት ህመም በየካቲት 12 ሆስፒታል በህክምና ሲረዳ ቆይቶ የካቲት 12/ 2016 ዓ.ም ሌሊት ሕይወቱ አልፏል።

በሙዚቃው የተለያዩ ትውልዶችን ማስተሳሰር የቻለው ጌታቸው ካሳ በኢትዮጵያ ሙዚቃ በነገሰበት የአምስት አስርት ዓመታት ቆይታውም አይረሴ የሚባሉ ሙዚቃዎችን አበርክቷል።

‘እወድሻለሁ’፣ ‘ትዝ ባለኝ ጊዜ’፣ ‘የከረመ ፍቅር’፣ ‘ውበትም ይረግፋል’፣‘አትጥፊ ከጎኔ’ እና ሌሎችን ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዎችን የተጫወተው ጌታቸው ምን ያህል ዘፈኖችን እንደሰራም በትክክል ቁጥሩን እንደማያውቀው በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር።

ጌታቸው ለየት ባለ ድምጹ እና ቅላጼው፣ በመድረክ ውዝዋዜው፣ የአዘፋፈን ስልቱ የራሱን አሻራ በኢትዮጵያ የሙዚቃ መድረክ መፍጠር የቻለ አርቲስት እንደሆነ ይነገርለታል።

ወርቃማ ተብሎ በሚጠራውም የኢትዮጵያ የሙዚቃና የሥነ ጥበብ ታሪክ ላይ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ይመሰክሩለታል።

በዓለማችን ውስጥ ስመ ጥር ከሆኑ እና ታላላቆቹ የሙዚቃ ጸሐፊ ከሚባሉት ውስጥ የሆነው አንዱ ቦብ ዲለንም ምርጥ ካላቸውም የሙዚቃ ስራዎች አንዱ የጌታቸው ካሳ ‘ትዝታ’ የሚለው ሙዚቃ እንደሆነ የሰፈረ ሲሆን ራሱ ጌታቸውም ስለዚህ ጉዳይ ተናግሮ ነበር።

ሙዚቀኛው ለ28 ዓመታት ገደማ ኑሮውን በአሜሪካ አድርጎ የነበረ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያም የተመለሰው ከአስር ዓመት በፊት ነበር።

ወደ ኢትዮጵያም ከተመለሰ በኋላ በተለያዩ መድረኮች ስራውን ያቀርብ ነበር።

በአዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ ተወልዶ ያደገው ጌታቸው ሙዚቃን መጫወት የጀመረው ገና በልጅነቱ ነበር።

በወቅቱ ታዋቂ የነበሩትን የጃዝ እና የሶል ሙዚቀኞች የነበሩትን የነ ሃሪ ቤላፎንቴ፣ ስቲቪ ወንደር እና የመሳሰሉ አፍሪካ አሜሪካውያን ዘፈኖችን አስመስሎ በመጫወትም ነበር ወደ ሙዚቃ ሕይወት የገባው።

የሙዚቃ ሕይወቱ በአባቱ ዘንድ ተቀባይነት ባለማግኘቱና እና አባቱም በእሳቸው ስም [በጸጋዬ] እንዲጠራ ባለመፈለጋቸው ጌታቸው የአባቱን ስም ለመለወጥ ተገዶ ነበር።

በአንድ ወቅት ፍቅረኛው የነበረችውን እና ዘፋኝ የነበረችውን አሰገደች ካሳ አባት ስምም በመውሰድ መጠሪያውን ጌታቸው ካሳ በሚል ቀየረ።

በኋላም ሂልተን ሆቴል ከዋልያስ ባንድ ጋር እየተጫወተ በነበረበት፣ በአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ ወቅት አባትየውን እንደጋበዛቸውና ተጸጽተው እንደተቀበሉትም ተናግሯል።

ከዚያም በኋላ በደረሰበት የሙዚቃ ስኬቱ አባቱ ይኮሩበት እንደነበር አስረድቷል።

ጌታቸው በፓትሪስ ሉምምባ ክለብ ውስጥ እየሰራ በነበረበት ወቅት ነው ታዋቂውን እና የመጀመሪያ የሆነውን ዘፈኑን ‘እመኛለሁ’ን ያወጣው።

ከዚያም በኋላ ያወጣቸው ‘የከረመ ፍቅር’ ‘ ትዝታ’ እና ሌሎችም ዘፈኖቹ ታዋቂነትን አስገኝተውለታል።

ከዘፈን በተጨማሪ በቬነስ፣ ዋሊያስ እና ኢትዮ ስታር ባንዶችም ቆይታውም ከበሮ ይጫወት ነበር።

አሜሪካም በአውሮፓውያኑ 1981 ወደ አሜሪካ ከሄደ በኋላ ለስድስት ዓመታት ያህል ‘ እወድሻለሁ’ እና ‘ አዲስ አበባ’ የሚሉ ዘፈኖቹንም እየሰራ ነበር።

ኢትዮጵያም ተመልሶ ከመጣ በኋላም እነዚህ ተወዳጅ የሆኑት ሙዚቃዎቹ ወጡ።

ተመልሶም ወደ አሜሪካ ከሄደ በኋላ ለሁለት አስርት ዓመታት በኖረባት አሜሪካ በታዋቂዎቹ ኢትዮጵያውያን ሬስቶራንቶች ብሉ ናይል፣ አዲስ አበባ፣ ዱከም፣ እቴቴ፣ ኩዊን ሼባ ሬስቶራንቶች ይጫወት ነበር።

ለሙዚቃው ባደረገውም አስተዋጽኦ በአሜሪካ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን የሕይወት ዘመን ሽልማት አበርክተውለታል።

‘ትዝታ’ የሚለው ሙዚቃው ‘ጎልደን ይርስ ኦፍ ሞደርን ሚዪዚክ’ በሚል ስብስብ ውስጥ በቡዳ ሬከርድስ አሳታሚነት፣ በፍራንሲስ ፋልሴቶ አማካኝነት ኢትዮፒክስ በሚለው አልበም ተካትቶ ሙዚቃው በመላው ዓለም ተሰሚነት እንዲኖረው አድርጎታል።

ነገር ግን ‘ያለኔ ፈቃድ ነው’ ሙዚቃዬ የወጣው በሚልም ክስ እንደመሰረተ ጌታቸው በቅርቡ ከኢቢኤስ ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሮ ነበር።

ትዝታ (እኔስ አልከፋ ) የሚል መጠሪያ ያለው ሙዚቃው መጀመሪያ የታተመው ጌታቸው ከዋልያስ ባንድ ጋር እየተጫወተ በነበረበት ወቅት ነው። የሙዚቃውም አሳታሚ የአምሐ ሬከርድስ ባለቤት አምሐ እሸቴ ነበር።

አንጋፋው ሙዚቀኛ ጌታቸው የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነው።