የፍልስጤም ነጻነት አቀንቃኙ እና የሐማሱ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ ግድያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሐማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ ማክሰኞ ሌሊት ሐምሌ 23/ 2016 ዓ.ም. ለረቡዕ አጥቢያ ስምንት ሰዓት ላይ በኢራኗ መዲና ቴህራን ቤት ውስጥ ሳሉ ተገድለዋል።
እስማኤል ሃኒያ ከአንድ ጠባቂያቸው ጋር መገደላቸውን ንጋት ላይ ለዓለም ይፋ ያደረገው የኢራን አብዮታዊ ዘብ ነው።
“የሐማስ እስላማዊ ንቅናቄ የፖለቲካ ቢሮ ኃላፊ የኢስማኤል ሃኒያ መኖሪያ ቤት ጥቃት ደርሶበታል። በዚህም ጥቃት እሳቸው እና አንድ ጠባቂያቸው ሰማዕት ሆነዋል” ሲል የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የዜና ድረገጽ የሆነው ሴፓ አትቷል።
አልጀዚራን ጨምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በመቅረብ የእስራኤል ዘመናትን ያስቆጠረ ወረራ፣ መዋቅራዊ ጭቆና፣ የፍልስጤምን የነጻነት እንቅስቃሴ በመናገር የሚታወቁት እና የሐማስ መለያ የነበሩት የ62 ዓመቱ ኢስማኤል ሃኒያ ወደ ኢራን ያቀኑት በአዲሱ ፕሬዚዳንት ማስዑድ ፔዜሽኪያን በዓለ ሲመት ላይ ለመታደም ነበር።
ኢስማኤል ሃኒያ የተገደሉት በኢራን መዲና ቴህራን በስተሰሜን በሚገኝ ለጦር ዘማቾች በተመሠረተ “ልዩ መኖሪያ” ውስጥ አርፈው ሳለ እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል።
'ዘ ታይምስ ኦፍ እስራኤል' የተሰኘው የእስራኤል ሚዲያ ሃኒያ በሚሳኤል ጥቃት መገደላቸውን ዘግቧል።
ከኢራን ከፍተኛ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጋር ግንኙነት ያለው 'ኑር ኒውስ' እንደዘገበው ደግሞ የሐማሱ መሪ ከአየር በተወነጨፈ ጥቃት ተገድለዋል ብሏል።
ግድያው “የቴህራንን መከላከያ ለማዳከም የተቃጣ አደገኛ ቁማር ነው” ሲልም ፈርጆታል።

ጥቃት በቤይሩት እና ቴህራን
የሃኒያ መገደል የተሰማው እስራኤል በወረራ በያዘቻቸው የጎላን ተራራዎች የሮኬት ጥቃት አድርሷል ያለችውን የሄዝቦላህን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ መግደሏን ባሳወቀች 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው።
የአየር ጥቃቱ የሄዝቦላህ ከፍተኛ አዛዥ የሆነውን ፉአድ ሹክርን ለመግደል ያለመ እንደነበር የተነገረ ሲሆን፣ ፉአድ በወቅቱ ከደቡባዊ ቤይሩት ወጣ ብሎ በሚገኝ ህንጻ ውስጥ የነበረ ሲሆን በሕይወት ይኑር ይሙት የተባለ ነገር የለም።
የሃኒያ ግድያ በመካከለኛው ምሥራቅ የኢራን አጋሮች ሐማስ፣ ሄዝቦላህ፣ የየመን ሁቲዎች እና በኢራቅ ውስጥ የታጠቁ ቡድኖችን ለብቀላ ሊያነሳሳ ይችላል ተብሏል።
