በአሜሪካ ፅንስ የሟቀረጥ መብት መሻር በሌሎች አገራት የፈጠረው የተደበላለቀ ስሜት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በትናንትናው ዕለት የፅንስ ማቋረጥን ሕገ መንግሥታዊ መብትን መሻር በተለያዩ አገራት የተቀላቀሉ ስሜቶችን እያስተናገደ ነው።
ፅንስ ማቋረጥን በሚደግፉም ሆነ በማይደግፉ ተሟጋቾች የአሜሪካ ፍርድ ቤት ውሳኔ ለአገሪቷ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ለተቀረው ዓለምስ ምን አይነት መልዕክት ያስተላልፋል በሚለው ጉዳይ ላይ አስተያየቶቻቸውን እየሰጡ ነው።
በጣሊያን፣ በኤልሳልቫዶር፣ በህንድ፣በአየርላንድና በካናዳ የሚገኙ የቢቢሲ ዘጋቢዎች በየአገራቱ የፈጠረውን የተደበላለቀ ስሜት ዘግበውታል።
የአሜሪካ ውሳኔ በጣሊያን አዲስ ውይይት ከፍቷል- ማርክ ሎወን ከሮም ጣሊያን
አሜሪካ ሮ ቨርሰስ ዌድ የተሰኘውን የፅንስ ማቋረጥን መብት ሕጋዊ ካደረገችበት ከአውሮፓውያኑ 1978፣ ከአምስት ዓመታት በኋላ ነው ጣሊያን ሕጋዊ ያደረገችው። ለአመታት ያህል የፅንስ ማቋረጥ መብት በጣሊያን ፖለቲካዊ ጉዳይ ባይሆንም በሕዝቡ ከፍተኛ መሰረት ካለው ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ጠንካራ ቀኝ አክራሪና ወግ አጥባቂ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማቆጥቆጥ እንደገና ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔም በጣሊያን የፅንስ ማቋረጥ መብት እንደ አዲስ መወያያ እንዲሆን አድርጎታል።የግራ ዘመም ፖለቲከኞች ውግዘት እና ማስጠንቀቂያን አስተላልፈዋል። የጣሊያን ፅንስ የማቋረጥን ሕግ 194ን እንዲጸድቅ ከረዱት መካከል አንዷ የሆኑት የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤማ ቦኒኖ በጣሊያን ወደ ኋላ የመመለስ ስሜትን ፈጥሯል ብለዋል። “ቋሚ የሚመስሉ ስኬቶችን የማጣት አደጋን ያሳያል” ብለዋል።
በአንዳንድ ቀኝ አክራሪዎችና ወግ አጥባቂዎች በኩል እንደ ድል የታየ ሲሆን “ታላቅ ድል ሲሉ” የቀኝ አክራሪ አባል የሆኑት ሲሞን ፒሎን ተናግረው፣ ጣሊያን እንዲሁም አውሮፓ ይህንን ውሳኔ ይከተላሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ሆኖም የፓርቲያቸው መሪ ማትዮ ሳልቫኒ “በእርግዝና ወቅት የመጨረሻው ውሳኔ የሴቲቱ ነው” ብለው እንደሚያምኑ በመግለፅ፣ በርካታ ጣሊያናውያን ፅንስን የማቋረጥ መብት በበርካታ ጣሊያናውን እንደሚደገፍ እውቅናን የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በአየርላንድ የፈጠረው ፍራቻ- ኤማ ቫርዲ የቢቢሲ አየርላንድ ዘጋቢ
በአየርላንድ ደሴት የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ፈጣን ምላሽ እና ጥልቅ ስሜትን ቀስቅሷል። በአየርላንድ በቅርቡ ነው ፅንስ ማስወረድ ከወንጀለኝነት እንዲወጣ የተደረገው። ከዚህም ጋር ተያይዞ በሁለቱም ወገን በኩል ድምፃቸው ጎልቶ የሚሰማ ተሟጋቾች አሉ።
“አሜሪካ በማትታወቅ መልኩ እየተቀየረች ባለበት ሁኔታ ዓለም መመልከቱን ቀጥሏል” በማለት በአውሮፓውያኑ 2018 በደብሊን ውስጥ የአየርላንድ ሪፐብሊክ ፅንስ ማቋረጥ በተፈቀደበት ውስጥ ደስታቸውን ለመግለፅ ወጥተው የነበሩና የዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ጄኒፈር ካሲዲ በትዊተር ላይ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በርካቶችም ገና ደስታቸውን ሳያጣጥሙ አሁን በአሜሪካ እየተመለከቱት ባለው ነገር ፍርሃታቸውን እየገለጹ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2012 በአየርላንድ ሴፕሲስ የፅንስ ማቋረጥ ስላልተፈቀደላት ሕይወቷ ያለፈውን ሳቪታ ሃላፓናቫር ታሪክንም እንደ አዲስ እያጋሩ ነው።
አሜሪካውያንም ለበርካታ ተመሳሳይ ሞት ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ በአየርላንድ በርካቶች እያስጠነቀቁ ነው።
