“እህቴን የሱዳን ወታደሮች ሲያንገላቷት ቪዲዮ ላይ አየሁ”

የፎቶው ባለመብት, Nerayo Ghebru Tesfamichael
ምህረት ገብሩ በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት የተሰራጩ ቪዲዮችን ስልኳ ላይ እየተመለከተች ነው።
ቪዲዮቹ በእርስ በእርስ ጦርነት እየታመሰች በምትገኘው ሱዳን ወታደሮች የጎረቤት አገራት ዜጎችን ሲደበድቡ እና ሲያንገላቱ የሚያሳዩ ናቸው።
ምህረት በእነዚያ ቪዲዮች ላይ ያየችውን ማመን ተሳናት።
ምህረት የገዛ እህቷ በሰው አገር በወታደሮች ስትደበደብ እና ስትሰቃይ ተመለከተች።
“ሉዋምን ወዲያው ነበር የለየኋት። በጣም የማውቀውን ብርቱካናማ ስካርፍ ነበር ያደረገችው። ጫማዋንም እንዲሁ አውቀዋለሁ” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
ምህረት እና ሉዋን ኤርትራውያን ናቸው። ልክ እንደ በርካታ ኤርትራውያን ሉዋም ገብሩ በኤርትራ የሚጠብቃትን አስገዳጅ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት በመሸሽ ከአገር ተሰደደች።
ሉዋም እአአ 2019 ላይ ኢትዮጵያ ገባች። የ24 ዓመቷ ወጣት በስደት በኢትዮጵያ ከመኖር ይልቅ አደገኛ ጉዞ በማድረግ ወደ አውሮፓ መድረሰን አልማለች።
ምህረት እንደምትለው እህቷ ሉዋም በሱዳን ያለውን ጦርነት አደጋ ባለመፍራት በሊቢያ በኩል አድርጋ አውሮፓ ለመግባት ከኢትዮጵያ መነሳቷን ትገልጻለች።
ሉዋም ወደ ሱዳን ጉዞ ከመጀመሯ ከወራት በፊት በሱዳን መንግሥት ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪዎች መካከል የተፈጠረ አለመግባባት ወደ ለየለት ጦርነት አምርቶ አገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ገብታለች።
የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ ምዕራባውያን አገራት ዜጎቻቸውን በፍጥነት ከሱዳን አስወጡ። በአገሪቱ የቀሩ ስደተኞች እንዲሁም እንደ ሉዋም ያሉ ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ ሱዳን የገቡ ስደተኞች ግን በተዋጊዎቹ ኃይሎች በዐይነ ቁራኛ እየታዩ የጦር ወንጀለኛ ተደርገው እየታሰሩ ይገኛሉ።
“ለረዥም ጊዜ ድምጿን ሳንሰማ ቆይተንየሆነ ጊዜ ሱዳን ከደረሰች በኋላ ደውላ፤ 'ምንም አታስቡ አሁን ሱዳን ደርሰናል። ምናልባት በቀጣይ ሳምንት ሊቢያ እንደርሳለን' ብላን ነበር።”
ሉዋም አውሮፓ እናስገባሻለን ያሏት ሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ሕይወቷን አደጋ ላይ ይጥላሉ ብላ ጨርሻ አልጠረጠረችም።
ሉዋም በእነዚያ በሚረብሹ ቪዲዮች ላይ ሚያዝያ ወር 2016 ዓ.ም. ከመታየቷ በፊት ድምጿ ለአምስት ወራት ጠፍቶ ቆይቷል።
ቢቢሲ ባደረገው ማጣራት እነዚያ ቪዲዮች ኢንተርኔት ላይ የተለቀቁት መጋቢት 29 ወይም 30/2016 ዓ.ም. ሊሆን እንደሚችል አረጋግጧል።
በቪዲዮው ላይ የሱዳን ጦር ጄኔራል ከሶማሊያ፣ ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ ወደ 50 የሚጠጉ ቅጥረኛ ወታደሮችን ማርከናል እያሉ ስደተኞቹን የጭንት መኪና ላይ ሲያግዟቸው ይታያል።
ስደተኞቹ የተያዙት ከመዲናዋ ካርቱም በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኘው እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እንደ ጦር ካምፕ አድርጎ ከሚቀምበት አካባቢ የነበረውን ከባድ ውጊያ ሲሸሹ እንደሆነ ይገመታል።