ኢራን “የግዛቷን አንድነት፣ ክብሯን፣ ሉዓላዊነቷን እንዲሁም ኩራቷን ትጠብቃለች። በቴህራን ሃኒያን የገደሉትን አሸባሪ ወራሪዎች በፈሪ ተግባራቸው እንዲጸጸቱ ታደርጋለች” ሲሉ አዲሱ የኢራን ፕሬዚዳንት ማስዑድ ፔዜኪሽያን ረቡዕ ዕለት በኃይለ ቃል ተናግረዋል።
ጠላቶቼ ናቸው የምትላቸውን ፖለቲከኞች አድና በመግደል የምትታወቀው እስራኤል የሐማሱን የፖለቲካ መሪ ግድያ በይፋ አላረጋገጠችም።
ነገር ግን 'ጠፍቷል' የሚል ማህተም የተደረገበት የሃኒያን ምሥል የእስራኤል መንግሥት ቢሮ ፕሬስ በፌስቡክ ገጹ ላይ ለጥፏል።
የሐማስ ከፍተኛ አመራር “በቴህራን፣ ኢራን ውስጥ በተነጣጠረ ጥቃት መገደሉን” ቢገልጽም ጥቃቱ በእስራኤል ስለመፈጸሙ ያለው ነገር የለም። ኋላ ላይ ግን ይህ ልጥፍ ከአንድ ሰዓት በላይ ከቆየ በኋላ ያለ ምንም ማብራሪያ እንዲነሳ ተደርጓል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“በሃኒያ ግድያ ላይ አልተሳተፍኩም” አሜሪካ
ሃኒያ በተገደሉበት በተመሳሳይ ዕለት አሜሪካ የኢራቅ የንቅናቄ ኃይል የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት የፈጸመች ሲሆን፣ ይህም በመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣናዊ ጦርነት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
ከሐማሱ መሪ ሃኒያ ግድያ ጋር ተያይዞ የአሜሪካ ተሳትፎ እየተነሳ ሲሆን፣ ይህንንም አስመልክቶ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ምላሽ ሰጥቷል።
አሜሪካ በኢራን በተፈጸመው የሐማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ ግድያ ውስጥ “አልተሳተፈችም ወይም አታውቅም” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አንቶኒ ብሊንከን ተናግረዋል።
ሃኒያ ያሉበትን ቦታ ለማወቅ እና ለመግደል ያገለገለው የስለላ መረጃ “የአሜሪካን እርዳታ” እንደሚጠቁም የአልጀዚራ የመከላከያ አርታኢ አሌክስ ጋቶፖሎስ ተናግሯል።
“የስለላ መረጃ [ኢንተለጀንስ] ቁልፍ ጉዳይ ነው። በዓለም ላይ ያለ ማንኛውም መሳሪያ በሚመራው ኢንተለጀንስ ላይ ይመሠረታል። ትክክለኛነቱም በዚህ ይወሰናል” ብሏል።
የኢራን ተቃዋሚዎች እንዲሁም ሞሳድ መሬት ላይ መረጃ ለማግኘት ጥቅም ላይ መዋላቸውን አርታኢው ጠቁሞ “እንዴት ሞተ የሚለው ብዙ ጠቃሚ አይደለም፤ ዋነኛው የመራው ኢንተለጀንስ ስለሆነ ነው” ይላል።
አሜሪካን እና ሌሎች ምዕራባውያን እስራኤል ወዳጆች ኢስማኤል ሃኒያን እና የሚመሩትን ድርጅታቸውን በሽብር ቡድንነት የፈረጁት ሲሆን፣ ግድያውን በተመለከተ ምንም ከመናገር ተቆጥበዋል።
