ፌስቡክና ዲዝኒን ጨምሮ የአሜሪካ ተቋሞች ፅንስ የሚያቋርጡ ሠራተኞቻቸውን የጉዞ ወጪ እንሸፍናለን አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ግዙፍ ተቋሞች ሠራተኞቻቸው ፅንስ ማቋረጥ ከፈለጉ የጉዞ ወጪያቸውን እንደሚሸፍኑላቸው አስታወቁ።
ዲዝኒ፣ ጄፒ ሞርጋን፣ ፌስቡክ (ሜታ) እና ሌሎችም ታዋቂ መሥሪያ ቤቶች የተቀጣሪዎቻቸውን የጉዞ ወጪ ለመሸፈን ቃል ገብተዋል።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፅንስ ማቋረጥ የሚፈቅደውን የሕገ መንግሥት አንቀጽ መሻሩ ይታወሳል።
ውሳኔውን ተከትሎ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ሴቶች የፅንስ ማቋረጥ አገልግሎት ማግኘት አይችሉም።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ፅንስ ማቋረጥን ሕገ ወጥ ያደረጉ የአሜሪካ ግዛቶች አሉ።
በሌላ በኩል ፅንስ ማቋረጥ ሕጋዊ ሆኖ እንደሚቀጥል ያስታወቁ ግዛቶችም አሉ።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ፣ በርካታ የአገሪቱ ተቋሞች ሠራተኞቻቸው ፅንስ ማቋረጥ ሕጋዊ ወደሆነባቸው ግዛቶች መሄድ ሲያስፈልጋቸው፣ የጉዞ ወጪያቸውን በጤና መድኅን ሥር እንደሚሸፍኑ አስታውቀዋል።
ዲዝኒ ለሠራተኞቹ በሰጠው መግለጫ “የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ እንገነዘባለን። ከሥነ ተዋልዶ ጤና ጋር የተያያዙ የሕክምና አገልግሎቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የምታገኙበት ዕድል እናመቻቻለን” ብሏል።
የዲዝኒ 80,000 ሠራተኞች የሚገኙት ፍሎሪዳ ነው።
የፍሎሪዳ አገረ ገዢ ከሐምሌ 1 ጀምሮ የሚተገበር እና ከ15 ሳምንታት እርግዝና በኋላ ፅንስ ማቋረጥን የሚከለክል ሕግ አጽድቀዋል።
የባንክ ተቋሙ ጄፒ ሞርጋን ለሠራተኞቹ በሰጠው መግለጫ “ሕጋዊ ፅንስ ማቋረጥን ጨምሮ ለሌሎችም የሕክምና አገልግሎቶች የጉዞ ወጪ እንሸፍናለን። ለሠራተኞቻችን ደኅንነት ቅድሚያ እንሰጣለን። ሁሉም የሕክምና አገልግሎት እኩል ተደራሽነት እንዲኖረው እንፈልጋለን” ብሏል።
የኢንቨስትመንት ባንኩ ጎልድማንስ ሳችስ እንዳለው፣ ከሐምሌ 1 ወዲያ ወደሌላ የአሜሪካ ግዛት ሄደው ፅንስ ማቋረጥ ለሚፈልጉ ሠራተኞቹ የጉዞ ወጪ ይሸፍናል።
መጠሪያውን ወደ ሜታ የተቀየረው ፌስቡክ በበኩሉ፣ ሠራተኞቹ ፅንስ ለማቋረጥ ለሚያደርጉት ጉዞ የሚያወጡትን ወጪ እንደሚሸፍንላቸው ገልጿል።
የቮግ መጽሔት አሳታሚ ኮንዴ ናስር፣ ጂንስ አምራቹ ሌቪ ስትራውስ እንዲሁም የመጓጓዣ አገልግሎት የሚሰጡት ሊፍት እና ኡበርም ለሠራተኞቻቸው ተመሳሳይ ውሳኔ አስተላልፈዋል።
ሊፍት ሠራተኞቹ ፅንስ ማቋረጥን በተመለከተ የፍርድ ቤት ክስ ከገጠማቸው እንደሚከላከላቸውም አስታውቋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፅንስ ማቋረጥን ሊሽር እንደሚችል የሚጠቁም መረጃ ከወራት በፊት ሾልኮ ሲወጣ፣ አማዞን፣ የተለያዩ መረጃዎች የሚሰጠው ድረ ገጽ የልፕ፣ ሲቲግሩፕ ባንክ እና ሌሎችም ተቋሞች ሠራተኞቻቸው ፅንስ ቢያቋርጡ እንደሚደግፏቸው መግለጻቸው አይዘነጋም።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሮው ቪ ዌድ የተባለውን ፅንስ ማቋረጥን የሚፈቅደውን የሕግ አንቀጽ ከሻረ በኋላ 13 የአሜሪካ ግዛቶች ፅንስ ማቋረጥን በሕግ አግደዋል።
20 ግዛቶች ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎትን ለመገደብ እንቅስቃሴ መጀመራቸውም ተገልጿል።
ፅንስ ለሚያቋርጡ ሠራተኞቻቸው የጉዞ ወጪ ለመሸፈን ቃል የገቡ ተቋሞች፣ ፅንስ ማቋረጥን ከሚነቅፉ ሪፐብሊካኖች ተቃውሞ ይጠብቃቸዋል።
የቴክሳስ ሕግ አውጪዎች ሲቲግሩፕ እና ሊፍትን ከወዲሁ እያስፈራሩ ነው።












