ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአዲስ አበባ ድርድር በታሰበበት ጊዜ በካርቱም በተፈጸመ የአየር ጥቃት ቢያንስ 22 ሰዎች ተገደሉ
የሱዳን መንግሥት ጦር ሠራዊት በዋና ከተማዋ ካርቱም በፈጸመው የአየር ጥቃት ቢያንስ 22 ሰዎች ሲገደሉ፣ በርካቶች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የዐይን እማኞች እና ባለሥልጣናት አስታወቁ።
የአየር ጥቃቱ ቅዳሜ ዕለት በካርቱም የአባይ ወንዝ ዳርቻ ተቃራኒ ወገን በሚኘው የኦምዱርማን አካባቢ የተጸፈመው ሲሆን፣ በጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል ሴቶች እና ሕጻናት እንደሚገኙበት የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህ በርካታ ሰዎች የተገደሉበት የአየር ጥቃት የተፈጸመው፣ ሱዳን አባል በሆነችበት ቀጠናዊው ድርጀት ኢጋድ አማካይነት አዲስ አበባ ላይ ሰኞ ዕለት የሰላም ንግግር ይጀመራል ተብሎ እየተነገረ ባለበት ጊዜ ነው።
ሦስት ወራትን ሊያስቆጥር በተቃረበው በአገሪቱ ጦር ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል እየተካሄደ ባለው ውጊያ፣ ሁለቱም ኃይሎች ዋና ከተማዋን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ለማስገባት እየተፋለሙ ነው።
ሱዳንን ወደ ከባድ የእርስ በርስ ጦርነት ያስገባት ቀውስ የተቀሰቀሰው፣ የአገሪቱ ጦር ሠራዊት አዛዥ በሆኑት ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪ በመሆኑት ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ መካከል በቀጣይ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ላይ በተፈጠረ አለመግባባት ነው።
የካርቱም አካባቢ የጤና ባለሥልጣናት በቅዳሜው አየር ጥቃቱ ቢያንስ 22 ሰዎች መገደላቸውን ለሮይተርስ የዜና ወኪል የተናገሩ ሲሆን፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ግን የሟቾች ቁጥር 31 ነው ብሏል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የተፈጸመውን የአየር ጥቃት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣ ጥቃቱ “በመኖሪያ ቤቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳትን አድርሷል።”
አንደኛው ተፋላሚ ወገን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የካርቱምን፣ የኦምዱርማንን እና የባህሪ ከተሞችን አብዛኞቹን ክፍሎች ተቆጣጥሮ ይገኛል።
በዚህም ሳቢያ የሱዳን ጦር ሠራዊት ከከተሞቹ ተቀናቃኙን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ለማስወጣት ተደጋጋሚ የመድፍ እና የአየር ድብደባዎችን ሲፈጽም ቆይቷል።
ትናንት ቅዳሜ ዕለት የተፈጸመው የአየር ጥቃት አስካሁን በከተሞች አካባቢ ከተፈጸሙት ተመሳሳይ ጥቃቶች ሁሉ በአንድ ጊዜ ከፍተኛ የሞት መጠን የተመዘገበበት ሳይሆን አይቀርም ተብሏል።
በሚያዝያ መጀመሪያ ሳምንት ተቀስቅሶ አስካሁን ድረስ በዘለቀው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት፣ የዋና ከተማዋ ካርቱም ነዋሪዎች ባልተቋረጠ ስጋት ውስጥ ይገኛሉ።
በካርቱም ውስጥ በአሁኑ ወቅት ሱቆች እና የገበያ ስፍራዎች አልፎ አልፎ ብቻ የሚከፈቱ ሲሆን፣ ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር ደረጃ በከተማዋ ያሉ የሕክምና ተቋማት ተዘግተዋል።
ጦርነቱ ከዋና ከተማዋ ባሻገር የዳርፉር ክልልን ጨምሮ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የተስፋፋ ሲሆን፣ በምዕራብ ዳርፉር ውስጥም የጎሳ ግጭት ተከስቷል።
በዚህ ጦርነት ምክንያት አስካሁን በተለያዩ የሱዳን ክፍሎች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፣ ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከቤታቸው ለመፈናቀል ተገደዋል።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በአሜሪካ እና በሳዑዲ አረቢያ አሸማጋይነት በተፋላሚ ኃይሎቹ መካከል ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት በተደጋጋሚ ቢደረስም ውጤታማ ሳይሆን ውጊያው ቀጥሏል።
አሁን ደግሞ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት - ኢጋድ በሱዳን ኃይሎች መካከል የሚደረግ የሰላም ስምምነት አዲስ አበባ ላይ ሰኞ ዕለት ለመጀመር ጥረት እያደረገ ነው።
ነገር ግን የሱዳን ጦር ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል አል ቡርሐን በሰላም ንግግሩ ላይ እንደማይሳተፉ ቃል አቀባያቸው መግለጹ ተዘግቧል።