ኢራን በበኩሏ በሃኒያ ላይ ለተፈጸመው ግድያ አሜሪካ ኃላፊነት አለባት ያለች ሲሆን፣ ለዚህም ምክንያቱ ለእስራኤል በምትሰጠው ድጋፍ ምክንያት ነው ብላለች።
የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ኻሚኒ በአገራቸው ምድር ላይ ለተፈጸመው ግድያ አጻፋዊ ምላሽ እንደምትሰጥ እና እስራኤል “ከባድ ቅጣት” እንደሚጠብቃት ዝተዋል። የሃኒያን ግድያ መበቀል የኢራን ግዴታ ነው ሲሉም ተሰምተዋል።
የፕሬዚዳንቷን በዓለ ሲመት ለመታደም በቴህራን የተገኙት ሃኒያን መጠበቅ ሳይቻል በግዛቷ መገደል ኢራንን አጸፋዊ እርምጃ እንድትወስድ ሊያነሳሳትም ይችላል እየተባለ ነው።
በቴህራን የመካከለኛው ምሥራቅ ጥናት ማዕከል ባልደረባ የሆኑት አባስ አስላኒ የሃኒያን በኢራን መዲና መገደልን አስመልክቶ ለአልጀዚራ እንደተናገሩት “በቴህራን የተፈጠረው ነገር ለኢራን የደኅንነት ተቋም መጥፎ ሁኔታ ነው። ለዚህም ነው ኢራን አጸፋዊ ምላሽ መስጠት እንዳለባት የሚሰማት” ብለዋል።
ኢራን አጸፋዊ ምላሽ መስጠቷ የማይቀር ነው ቢሉም ምን ዓይነት ምላሽ ሊሆን ይችላል በሚለው ላይ ግን እርግጠኛ አይደሉም። የሚሰጠው ምላሽ የሚታይ ይሆናል የሚሉት አባስ ከደኅንነት ተቋሙ አንጻር መሠረታዊ ጉዳይ ነው በማለት አጽንኦት ይሰጣሉ።
እስራኤል በቴህራን ግዛት ላይ ጥቃት በመሰንዘር የሐማስን መሪ መግደሏ ለኢራን መልዕክት እንደሆነ እና እስራኤል ጦርነቱን ለመቀጠል ቁርጠኛ ውሳኔ አላት የሚለውንም አሳይቷል ተብሏል።

የእስራኤል በሐማስ መሪዎች ላይ ያነጣጠረ ግድያ
እስራኤል ምንም እንኳን የሐማሱን መሪ ገድያለሁ ባትልም የእስራኤል ጥቃት ስለመሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው ተብሏል። አንድ ሚኒስትሯም በሃኒያ ሞት ደስታቸውን ገልጸዋል።
ግድያውን “በመኖሪያ ቤታቸው ላይ የተፈጸመ በተንኮል የተሞላው የጽዮናውያን ወረራ” ሲል ነው ሐማስ የጠራው።
እስራኤል ለመግደል ስታድናቸው የነበረው ሃኒያን ብቻ ሳይሆን ቤተሰባቸውንም ዒላማ አድርጋ ከጥቂት ወራት በፊት በሰሜን ጋዛ ሻቲ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ በፈጸመችው የአየር ጥቃት አስር ቤተሰቦቻቸውን ገድላለች።
በዚያን ወቅትም የጋዛ ጦርነት ከተጀመረበት ከመስከረም መጨረሻ በኋላ 60 የሚሆኑ የቤተሰብ አባሎቻቸው ተገድለውብኛል ሲሉ ተናግረዋል። በሚያዝያ ወር ሦስቱ ልጆቻቸው እና አራት የልጅ ልጆቻቸው በጋዛ ሻቲ ካምፕ መኪና ውስጥ ሳሉ በቦምብ ጥቃት ተገድለዋል።
ሐማስን እንዲሁም የሐማስን አመራሮች ለማጥፋት በተደጋጋሚ እስራኤል ስትዝት ቆይታለች። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ ውስጥም ሆነ ከጋዛ ውጪ የሐማስ መሪዎችን ኢላማ አደርጋለሁ ሲሉም ተደምጠዋል።