በቪዲዮ ላይ የሱዳን መንግሥት ጦር ጄኔራል “ቅጠረኛ ወታደሮቹ“ ” ዋዲ ሰይደና ወደተባለ የጦር ካምፕ እንደሚላኩ ሲናገሩ ይሰማል።
በዚህ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የሱዳን መንግሥት ጦር ሠራዊትን እየተዋጋ ያለው የሐምዳን ዳጋሎ ኃይል የውጭ ዜጋ የሆኑ ቅጠረኛ ወታደሮችን ይጠቀማል የሚል ያልተረጋገጠ ሪፖርት ሲወጣ ቆይቷል።

የፎቶው ባለመብት, Social media
በተንቀሳቃሽ ምሥሉ ላይ ሉዋምን ጨምሮ በርካታ ስደተኞች በጠባብ መጋዘን ውስጥ ታጭቀው ያሳያሉ።
በስደተኞቹ ፊት እጅግ ፍርሃት እና ጭንቀት ይታያል።
ምህረት ከእህቷ በተጨማሪ በኤርትራ ጎረቤቷ የነበረ ሌላ ወጣት ልጅንም በቪዲዮ ላይ ተመልክታለች።
ምህረት በአሁኑ ወቅት እህቷ ስላለችበት ሁኔታ ጨርሶ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌላት ትናገራለች።
“በሱዳን መንግሥት ተይዘዋል ከመባል ወጪ ምንም የምናውቀው ነገር የለም” በማለት ምህረት ትገልጻለች።
ሌሎች ኤርትራውያንን ጨምር በሱዳን ስደተኛ ተብለው ተመዝገበው የነበሩ ዘመዶቻቸው በሱዳን ጦር ተይዘዋል ከተባለ በኋላ የደረሱበት እንደማይታወቅ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከእነዚህ መካከል የ17 ዓመቱ ዮናታን ተስፋሥላሴ እና የ20 ዓመቱ ኤደመን ኪዳኔ ቤተሰቦች ይገኙበታል።
ሁለቱ ወጣቶች በሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች አማካይነት ከኤርትራ ከወጡ በኋላ ጥቅምት 2016 ዓ.ም. በሱዳኗ ከሰላ ግዛት የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጣቢያ ደርሰው ስደተኛ ተብለው ተመዝግበው ነበር።
አብዛኞቹ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር ቅርበት አላቸው የሚባሉ ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ በክፍያ ደኅንነታቸውን አስጠብቀው በሱዳን በኩል ከአገር እንደሚያሰወጧቸው ያሳምኗቸዋል።
ወጣቶቹን ከአገራቸው ካስወጧቸው በኋላ በውጭ ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው ተጨማሪ ገንዘብ እንዲያስልኩ ካስገደዷቸው በኋላ መንገድ ላይ ጥለዋቸው ይሰወራሉ።
ዮናታን እና ኤደመን ከአገር የወጡት ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ነበር። ይሁን እንጂ ሱዳን ከደረሱ በኋላ ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ጥለዋቸው ተሰውረዋል።
ሁለቱ ወጣቶች ከሱዳን መዲና ካርቱም 190 ኪሎ ሜትር ርቃ ብምትገኘው ዋድ ማዳኒ ሳይደርሱ እንዳልቀረ ይታመናል።
ይህ አካባቢ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ኅዳር 2016 ዓ.ም. ላይ በቁጥጥር ስር ከመግባቱ በፊት አንጻራዊ ሰላም ያለበት አካባቢ ነበር።
ይሁን እንጂ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በጌዚራ ግዛት የምትገኘውን ዋድ ማዳኒ ከተቆጣጠረ በኋላ ከ300 ሺህ ያላነሱ ሰዎች አካባቢውን ጥለው ተሰደዋል።
የዮናታን ቤተሰቦች እንደሚሉት የልጃቸውን ድምጽ ለመጨረሻ ጊዜ የሰሙት ኅዳር 2016 ዓ.ም. ላይ ነበር። ዮናታን ከሌሎች ስደተኞች ጋር በመሆን ወደ ደቡብ ሱዳን ለመጓዝ እየተዘጋጀ እንደሆነ ነግሯቸው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የዮናታን እህት ዊንታ ተስፋሥላሴ ደቡብ ሱዳን ከደረሱ ሌሎች ስደተኞች እንደሰማችው ከሆነ ዮናታን ራቤካ በተባለች ከተማ በሱዳን ጦር በቁጥጥር ስር ሳይውል አይቀርም።
