የኢስማኤል ሃኒያ ግድያን ተከትሎ በመካከለኛው ምሥራቅ ሌላ ጦርነት አይቀሬ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሐማስ የፖለቲካ መሪ የሆኑት ኢስማኤል ሃኒያ ኢራን ውስጥ መገደላቸውን ተከትሎ በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ የሚስፋፋ ጦርነት ሊከሰት እንደሚችል አገራት ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
የአሜሪካ፣ የሩሲያ እና የቱክር መንግሥታት ግድያው በጋዛ በሚካሄደው ጦርነት ሰበብ ውጥረት ውስጥ የሚገኘው የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ላይ ተጨማሪ የጦርነት የሚያስከትል ነው ብለዋል።
በእስያ አገራት ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን፤ በመካከለኛው ምሥራቅ ሌላ ጦርነት አይቀሬ ነው በማለት “ለዲፕሎማሲ መፍትሄ ግን ሁልጊዜም ቢሆን ዕድል አለ” ብለዋል።
ከአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር በተጨማሪ የሩሲያ እና ቱርክ መንግሥታት የሐማሱ መሪን ግድያን አጥብቀው ካወገዙ በኋላ፤ ግድያው በመካከኛው ምሥራቅ ጦርነትን የሚያስፋፋ ነው ብለዋል።
የጋዛን ጦርነት ለማስቆም ከእስራኤል ጋር በሚደረገው ድርድር የሐማስ ተወካይ የነበሩት ኢስማኤል ሃኒያ፤ ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 24/2016 ዓ.ም. ንጋት ላይ በኢራን መዲና ቴህራን በሚገኘው መኖሪያቸው ላይ በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸው ይፋ ሆኗል።
ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ በእስራኤል የአየር ጥቃት የኢስማኤል ሃኒያ ሦስት ልጆች እና አራት የልጅ ልጆቻቸው በእስራኤል በተፈጸመ ጥቃት ጋዛ ውስጥ መገደላቸው ይታወሳል።
የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚካሂል ቦግዳኖቭ፤ የሃኒያ ግድያ በቀጣናው ሌላ ውጥረት ይፈጥራል ብለዋል።
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ግድያውን፤ “ቴህራን ውስጥ የተፈጸመ አሳፋሪ ግድያ” ብሎ ከገለጸው በኋላ “ይህ ጥቃት በጋዛ ያለው ጦርነት ወደቀጠናው እንዲስፋፋ ያለመ ነው” ብሏል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሃኒያን ግድያ “በጭራሽ ተቀባይነት የሌለው የፖለቲካዊ ግድያ ነው” ሱሉ ገልጾታል።
ሐማስ የቁጥር አንድ የመሪውን ግድያ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ሃንዬህ በእስራኤል በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸውን አስታውቋል። ነገር ግን እስካሁን በእስራኤል በኩል የተባለ ነገር የለም።
ይህ የሐማስ መሪ በኢራን ምድር መገደል በመካከለኛው ምሥራቅ ሌላ አደገኛ ውጥረት የሚፈጥር ነው ተብሏል።
በጆርጅታወን ዩኒቨርሲቲ የመካከለኛው ምሥራቅ ጥናት መምህር የሆኑት ናዴር ሀሺም፤ የሐማስ መሪው ግድያ ቀጠናውን ከመቼው ጊዜ በላይ ወደለየት ጦርነት እንዲገባ ይገፋዋል በማለት፣ የኢራን ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው በትኩረት የሚጠበቅ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“ኢራን ውጥረቱን ከፍ ወዳለ ደረጃ መውሰድ የምትፈልግ ከሆነ የሃኒያ ግድያ ምክንያት ይሆናታል” ብለዋል።
የቢቢሲ የመካከለኛው ምሥራቅ ዘጋቢ ሂዩጎ ባቼጋ እንዲሁ ግድያው በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ውጥረት ላይ ቤንዚን እንደመርጨት ነው ይላል።
ሂዩጎ ይህ የሐማሱ መሪ ገድያ የተሰማው በቤይሩት ሌላ የሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራር በእስራኤል የመገደሉ ዜና ከተሰማ በኋላ መሆኑን በማስታወስ፤ ለሁለቱ ግሰለቦች ግድያ ሐማስ፣ ሄዝቦላ እና ኢራን የሚሰጡት ምላሽ የሚጠበቅ ነው ይላል።
የእስራኤል ጦር የሄዝቦላ መሪ ቀኝ እጅ ነበር ያለውን ፉአድ ሹከር ቤይሩት ውስጥ በፈጸመው የአየር ጥቃት መግደሉን አስታውቋል።
150 ሺህ ሚሳኤሎች እና ሮኬቶች በይዞታው ያሉት ሄዝቦላህ የሁለቱን ግለሰቦች ግድያ ተከትሎ ያለው ነገር የለም።
እስካሁን ድረስ የሄዝቦላህ እና እስራኤል የተኩስ ልውውጥ በእስራኤል እና በሌባኖስ አዋሳኝ የድንበር አካባቢዎች ተገድቦ መቆየቱን የሚያስታውሰው ሂዩጎ፤ የሁለቱ ግለሰቦች ግን እስራኤል እና ሄዝቦላህን ወደለየለት ጦርነት ሊያስገባ ይችላል ይላል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
“የሃኒዬህ ደም ፈስሶ አይቀርም”
የሐማሱ ፖለቲካዊ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ ቴህራን ውስጥ መገደሉ ኢራንን በእጅጉ አስቆጥቷታል።
ከእስራኤል ጋር ፍጥጫ ውስጥ የምትገኘው ኢራን የጋዛውን ጦርነት ተከትሎ ሶሪያ ውስጥ በእስራኤል ከፍተኛ የጦር ጄኔራሎቿ መገደላቸው ይታወሳል።
ይህንንም ለመበቀል በእስራኤል ላይ የሚሳኤል እና የሮኬት ጥቃቶችን ፈጽማ በጦርነት ዝግጁነት ውስጥ ትገኛለች።
አሁን ደግሞ በፕሬዝዳንቷ በዓለ ሲመት ላይ የተገኙትን የሐማስ መሪ ግዛቷ ውስጥ በእስራኤል መገደላቸው ለሌላ የበቀል እርምጃ እንድትነሳ ሊያደርጋት ይችላል።
ግድያውን ተከትሎም የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢስማኢል ሃኒያ ደም እንዲሁ ፈስሶ አይቀርም ብሏል።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ በሐማሱ መሪ ግድያ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፤ ሃኒያ “ኩሩ ታይጋይ ነበር” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
ቃል አባዩ መንግሥታቸው ግድያውን እየመረመረ እንደሆነ ገልጸው፤ የሃኒያ ግድያ “በኢራን እና በፍልስጤማውያን መካከል ያለውን ጥልቅ እና የማይሰበር ወዳጅነት የሚያጠናክር ነው” ብለዋል።