ሃኒያ እንዲሁም የሐማስ መሥራች እና መንፈሳዊ መሪ የሆኑትን ሼክ አህመድ ያሲን በአውሮፓውያኑ 2003 ከእስራኤል የግድያ ሙከራ ተርፈዋል።
እስራኤል እነ ሃኒያ የነበሩበትን ህንጻ በአየር ጥቃት ከመምታቷ ከሰኮንዶች በፊት ነበር ያመለጡት።
ሆኖም ከወራት በኋላ ሼክ ያሲን ከሶላት በኋላ ከመስጊድ ሲወጡ በእስራኤል ወታደሮች ተገደሉ። ከዚህ በኋላ በነበረው ወርም እሳቸውን የተኩት አብዱልአዚስ አል ራንቲሲን በእስራኤል የሚሳኤል ጥቃት ጋዛ ውስጥ ተገድለዋል።
እስራኤል በጋዛ እያካሄደችው ካለው መጠነ ሰፊ ዘመቻ አንጻር እንደ ዋነኛ ዓላማ አድርጋ ከያዘቻቸው ጉዳዮች መካከል ታጣቂውን ሐማስ መደምሰስ ብቻ ሳይሆን ሐማስን እንደ እንቅስቃሴ ማጥፋት እንደሆነ ይነገራል።
በአሁኑ ወቅት እንቅስቃሴውን ማጥፋቱ የማይቻል እንደሆነ የታየ ሲሆን፣ የሐማስ ሁሉንም አመራሮች መግደል እንደ አንድ ዒላማ በእስራኤል እንደተያዘም ተንታኞች ይናገራሉ።
እንደ ሐማስ እና ሄዝቦላህ ያሉ ቡድኖችን አመራሮች መግደል እስራኤል እንደ ስትራቴጂ ይዛዋለች የሚባል ሲሆን፣ ነገር ግን ከዚህ በፊት የተፈጸሙ ግድያዎች እንቅስቃሴዎችን ከማክሰም ይልቅ ሕዝባዊ ድጋፋቸው እየጨመረ መምጣቱ ተስተውሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሃኒያ በፍልስጤማውያን እንቅስቃሴ ያላቸው ስፍራ
ሃኒያ በዓለም ዙሪያ የፍልስጤም ትግል ተምሳሌት እንዲሁም ትግል ካቀጣጠሉ እና ድጋፍ እንዲገኝ ካደረጉት ታዋቂ የሐማስ መሪዎች አንዱ ነበሩ።
ሃኒያ በአውሮፓውያኑ 2006 በፍልስጤም አስተዳደር መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለአጭር ጊዜ አገልገግለዋል። በፍልስጤም የነጻነት ንቅናቄ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያላቸው ሃኒያ እንደ ሌሎች የእሳቸው ትውልድ አባላት ፖለቲከኞች፣ የነጻነት ታጋዮች በእስራኤል ጥርስ ተነክሶባቸው ነበር።
ሃኒያ የተወለዱት በጋዛ በሚገኘው ሻቲ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ነው። የእሳቸው ወላጆች እስራኤል እንደ አገር በአውሮፓውያኑ 1948 ስትመሠረት ከአስቃላ ከአሁኗ አሽኬሎን ተፈናቅለው ነው ወደ ጋዛ የመጡት።
ሃኒያ በወጣትነታቸው በጋዛ በሚገኘው ኢስላሚክ ዩኒቨርስቲ የአረብኛ ሥነ ጽሁፍን ያጠኑ ሲሆን፣ በነቃ ተሳትፏቸውም ይታወቁ ነበር። በአውሮፓውያኑ በ1983 ቆይታቸው የሐማስ መሠረት ነው የሚባለውን ኢስላሚክ ስቱደንት ብሎክን ተቀላቀሉ።
ኢንቲፋዳ ተብሎ የሚጠራው የእስራኤልን ወረራ የሚቃወመው ሰፊው የፍልስጤም አመጽ በአውሮፓውያኑ 1987 ሲቀሰቀስ ሃኒያ በዚህ ተቃውሞ ተሳታፊ ነበሩ።
ሐማስም በዚሁ ዓመት ሲሆን የተመሠረተው ሃኒያ በዕድሜ ትንሹ አባል ነበሩ። ሃኒያ በእስራኤል ቢያንስ ሦስት ጊዜ ታስረዋል።