ስደተኞቹ ለዊንታ እንደተናገሩት ከሆነ ራቤካ በተባለች የሱዳን ከተማ በአገሪቱ ጦር የተያዙ ስደተኞች ሲንጃህ እና ሴናር ወደተባሉ አንስተኛ ከተሞች ተወስደዋል።
“መላው ቤተሰብ እጅግ ተጨንቋል። ምንም ማድረግ አንችልም። ደህና መሆኑን መስማት እንፈልጋለን። በዚህ ለጋ ዕድሜው ይህን ሁሉ ስቃይ ማየት የለበትም። በሱዳን ካለው ጦርነት ውስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ የለውም” በማለት ዊንታ የ17 ዓመት ወጣት ስለሆነው ወንድሟ ትናገራለች።
የኤድመን ቤተሰብ እንዲሁ ስለልጃቸው የሰሙት ዋድ ማዳኒ ከተማ ሳለ ነበር።
“ደላሎቹ ወንድሜ በሱዳን ወታደሮች ታስሮ እንደሚገኝ ነግረውኛል” በማለት በአንጎላ የምትገኘው እህቱ አዲያም ኪዳኔ ለቢቢሲ ተናግራለች።
አዲያም ብቸኛ የመረጃ ምንጯ የሆነው ደላላ በአሁኑ ሰዓት ስልኳን ሰለማያነሳ ወንድሟ ስላለበት ሁኔታ ምንም መረጃ እንደሌላት ትገልጻለች።
“ለእናታችን ለረዥም ጊዜ ወንድማችን ስላለበት ሁኔታ ሳንነግራት ቆይተናል። በመጨረሻ ወንድማችን የት እንዳለ እንደማናውቅ ስንነግራት እራሷን ሳተች። ሁላችንም ጭንቀት ውስጥ ነን። በየቀኑ ምን ገጥሞት ይሆን? እያልን እንጨነቃለን።”

የፎቶው ባለመብት, Adiam Kidane
ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙ ከሆነ የሱዳን ጦር ከዋድ ማዳኒ ከተማ ለቆ ሲወጣ እስረኞቹን ይዞ ወጥቷል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ በሱዳን ስደተኛ ተብለው የተመዘገቡ ስደተኞች በሰዱን ጦር ቅጥረኛ ወታደሮች እየተባሉ እየታሰሩ ስለመሆኑ ሪፖርቶች እንደሚደርሱት ገልጿል።
እንደ ድርጅቱ ከሆነ በሱዳን ከ147 ሺህ በላይ ኤርትራውያን እንዲሁም ከ70 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ።
ተመድ ከስደተኞች ቤተሰቦች ጥቆማ በመነሳት በርካታ ስደተኞች ታስረው ይገኛሉ በተባሉባቸው የሱዳን ከተሞች የማጣራት ሥራ ለማካሄድ ማቀዱን ለቢቢሲ ተናግሯል።
በተመሳሳይ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ቤተሰቦች የጠፉባቸውን ዘመዶች ለድርጅቱ ስልክ በመደወል ወይም ቅጽ በመሙላት እንዲያሳውቁ ጠይቋል።
የውጭ አገር ስደተኞችን እስር እና ስቃይን በተመለከተ ቢቢሲ በለንደን ለሚገኘው የሱዳን ኤምባሲ ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል።
በሱዳን ሁለት የጦር ጄኔራሎች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ በሱዳን የተቀሰቀሰውን የእርስ እርስ ጦርነት ለማስቆም ሲደረግ የቆየ ዓለም አቀፍ ጥረት ፍሬ ሳያፈራ እስካሁን ጦርነቱ እንደቀጠለ ነው።
በዚህ ጦርነት ከ15ሺህ የማያንሱ ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉ ይገመታል።
ለቢቢሲ ቃላቸውን የሰጡ ሦስቱ እህቶች ስለ እህት ወንድሞቻቸው የትኛውንም ዓይነት መረጃ ከቀይ መስቀል፣ ከተባበሩት መንግሥታትም ይሁን ከሱዳን ጦር ማግኘት እጅግ ከባድ መሆኑን ይናገራሉ።
ዊንታ “እባካችሁ፤ የመንግሥታቱ ድርጅትም ሆነ ማንኛውም አካል እባካችሁ እርዱን. . . የምናደርገው ጠፍቶናል” በማለት ስላሉበት ሁኔታ ገልጻለች።
“የሱዳን ጦር ለቋቸው ምንም ዓይነት ተሳትፎ የሌላቸው እነዚህ ወጣቶች ወደ ደቡብ ሱዳን እንዲሄዱ እንዲፈቅድላቸው እንለምናለን” ስትል ተማጽናለች።












