በፈረንሳይ ምርጫ ስደተኛ ጠል የሆነው ፓርቲ ከፍተኛውን የምክር ቤት ወንበር አሸነፈ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS/Yves Herman
ቀኝ ዘመሙ ስደተኛ ጠል ፓርቲ የፈረንሳይ ምክር ከፍተኛውን ወንበር እንደሚይዝ ተገመተ።
ከፓርቲው መሪዎች አንዷ የሆኑት ማሪን ለ ፔን ከድምጽ አሰጣጥ በኋላ የፕሬዝዳንት ማክሮን ስብሰብ “ተጥረግርጎ ወጥቷል” ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።
ራሊ ናሽናል የተባለው ቀኝ ዘመም ፓርቲ ከምክር ቤቱ አጠቃላይ ወንበር 33.2 በመቶ እንደሚያሸንፍ የተገመተ ሲሆን፤ ግራ ዘመሙ ጥምር ፓርቲ 28.1 በመቶ ድምጽ ሲያገኝ የማክሮን ስብስብ ደግሞ 21 በመቶ ድምጽ ማግኘቱ ተመልክቷል።
ይህ የፈረንሳይ ምርጫ የተደረገው ከታቀደለት ጊዜ ቀድሞ ነው። ከጥቂት ሳምንታት በፊት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኤማኑኤል ማክሮን ተቀናቃኛቸው በአውሮፓ ኅብረት አገራት የፓርላማ ምርጫ ላይ ስኬት ማግኘታቸውን ተከትሎ የፈረንሳይ ፓርላማን በትነው አስቸኳይ ምርጫ መጥራታቸው ይታወሳል።
በፈረንሳይ ፖለቲካ ውስጥ የማክሮን ተቀናቃኝ የሆኑት የማሪን ለ ፔን ቀኝ ዘመም ናሽል ራሊ ፓርቲ በአውሮፓ የፓርላማ ምርጫ ስኬትን አስመዝግቧል። በአውሮፓ ፓርላማ ምርጫ ከፈረንሳዩ በተጨማሪ የጀርመን፣ የግሪክ፣ የፖላንድ እና የስፔን ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች ስኬታማ መሆናቸው ይታወሳል።
የ28 ዓመቱ የራሊ ናሽናል ፓርቲ መሪ የሆኑት ጆርዳን ባርዴላ “ፈረንሳይዊያን ድምጻቸውን ከሰጡን የሁሉም ፈረንሳዊ ጠቅላይ ሚኒስትር እሆናለሁ” ብለዋል።
በፈረንሳይ ታሪክ በፓርላማ ምርጫ ቀኝ ዘመም ፓርቲ አብላጫ ወንበር ይዞ አያውቅም።
የራሊ ናሽናል ፖርቲ ምልክት ተደርገው የሚታዩት መሪን ለ ፔን እና ጆርዳን ባርዴላ ከአጠቃላይ 577 የምክር ቤቱ ወንበር 289 ማሸነፈን ያልማሉ።
ይሁን እንጂ ድህረ ምርጫ ግምቶች ፓርቲው ከሌሎች ፓርቲዎች የተሻለ ወንበር ቢያዝም 50 በመቶ የምክር ቤት ወንበር እንደማያሸንፍ አሳይተዋል።
ፓርቲው ከ50 በመቶ በላይ ወንበር ካልያዘ በኢሚግሬሽን፣ በታክስ ቅነሳ እንዲሁም ከሕግ እና አስተዳደር ጋር የተያያዙ ፖሊሲዎቹን ለማስፈጸም ይቸገራል።
በወጣት መሪ የሚመራው ናሽናል ፓርቲ ከሦስት ፈረንሳይዊ ቢያንስ የአንዱን ድጋፍ ለማግኘት ባለፉት ዓመታት ብዙ ሰርቷል።
በጸረ ስደተኛ አቋሙ የሚታወቀው ፓርቲው ስልጣን ከያዘ ሞባይል ስልኮችን ከትምህርት ቤት ከማገድ እስከ ለውጪ ዜጎች የሚሰጥ ጥቅማጥቅምን ማስቀረት የሚሉ ፖሊሲዎቹን እንደሚተገብር ሲገልጽ ነበር።
ስደተኛ-ጠል ናቸው የሚባሉት ቀኝ አክራሪ ፓርቲን የሚመሩት ማሪን ለ ፔን ከዚህ ቀደም 3 ጊዜ ፈረንሳይን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ለምርጫ ቀርበው ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
ለ ፔን በምርጫ ቅስቀሳዎች ወቅት በአደባባይ ኢስላማዊ ሒጃብ እንዳይለበስ እከለክላለሁ እንዲሁም ፈረንሳይ ከአውሮፓ ኅብረት እንድትወጣ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ አደርጋለሁ ሲሉ ተደምጠዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ወደ ፈረንሳይ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር መቀነስ የሚያሰችል ፖሊሲ እንደሚያረቁ ጭምር ተናግረዋል።