ረጅሙን የእስር ጊዜ ሦስት ዓመት ከቆዩ በኋላ በአውሮፓውያኑ 1992 በመቶዎች ከሚቆጠሩ የሐማስ አባላት፣ የሐማስ አመራሮች እና ሌሎች የፍልስጤም ንቅናቄ አባላት ጋር ወደ ሊባኖስ ተባረሩ።
በፍልስጤም እና በእስራኤል የተፈረመውን የኦስሎ ስምምነት ተከትሎ ሃኒያ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ጋዛ ተመለሱ። እስራኤል አስራቸው የነበሩት የሐማስ መንፈሳዊ መሪ እና መሥራች ሼክ አህመድ ያሲን ሲፈቱ ሃኒያ ረዳት ሆነው ተሾሙ።
ሃኒያ በአቋማቸው እንዲሁም መገናኛ ብዙኃን ላይ በተደጋጋሚ በመቅረባቸው ከአውሮፓውያኑ 2003 በኋላ እውቅናን ያተረፉ ሲሆን፣ ይህም እስከተገደሉበት ድረስ ቀጥሏል ተብሏል።
ሐማስ ከምሥረታው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓውያኑ 2006 በፍልስጤም የሕግ አውጪ ምርጫ ላይ መወዳደራቸውን ተከትሎም የሃኒያ በፍልስጤም ትግል ያላቸው ስፍራ ጎላ።
በርካቶችን ባስደነገጠ መልኩ ሐማስ ከፍተኛ ድምጽ ማግኘቱን ተከትሎ ሃኒያ በፍልስጤም አስተዳደር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ።
ሐማስ በፍልስጤም አስተዳደር ውስጥ ባለው ማዕከላዊ ሚና ያልተደሰቱት ምዕራባውያን መንግሥታት ለአስተዳደሩ የሚሰጡትን እርዳታ አቆሙ። አሜሪካ እና ሌሎች በርካታ የምዕራባውያን መንግሥታት ሐማስን በአሸባሪነት ፈርጀውታል።
በምዕራቡ ዓለም ግፊት የተነሳ በሃማስ እና ሌላኛው ፓርቲ ፋታህ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ የአስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ ሃኒያን አሰናብተው መንግሥቱን በተኑ።
ይህንንም ተከትሎ ነው በጋዛ በሐማስ የሚመራ መንግሥት ተቋቁሞ ሃኒያም መሪ ሆኑ። ሐማስ የጋዛን አስተዳደር ሲረከብ እስራኤል ከጎረቤቷ ግብፅ ጋር በመተባበር ጋዛን ለ17 ዓመታት በዘለቀ ከበባ ውስጥ አቆይታታለች።
ሃኒያ በጋዛ ሰርጥ ላይ የተጣለው ከበባ የፍልስጤምን ትግል እና እንቅስቃሴ ሊያዳክም አይገባም ሲሉም ይደመጡ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2017 የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተሾሙትን ካሊድ ሜሻልን በመተካት ቦታውን በመረከብ በቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ ኃላፊነት ያዙ።
ሃኒያ የሐማስን ዲፕሎማሲ ከቱርክ እና ከኳታር መዲና ዶሃ ሆነው በመምራት በተኩስ አቁም ውይይት ላይ ተደራዳሪ ነበሩ።
እንዲሁም የፍልስጤምን ነጻነት ቁልፍ ደጋፊ ከሆነችው ኢራን ጋር ሲነጋገሩ ቆይተዋል። ሃኒያ እስከተገደሉበት ዕለት ድረስ በአብዛኛው መቀመጫቸው በኳታር ነበር።












