በኢስማኤል ሃኒያ ግድያ እስራኤል ‘ከባድ ቅጣት’ እንደሚጠብቃት ኢራን ዛተች

ኢስማኤል ሃኒያ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ከሐማስ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ ግድያ በኋላ ኢራን በእስራኤል ላይ ‘ከባድ ቅጣት’ እንደምታደርስ ዛተች።

እስራኤል የሐማስን መሪ እንደገደለች ኢራን ገልጻለች። እስራኤል ኢስማኤል ሃኒያ ቴህራን ውስጥ ስለተገደሉበት ጥቃት ምንም አስተያየት አልሰጠችም።

ሆኖም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸው ባለፉት ጥቂት ቀናት በጠላቶቻቸው ላይ ‘ከባድ ምት’ ሰንዝራለች ብለዋል።

ይህም ቴህራን ውስጥ ጥቃት ከመፈጸሙ ከሰዓታት በፊት የሄዝቦላህ ኮማንደር ሊባኖስ ውስጥ መገደልን ይጨምራል።

ግጭቱ እየተባባሰ ይሄዳል የሚል ፍርሃት ያለ ሲሆን፣ ‘ከባድ ቀናት ከፊታችን ይጠብቁናል’ ሲሉ ዜጎቻቸውን አስጠንቅቀዋል።

“ቤይሩት ጥቃት ከደረሰ በኋላ ከሁሉም አቅጣጫ አደጋ አንዣቧል። ለሁሉም ነገር ዝግጁ ነን። በአንድነትና በቆራጥነት እንቆማለን” ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ “አስጊ የግጭት መፋፋም” በቀጠናው ሊኖር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

የፀጥታው ምክር ቤት ስለ ጉዳዩ ለመምከር ለትናንት ቀጠሮ ይዞ ነበር።

የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ የኢስማኤል ሞት “ውጊያውን አዲስ አቅጣጫ የሚያስይዝ” እንደሆነና ከፍተኛ ቅጣት እንደሚከተል አስታውቋል።

በጋዛ የተኩስ አቁም ለማድረግ ዋነኛ ተደራዳሪ ከነበሩት አንዱ ኢስማኤል ነበሩ።

የኢራን አዲስ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዘሽኪያን በዓለ ሲመትን ታድመው በሰዓታት ውስጥ ነው የተገደሉት።

ከፍተኛ የሐማስ አመራር ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም ኢስማኤል ኢራን ሳሉ ያርፉበት በነበረ ሕንጻ ውስጥ ነው ግድያው የተፈጸመው።

በዛው ሕንጻ ውስጥ ሦስት የሐማስ መሪዎችና ጠባቂዎችም አብረው ነበሩ።

ከፍተኛ የሐማስ ባለሥልጣኑ ካሕሊል አል-ሐያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፣ የተተኮሰው ሚሳዔል በቀጥታ ዒላማ ያደረገው ኢስማኤልን ነው።

ከፍተኛ የሐማስ አመራር ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ አመራሩ “ድንጋጤ ውስጥ” ገብቷል።

ከግድያው ከሰዓታት በፊት እስራኤል ከፍተኛ የሄዝቦላህ አመራር ፉዓድ ሹኩርን ቤይሩት ውስጥ መግደሏን ገልጻለች።

ባለፈው ቅዳሜ በጎላን ተራራዎች 12 ሰዎች ከተገደሉበት ጥቃት ጀርባ እሱ እንዳለ እስራኤል ታምናለች።

ሄዝቦላህም ግድያው እንደተፈጸመና አስክሬኑ በመኖሪያ ሕንጻ አካባቢ ሁለት ሕጻናትና ጨምሮ ከአራት ሰዎች ጋር መገኘቱን አስታውቋል።

ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የሄዝቦላህ አመራሮች ዒላማ ሲደረጉ ቡድኑ ወደ እስራኤል ሮኬቶች በመቶስ የአፀፋ ምላሽ ይሰጣል። አሁንም ይህ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።

አሜሪካ ዜጎቿ ወደ ሊባኖስ እንዳይሄዱ ስታስጠነቅቅ፣ ዩኬ ዜጎቿ እንዲወጡ ማሳሰቢያ ሰጥታለች።

ብዙ አየር መንገዶች ወደ ቤይሩት የሚያደርጉትን ጉዞ ሰርዘዋል።