በሰሜን አየርላንድ የፅንስ ማቋረጥ መብትን ለማስከበር ከፍተኛ ትግል ያደረጉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ባልደረባ ግራይን ታጋርት “አሳፋሪ ውሳኔ” ብለውታል።
ነገር ግን በአየርላንድ የፅንስ ማቋረጥ ሕጋዊነት የተበሳጩ ተሟጋቾች እንደገና እንዲበረታቱ በር ከፍቷል። ከአሜሪካም በርካታ የምንማረው ነገር አለ በማለትም መልዕክታቸውን እያስተላለፉ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወግ አጥባቂ ቡድኖች ተበረታተዋል- ዊል ግራንት፣ ሳን ሳልቫዶር፣ ኤል ሳልቫዶር
በላቲን አሜሪካ ፅንስ የማቋረጥ መብትን ለማስፈን እየታገሉ ያሉ በርካታ ተሟጋቾች የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሮ ቨርሰስ ዌድ ላይ ያስተላለፈው ብይን ትግሉን ሊያጨናግፈው ይችላል በሚል ስጋታቸውን እያጋሩ ነው።
በኤል ሳልቫዶር ግንባር ቀደም የፅንስ ማቋረጥ መብት ተሟጋች የሆኑት ማሪያና ሞይሳ "ይህ በአገራችን ያሉ ወግ አጥባቂ ቡድኖችን ያበረታታል" ሲሉ ተናግረዋል።
በኤልሳልቫዶር በማንኛውም ሁኔታ ፅንስ ማቋረጥ አይቻልም። ሌሎች አገሮች በሚፈቅዷቸው የእናቲቱ ሕይወት አደጋ ውስጥ ቢገባም፣ በመደፈርም ወይም በዘመዶች መካከል የተፈጠረ ግንኙነት ቢሆንም አይቻልም።
“ሴቶች እና ታዳጊዎችን የሰብዓዊ መብት በመንፈግ የጥቃት ውጤት የሆኑ ልጆች እንዲወልዱ ማስገደድ” ነው ሲሉ ከወዲሁ ተመጣጣኝ ባልሆነ መልኩ በኅብረተሰቡ ወስጥ በጣም ድሃ የሆኑትን ማኅበረሰብ ይጎዳል ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኤልሳልቫዶርን ፓርላማ የሚቆጣጠሩት ፅንስን ማቋረጥ የሚቃወሙ ፖለቲከኞች ውሳኔውን በደስታ ተቀብለው በዚህ ላይ ያላቸው የጸና አቋም በአሜሪካ አህጉር ዋነኛ አቋም እንደሆነም አጥብቀው ገልጸዋል።
አሳዛኝ ውድቀት - ሮቢን ሌቪንሰን ኪንግ፣ ቶሮንቶ፣ ካናዳ
ካናዳ አብዛኛውን ጊዜ በጎረቤት አገሮች በተለይም በትልቋ የንግድ ሸሪክ በሆነችው አሜሪካ ጉዳይ ጣልቃ መግባት አትወድም።
ነገር ግን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ የካናዳው ተራማጅ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶን ዝም እንዲሉ አላስቻላቸውም “አሳዛኝ ውድቀት” እንዲሁም ለሴቶች አስፈሪ ነው ብለውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት በኪጋሊ ሩዋንዳ በተካሄደው የኮመንዌልዝ ስብሰባ ላይ ሲሆን “በእውነቱ ለመናገር፣ በሁሉም ሰው ነፃነት እና መብት ላይ የሚፈጸም ጥቃት ነው” ብለዋል።
ከአውሮፓውያኑ 1983 ጀምሮ በካናዳ ፅንስ የማቋረጥ መብት ቢረጋገጥም በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የፅንስ ማቋረጫ ክሊኖኮች ስለሌሉ በበርካታ ገጠራማ አካባቢዎች በርካታ ሴቶች ለሰዓታት በመኪና መጓዝ ይጠበቅባቸዋል።
አሜሪካ ለአለም ሞዴል ነች - ጌታ ፓንዲ፣ ደልሂ፣ ህንድ
በህንድ የሥርዓተ-ፆታ ፍትህ ተሟጋቾች ፍርዱን "የሴቶችን መብት ወደኋላ የጎተተ እርምጃ ነው" ሲሉ ገልፀው በጥንታዊው "ቪክቶሪያ ሥነ ምግባር" የተመራ ነው ብለውታል።
የህክምና ባለሙያና፣ የህክምና ሥነ ምግባርን ለዶክተሮች የሚያስተምሩት ተሟጋችና ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ቬና ጄኤስ፣ ውሳኔው በአሜሪካ ውስጥ የሴቶች መብት ላይ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይም አስከፊ ተጽእኖ ይኖረዋል ብለዋል።
"አሜሪካ በአጠቃላይ ለዓለም ሞዴል ነች እና እኔ የምሰጋው በሆነ ወቅት ህንድ ይህንን በመከተል ተመሳሳይ ሕግ ልታወጣ ትችላለች" የሚሉት ፕሮፌሰሯ "እና የማንፈልጋቸውን ልጆች ለማሳደግ እንገደዳለን" ብለዋል።
ይህም በሴቶች እና ህጻናት አካላዊ እና አዕምሮአዊ ጤንነት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ዶክተር ቬና ያስረዳሉ።
በህንድ ከአውሮፓውያኑ 1971 ጀምሮ ፅንስ ማስወረድ ሕጋዊ ቢሆንም ለዚህ ግን ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው።












